1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«ቆሼ » መንደር ልጆች

ዓርብ፣ መጋቢት 8 2009

መጋቢት ሁለት ምሽት በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፣ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የደረሰውን አደጋ ለተመለከተ እና አካባቢውን ለማያውቅ ሰው ምን አይነት ሰዎች እዛ አካባቢ ይኖራሉ? ብሎ መጠየቁ አይቀርም። እዛ የሚኖሩ ወይም ተወልደው ያደጉ ወጣቶች አካባቢያቸውን እንዴት ይገልፁታል? ጠይቀናቸዋል።

https://p.dw.com/p/2ZMZV
Äthiopien Erdrutsch in einer Mülldeponie in Addis Abeba
ምስል DW/Y. G. Egziabher

የ«ቆሼ » መንደር ልጆች

ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በተለምዶ ቆሼ በሚባለው ስፍራ ለዓመታት የተከመረ የቆሻሻ ተራራ ሲደረመስ የዓለም የመገናኛ ብዙኃን ዜናውን ተቀባብለውታል። የተጎሳቆሉ ጎጆዎች፣ በሸራ እና ፕላስቲክ የተወጠሩ ድንኳኖች እና በአይን ባይታዩም መጥፎ ጠረንን የሚያመላክቱ ቆሻሻዎች በምስል ዘገባዎች ተካተዋል። በዚህ የቁሻሻ መጣያ ዙሪያ ደግሞ በፊትም አሁንም ሰዎች ይኖራሉ።  የ«ቆሼ » ሰፈር ልጆች። «ዝቅተኛ ማህበረሰብ የሚኖርበት አካባቢ ነው» ይላል ከልጅነቱ አንስቶ ቄሼ በሚባለው አካባቢ የሚኖረው ኤፍሬም ሰፈሩን ሲገልፅ። ፒያሳ አካባቢ የተወለደው ኤፍሬም ከ 20 ዓመት በፊት በህፃንነቱ ነው ከእናቱ ጋር ወደዚህ ስፍራ የመጣው። ሌላው ወጣት ዳንኤል ደግሞ ብዙም በማይርቀው መካኒሳ ነው ተወልዶ ያደገው። ቆሼ መኖር የጀመረበት ምክንያት የቤት ኪራይ ስለሚቀንስ ነው። ዳንኤል  ቆሼን ሰፈሬ ነው ካለ 10 ዓመት አለፈው። አማራጭ ስለሌለው ሌሎች ስለሰፈሩ የሚሉትን ተቀብሎ ይኖራል። 
በዚህ ሰፈር ተወልዳ ያደገችው አመል ወርቅ በሰሞኑ አደጋ የምታውቃቸው በርካታ ሰዎች ሞተዋል እንዲሁም ተጎድተዋል። «አሁን በሰፈራችን የሚታየውም የሚሰማውም ነገር ምንም የሚያስደስት አይደለም» ትላለች። እንኳን ሀዘን ተጨምሮበት በፊትም እዛ አካባቢ በመኖሯ ሰው ይንቃት ነበር። ስለሆነም ኤፍሬም እንደገለፀልን የአካባቢው ልጆች ሰፈራቸው የት እንደሆነ ለሌሎች ሰዎች መናገርም ይሁን ማሳየት አይፈልጉም። ግን እንደሰሞኑ ሊደበቁ የማይችሉ አጋጣሚዎች ይኖራሉ። አመል ወርቅ ከእነዚህ በጣት ከሚቆጠሩት ወጣቶች ትመደባለች። ሰፈሯን ከመናገር ወደ ኃላ አትልም። ሌሎች ሰፈሯን ሲያራክሱባትም አትወድም።
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የማህበራዊ ኑሮ ባለሙያ ( የሶሲዮሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር) የሆኑት ዶክተር የራስ ወርቅ አድማሴ ከአካባቢው ልጆች ላይ ጥናት ያደረገች አንዲት ተማሪያቸው ጥናትን ተመልክተዋል። የወጣቷ አማካሪ ሆነው በተመደቡበት ሰዓትም፤ ጥናቷ ከባድ እንደሚሆን ቢያምኑም የዛ ሰፈር ልጅ በመሆኗ ለጉዳዮ ቅርብ መሆኗን አሳምናቸው ጥናቷን እንዳካሄደች ገልፀውልናል። የመመረቂያዋ ፁሁፏ ውጤት ምን እንደነበርም ዛሬ ያስታውሳሉ። ለምን « የቆሼ ልጆች» እንደተባሉ። ሌላው ምንም እንኳን ወጣቶቹ የድህነት እጣ ፋንታቸውን ቢቀበሉም በሌላው ህብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ማጣታቸው ከፍተኛ ችግር ነበር።  ዶክተር የራስ ወርቅ እንደሚሉት የዚህ አካባቢ ሰዎች ችግር በራስ አለመተማመን ሳይሆን ድህነት ነው። ነዋሪዎቹ ብቻቸውን ሊፈቱት ያልቻሉትን  ችግሮች ባለፈው ቅዳሜ የደረሰው አደጋ የመንግሥት ትኩረትን ፈጥሮ የአካባቢያቸው የወደፊትን ገጽታ ይቀይር ይሆን? 
የ«ቆሼ » ልጆች የማህበረሰባዊ እና ስነ ልቦናዊ ችግሮችን የቃኘንበትን የወጣቶች ዓለም ዝግጅት በተጨማሪ በድምፅ ያገኙታል።
 ልደት አበበ
ኂሩት መለሰ 
 

Äthiopien Hauptstadt Addis Abeba
ዘመናዊዋ አዲስ አበባምስል DW/T. Haile
Äthiopien Erdrutsch in einer Mülldeponie in Addis Abeba
መጋቢት ሁለት ምሽት በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የደረሰው አደጋምስል DW/Y. G. Egziabher