1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጎንደር የቅማንት የሕዝበ ዉሳኔ እሁድ ዕለት ይካሄዳል

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ መስከረም 5 2010

በአማራ ክልል ለቅማንት ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሕዝበ ዉሳኔ ለማካሄድ የድምፅ ሰጭዎች ምዝገባ ከነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓም እስከ መስከረም 3 ቀን 2010 ድረስ መካሄዱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጭ ቦርድ መረጃ ያመለክታል።

https://p.dw.com/p/2k4OB
የቅማንት የህዝበ ዉሳኔ
ምስል James Jeffrey

Kimant Refrendum to be Held Sunday - MP3-Stereo

እሁድንና የበዓል ቀናትን ጨምሮ ለ10 ቀን የተካሄደዉ የመራጮች ምዝገባ የህዝበ ዉሳኔ ለማካሄድ ከተገመተዉ 25,000 ህዝብ ዉስጥ ከ23,000 በላይ መራጮች መመዝገባቸዉን በቦርዱ የህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም አባይ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ፌዴሬሸን ምክርቤት የአማራና የቅማንት ህዝቦች ተቀላቅለዉ በሚኖሩባቸዉ በ12 ቀበሌዎች ዉስጥ ህዝበ ዉሳኔዉ እንዲካሄድ ቢታቀድም በስምንት ቀበሌዎች  ላይ ብቻ የመራጮች ምዝገባ መካሄዱ አቶ ተስፋለም ተናግረዋል።

መጭዉ እሁድ የህዝበ ዉሳኔዉን ለማከሄድ ከኦሮሚያ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከአድስ አበባና ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተወጣጡ ልምድ ያላቸዉ የምርጫ አስፈፃምዎች በቦታዉ እንደምገኙ አቶ ተስፋለም ይናገራሉ። ምርጫዉንም ለመታዘብም ሆነ ተሳትፎ ለማድረግ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ያገባኛል የሚሉት አካላት አልተሳተፉም ሲሉ ፌደሬሽኑንም ሆነ ምርጫ ቦርድን የሚተቹ አሉ።

ለዘመናት አብሮ ጎን ለጎን በኖረዉ የአማራና የቅማንት ማህበረሰብ መካከል የነበሩት ግኑኝነቶች «በጣም ሰላማዊ» እንደነበረ በአድስ አበባ ዩኒቬርስት በማህበረሰባዊ ጥናት ስለ አማራና ቅማንት ማህበራዊ፤ ፖለትካዊና ኤኮኖሚያዊ ግንኙነት ለዶክቴሬት ዲግሪያቸዉ በማጥናት ላይ የሚገኙት አቶ ዳዊት ዮሴፍ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

ገዥዉ ፓርት አማራና ቅማንትን ብሎም ጎንደርን በሁለት ለመክፈል ያቀደው የህዝብ ዉሳኔ እንጅ ሁለቱም ማህበረሰብ የባህልም ሆነ የቋንቋም እንዲሁም የሃይማኖት ልዩነት የላቸውም የሚሉት ደግሞ የጎንደር ህብረት ለኢትዮጵያ አንድነት የስራ አስፈፃም አባል አቶ አበበ ንጋቱ ናቸው። ገዥዉ ፓርት መራጮችን በማስፈራራትና ለመራጮች ገንዘብ በመስጠት ድምጽ እንዲሰጡ እያስገደደ ነው የሚሉትንም ትችቶች እንደሚጋሩም ይናገራሉ።

በፊታችን እሁድ ድምጽ አሰጣጡ ከ12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት እንደሚካሄድና እንደተጠናቀቀም ድምፅ ቆጠራ እንደሚጀምር ቦርዱ ያወጣዉ የጊዜ ሰሌዳ ያመለክታል። መስከረም 8 የህዝብ ዉሳኔዉ የድምጽ ቆጠራ በድምፅ መስጫ ጣቢያዎች  በይፋ እንደሚገለፅና የድምፅ ቆጠራ ዉጤት ተጠናቅሮ መስከረም 15 ለፌዴሬሼን ምክርቤት እንደሚላክም የጊዜ ሰሌዳዉ ያመለክታል።

መርጋ ዮናስ

ኂሩት መለሰ