1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቁንጅና ውድድር

Eshete Bekeleሰኞ፣ መስከረም 10 2008

በዩጋንዳ የሚገኝ የወጣቶች ድርጅት ኤች.አይ.ቪ ፖዘቲቭ የሆኑ ወጣቶች የሚሳተፉበትን የቁንጅና ውድድር "Y+2015" በተሰኘ መርህ አካሂዷል። የውድድሩ ዋንኛ አላማ ከኤች.አይ.ቪ. ጋር የሚኖሩ ሰዎችን በራስ የመተማመን መንፈስና ግንዛቤ ማሳደግ ነው። የአሌክስ ጊታን ዘገባ እሸቴ በቀለ ያቀርበዋል።

https://p.dw.com/p/1Ga35
Uganda Schönheitswettbewerb für HIV-Positive
ምስል picture-alliance/dpa/H. Wasswa

[No title]

በዩጋንዳ ከኤች.አይ.ቪ. ጋር የሚኖሩ ወጣቶች ህይወታቸውን በተረጋጋ መንገድ እንዲኖሩ ያለመ መሰናዶ ተዘጋጅቷል። የመሰናዶው ታዳሚዎች የሚደግፏቸውን ተወዳዳሪዎች ሲያበረታቱ አየሩ በሙዚቃ ተመልቷል።

ዋይ ፕላስ ወይም ከኤች.አይ.ቪ. ጋር የሚኖሩ ወጣቶች የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው መሰናዶ የቁንጅና ውድድር ነው። የውድድሩ አዘጋጆች በመላው ዩጋንዳ በመዘዋወርና ከኤች.አይ.ቪ. ጋር የሚኖሩ ወጣቶች በመፈለግ በውድድሩ እንዲሳተፉ አበረታተዋል።

ተወዳዳሪዎቹ የልብስ ቅድ ስራዎቻቸውን ለእይታ አቅርበው፤በመድረክ ላይ ታይተውና ቢያሸንፉ ምን ሊያደርጉ እንዳቀዱ የቀረበላቸውን ጥያቄ መልሰው ሁለት አሸናፊዎች ተመርጠዋል። አሸናፊዎቹ ስለተስፋ ሊያስተምሩ በመላ አገሪቱ የሚዘዋወሩ ይሆናል። በዋናነት ግን ወጣቶች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የደም ምርመራ በማድረግ ያሉበትን ሁኔታ እንዲያውቁ ያበረታታሉ።

Uganda Schönheitswettbewerb für HIV-Positive
ምስል picture-alliance/dpa/H. Wasswa

ሲላስ ሬጋን ሉባንጋኬኔ የውድድሩ መልከመልካም ወንድ ሆኖ ተመርጧል።

«እዚህ ለመድረስ ጉዞው ረጅም ስለነበር አሁን በጣም ደስተኛ ነኝ። ለእግዚዓብሄር የዘወትር ጸሎቴ ድምጼ እንዲሰማ ነበር። አሁን ወጥቼ ወጣቶችን ለማስተማር እድሉን አግኝቻለሁ። ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከኤች.አይ.ቪ. ጋር የሚኖሩ ወጣቶች ዘንድ የሚታየውን nm,ገለልና መድሎ ለመታገል ገና መጀመሪያው ነው።»

መድረኩን ከእንስቶቹ ጎራ የቁንጅና ውድድሩን ያሸነፈችው ሮቢና ባቢርዬ ተቀላቀለችው።

«ለመድረስ አስቸጋሪ ወደ ሆኑት ሩቅ አካባቢዎች በመሄድ ከኤች.አይ.ቪ. ጋር የሚኖሩ ወጣቶች የራስ የመተማመን መንፈሳቸውን አዳብረው መገለልና መድሎን እንዲታገሉ እሰራለሁ። ከኤች.አይ.ቪ. አሁንም እየተስፋፋ ነው። በመሆኑም በአግባቡ መፍትሄ ልንሰጠው ይገባል።»

የቁንጅና ውድድሩ በዩጋንዳ ከኤች.አይ.ቪ. ጋር የሚኖሩ ወጣቶች ብሄራዊ ማህበር የተዘጋጀ ነው። የማህበሩ ሃላፊ ጃኪ አሌሲ በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ተመርምረው ውጤታቸውን ባላወቁ ሰዎች ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ለዶይቼ ቨሌ ተናግረዋል።

Uganda Schönheitswettbewerb für HIV-Positive
ምስል picture-alliance/dpa/H. Wasswa

«ወጣቶችን እንዴት ማስተባበር እንችላለን ብለን ስናስብ ነበር። ሰዎች ተመርምረው ውጤታቸውን በማወቅ በግልጽ ባለመናገራቸው በቫይረሱ የሚያዙ ቁጥር እየጨመረ ነው። መገለልን ይፈራሉ። ለምን ራሳችሁን ግልጽ አታደርጉም ተብለው ሲጠየቁ መገለልን እፈራለሁ ሲሉ ይመልሳሉ። ስለዚህ ሰዎች ኤች.አይ.ቪ. ፖዘቲቭ በመሆናቸው ሊሸማቀቁ እንደማይገባ ማሳየት ይኖርብናል። ኤች.አይ.ቪ. ሊያፍሩ ሳይሆን ሌሎች ሰዎች ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ መርዳት ይኖርባቸዋል።

ይህ ዘመቻ ሰዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የደም ምርመራ እንዲያደርጉና ውጤታቸውን በይፋ እንዲያሳውቁ ለማበረታታት የታለመ ነው።

በዩጋንዳ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከኤች.አይ.ቪ. ጋር እንደሚኖሩ ይታመናል። በቫይረሱ ከሚያዙ አዳዲስ ሰዎች አብዛኞቹ ወጣቶች እንደሆነ የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያምናል።

የአሌክስ ጊታ/እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ