1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ህዝበ ውሳኔው በሰሜን ጎንደር 12 ቀበሌዎች ይካሄዳል

ሰኞ፣ ነሐሴ 15 2009

የአማራ ክልል ለቅማንት ማህበረሰብ ራስን በራስ የማስተዳደር እውቅና ከሰጠ በኋላ 42 ቀበሌዎች በአስተዳደሩ ውስጥ እንዲካተቱ ወስኖ ነበር፡፡ የቅማንት ተወላጆች በብዛት ይኖሩባቸዋል የተባሉ 21 ቀበሌዎች ዘግየት ብለው ተጨምረዋል፡፡ የአማራ እና የቅማንት ህዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ደግሞ ህዝበ ውሳኔ ሊካሄድ ቀን ተቆርጧል፡፡

https://p.dw.com/p/2ibad
Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

ህዝበ ውሳኔው በሰሜን ጎንደር 12 ቀበሌዎች ይካሄዳል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ 12 ቀበሌዎች መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም ህዝበ ውሳኔ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡ ቦርዱ ህዝበ ውሳኔ ለመካሄድ እየተዘጋጀ ያለው የአማራ እና ቅማንት ህዝቦች በጋራ በሚኖሩባቸው ቦታዎች እንደሆነ በቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም አባይ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል፡፡

“ሁለቱ ህዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ቦርዱ ቅድመ ዝግጅት እያካሄደ ነው፡፡ ይሄ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ለቦርዱ በቀረበው ጥያቄ መሰረት ነው፡፡ ቦርዱ መጀመሪያ ደብዳቤ ከደረሰው በኋላ የቦርዱ ጽህፈት ቤት የቴክኒክ ኮሚቴ ጉዳዮችን ለመመርመር አንድ ቡድን ወደ ቦታው ሄዷል፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴው እዚያ ቦታ ሄዶ ስንት ምርጫ ጣቢያዎች መቋቋም እንዳለበት፣ ስንት የምርጫ አስፈጻሚዎች እና ታዛቢዎች ማሰማራት እንዳለብን ለይቶ ነው የመጣው፡፡ ከዚያ በኋላ ቦርዱ ከሚመለከታቸው የክልሉ አካላት ጋር ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ አዘጋጅቶ ውይይት አካሄዷል፡፡ በትላንትናው ዕለትም የጊዜ ሰሌዳውን ቦርዱ አጽድቋል” ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

በጸደቀው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የህዝበ ውሳኔው የድምጽ መስጫ ዕለት መስከረም 7 ሲሆን የድምጽ አሰጣጡ እንደተጠናቀቀ ቆጠራ እንደሚካሄድ አቶ ተስፋለም ተናግረዋል፡፡ የድምጽ ቆጠራው ውጤት በየድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በነጋታው በይፋ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የድምጽ ውጤቱ ተጠናቅሮ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚላከው ደግሞ መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚሆን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ 34 የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች እንደሚዘጋጁ እና 25 ሺህ ህዝብ ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 

ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ ጥያቄውን ያቀረበው የፌደሬሽን ምክር ቤት ባለፈው መስከረም ወር ባካሄደው ስብሰባው “በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሱ የማንነት ጥያቄዎች በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ምላሽ እንደሚያገኙ” አስታውቆ ነበር፡፡ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ፌደሬሽን ምክር ቤት ከመድረሱ በፊት በአማራ ክልል ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎች ሲሰጡበት ቆይቷል፡፡ በውሳኔው ያልረኩት የቅማንነት ተወላጆች ግን “ጥያቄያችን ሙሉ ለመሉ አልተፈታም” በሚል ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡

የቅማንት ማህበረሰብ የማንነት ጥያቄ ለበርካታ ዓመታት የቆየ ቢሆንም ጠንከር፣ ጎላ ብሎ መደመጥ የጀመረው ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ የመመረቂያ ጽሁፋቸውን የሰሩት እና በአሁኑ ወቅት በጎንደር ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር የሆኑት አቶ በላይ ሺበሺ ይናገራሉ፡፡

Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

“መነሻው እንግዲህ የፌደራል ስርዓትን ስናይ አንድ ህዝብ ብሔር ብሔረሰብ ለመባል መስፈርቶች አሉት፡፡ ያንን መስፈርት ሲያሟላ ብሔር ብሐረሰብ ይባላል፡፡ ብሔር ብሔረሰብ ከተባለ ደግሞ ራሱን በራሱን ማስተዳደሩ በቀጥታ የሚመጣ ነው፡፡ በአንቀጽ 39 ባሉ ንዑስ ቁጥሮች መሰረት ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት አለው፡፡ ስለዚህ ቅማንትም ይህን ጥያቄ ሲጠይቅ የማንነት እና የራስ አስተዳደር በማለት ሁለቱንም ነው የጠየቀው፡፡ የማንነቱን በጥያቄ ያቀረበበት ምክንያት ካሁን በፊት ማንነቱ ተክዶ ባያውቅም በ1999 ዓ.ም ተካሄዶ በነበረው የቤቶች እና ህዝብ ቆጠራ ከኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች መዝገብ ተሰርዟል፡፡ እርግጥ ከዚያ በፊት ጥያቄ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ ይበልጥ ጥያቄ እንዲጠነክር ያደረገው የመሰረዙ ጉዳይ ነው፡፡” 

የአማራ ክልል ምክር ቤት ለቅማንት የማንነት እና የራስ አስተዳደር እውቅና የሰጠው በመጋቢት 2007 ዓ.ም ነበር፡፡ የቅማንት ተወላጆች በሰሜን ጎንደር የሚገኙ 126 ቀበሌዎች በአስተዳደሩ ውስጥ እንዲካተቱ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምክር ቤቱ አርባ ሁለቱን ብቻ መቀበሉ ተቃውሞ ቀስቅሷል፡፡ የቅማንት ተወላጆች ለተቃውሞ በወጡ ወቅት በጸጥታ ኃይሎች “ከፍተኛ የኃይል እርምጃ” እንደተወሰደባቸው መንግስታዊው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሳይቀር አምኗል፡፡ ኮሚሽኑ በዚህ ዓመት ህዳር ወር ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ዘገባ መሰረት በሰሜን ጎንደር በተነሳው ግጭት 97 ሰዎች መሞታቸውን እና 86 መቁሰላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ 

ከዚያ በኋላ ስለነበረው ሂደት እና ህዝበ ውሳኔው የቅማንነትን ጥያቄ ይመልስ እንደው ለአቶ በላይ ጥያቄ አቅርበንላቸው ነበር፡፡ ህዝበ ውሳኔው “ጥሩ ጅምር ነው” ይላሉ፡፡ 

“ባለፉት ወራት የህዝብ ውይይት ተካሂዶ 21 ቀበሌዎች፣ ከ42ቱ ላይ፣ ያለ ህዝበ ውሳኔ እንዲጨመሩ [ተወስኗል]፡፡ ቀሪዎቹ፣  በቅልቅል ይኖሩባቸዋል የተባሉት ግን ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የተወሰነባቸው ናቸው፡፡ በሁለቱም ወገን በኩል ስምምነት አለ፡፡ ስለዚህ የእነዚህ የህብረተሰቡም ጥያቄ የነበረ ነው፡፡ ፍትሃዊ፣ ነጻ እና ገለልተኛ ምርጫ ከተካሄደ የሁለቱንም ህዝብ ጥያቄን የሚመልስ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ውጭ ተጠይቀው በእንጥልጥል የቀሩ፣ ገና ያልተጠቃለሉ አሉ፡፡ ህዝበ ውሳኔ ይካሄድባቸው አልተባሉም፡፡ እንደምሳሌ ብነግርህ መተማ ዮሃንስ ህዝበ ውሳኔ ይካሄድበት ተብሎ ተጠይቆ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ አላጠቃለለውም፡፡ ለምን እንደሆነ እስካሁን ግልጽ የሆነ ነገር የለም” ብለዋል፡፡  

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ