1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀጠለዉ የአሸባብ ጥቃት

ዓርብ፣ ጥር 6 2008

ሶማሊያ ዉስጥ የሚንቀሳቀሰዉ ፅንፈና እስላማዊ ሁድን አሸባብ ሰሞኑን በተከታታይ ሶማሊያ ዉስጥ በተለያዩ ስፍራዎች ጥቃት እያደረሰ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1HeLJ
African Union Mission in Somalia
ምስል picture-alliance/dpa/Amisom Photo /T. Jones

[No title]

ትናንት በማዕከላዊ ሶማሊያ ኤልቡር ከተማ በሚገኝ አዉሮፕላን ማረፊያ ላይ በሰነዘረዉ ጥቃት 11 ሰዎችን መግደሉ የተነገረዉ ይህ ቡድን ዛሬ ደግሞ በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኝ የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ሰፈር ላይ በሰነዘረዉ ጥቃት ቢያንስ 40 ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ የጀርመን የዜና ወኪል ዘግቧል። እንደዘገባዉ በጥቃቱ የኬንያ እና የሶማሊያን ወታደሮች ጨምሮ የአሸባብ ታጣቂዎችም ተገድለዋል።

ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለዉ የሚነገርለት የሶማሊያው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ደቡባዊ ምዕራብ ሶማልያ የሚገኝዉን የአፍሪቃ ሕብረት ወታደሮች የጦር ሰፈር ማጥቃቱ ተዘገበ። የኬንያዉ ፕሬዚዳንት አሁሩ ኬንያታ በሶማልያ የኬንያ ወታደሮች መገደላቸዉን አረጋግጠዋል። የሚያሳዝን ክስተት ሲሉ የተናገሩት ኬንያታ ስንት ወታደሮች እንደተገደሉ ግን የገለፁት ነገር የለም። የሶማልያ ጦር ሰራዊትና የዓይን እማኞች እንደገለፁት በጥቃቱ በርካቶች ሞተዋል። የሶማሊያ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ኢድሪስ አህመድ እንደተናገሩት ጥቃት አድራሾቹ ኧል-አዴ የሚገኘዉን የጦር ሰፍር በማጥቃት ከባድ ዉግያን አካሂደዉ ጉዳት አድርሰዋል። በኬንያና እና በኢትዮጵያ ድንበር አቅራብያ በሚገኘዉ ጊዶ በተሰኘዉ አዉራጃ በሚገኘዉ በዚሁ የአሚሶም የጦር ሰፈር ላይ ጥቃቱ የተጀመረው አንድ የአሸባብ አጥፍቶ በመኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ከፈነዳ በኋላ ነው። አሚሶም በጽሑፍ በሰጠዉ መግለጫ ጦር ሰራዊቱ ላይ ጥቃት መፈፀሙን ከመግለጽ በስተቀር ተጨማሪ የሰጠዉ ዝርዝር መግለጫ የለም። በጥቃቱ 63 የኬንያ ወታደሮች መገደላቸዉን አብዛኞቹ ደግሞ ክርስትያን መሆናቸዉን የአሸባብ ቃል-አቀባይ አብዲአዚዝ አቡ ሙሳብ መናገራቸዉንና የሟቾቹን አዣንስ ፍራንስ ፕሪስ ዘግቦአል። በጎርጎረሳዊው መስከረም 2015 የአሸባብ ተዋጊዎች ከመቃዲሾ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘዉ የአሚሶም የጦር ሰፍር ዉስጥ የነበሩ የዩጋንዳ ወታደሮች መግደላቸው ይታወሳል። ባለፈዉ ሰኔም አልሸባብ ሰሜን ምዕራብ መቃዲሾ በሚገኘዉ አሚሶም ጦር ሰፈር በጣለው ጥቃት የቡሩንዲ ወታደሮች ተገድለዋል። እንድያም ሆኑ 22 ሺህ ወታደሮች ያሉት የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ አሸባብን በማባረር ታላቅ ድልን ማስመዝገቡ ተመልክቶአል። በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ «AMISOM» የሚገኙ የሶማልያና የኬንያ ወታደሮች ዛሬ ጥቃት ከደረሰበት ጦር ሠፈር መነሳታቸዉ ተመልክቷል ። ናይሮቢ የሚገኘዉን ወኪላችንን ስለሁኔታዉ አነጋግረነዉ ነበር።

Somalische Friedensmission
ምስል picture-alliance/dpa/M. Makaraan

ፋሲል ግርማ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ