1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበርበራ ወደብ እና ኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 5 2008

ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓጓዘው የእርዳታ እህል እና ማዳበሪያ ጭነት መብዛት በአገሪቱ የትራንስፖርት ዋጋ ንረት ፈጥሯል። የኢትዮጵያ መንግስት ጅቡቲ ወደብ ላይ የተፈጠረውን መጨናነቅ ለመቀነስ የበርበራ ወደብን ለመጠቀም ስምምነት ፈርሟል። ለመሆኑ የሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ ምን ያክል ለአጠቃቀም ምቹ ነው?

https://p.dw.com/p/1IUjy
Dschibuti Containerhafen und Rotes Meer
ምስል Getty Images/AFP/S. Maina

የበርበራ ወደብና ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም ከሚጠቀምበት የጅቡቲ ወደብ በተጨማሪ በሶማሌላንድ የበርበራ ወደብን ለመጠቀም ወስኗል። የኢትዮጵያ መርከቦች ድርጅት እና የበርበራ ወደብ አስተዳዳሪ ባለስልጣን በቢሾፍቱ ከተማ ስምምነት ከተፈራረሙ ጥቂት ቀናት በኋላ 25 ቶን የእርዳታ እህል የጫነች የአሜሪካን መርከብ በወደቡ ቆማለች።

በዓመት 12 ሚሊዮን ቶን ዕቃ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው ኢትዮጵያ ከጅቡቲ በተጨማሪ አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም ከወሰነች ቆይታለች። ረዳት ፕሮፌሰር መድህኔ ታደሰ የጸጥታ እና ደህንነት ተንታኝ ናቸው። ፕሮፌሰሩ የመጀመሪያው የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል። ረዳት ፕሮፌሰር መድህኔ ታደሰ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት አገሪቱ ከአሰብ እና የኤርትራ ወደቦች በተጨማሪ አማራጮች መፈለግ እንዳለባት ከሚወተውቱ ምሁራን መካከልም አንዱ ነበሩ።የሶማሌላንድ ፖለቲከኞች ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ለመመሥረት ፈቃደኛ እንደነበሩም ይናገራሉ።

ከኢትዮጵያ ድንበር እስከ በርበራ ድረስ የ241 ኪሎ ሜትር ርቀት አለው። መንገዱ እውቅና ያላገኘው የሶማሌላንድ መንግሥት ከአውሮጳ ኅብረት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተሠራ ነው። ከኤደን ባህረ-ሰላጤ ደቡባዊ ጫፍ ላይ የምትገኘው ሶማሌላንድ እንደ አገር ለመቆም የሚያስፈልጋትን ቅድመ-ሁኔታዎች ሁሉ ታሟላለች። የመገበያያ ገንዘብ፣ በተግባር የሚሠራ የቢሮክራሲ ስርዓት፤ የሰለጠነ ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አላት። መቀመጫውን ሐርጌሳ ላይ ያደረገው እና ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት የሚታትረው መንግሥት የሶማሌላንድን ድንበር ማስጠበቅ፤ ከሞቅዲሾ መንግሥት ጋር መደራደር ችሏል። ረዳት ፕሮፌሰር መድህኔ ታደሰ የሶማሌላንድ የሚሠራ የዴሞክራሲ ስርዓት የተሻለ ጸጥታ እና ደህንነት ያላት በመሆኑ ስጋት እንደማይኖርበት ይናገራሉ።

በዚህ ሳምንት የኢትዮጵያዎቹን ሸበሌ፤ አሶሳ፤ ጊቤ፤ መቀሌ እና ጋምቤላን ጨምሮ ከ20 በላይ መርከቦች በጅቡቲ ወደብ ቆመዋል። አብዛኞቹ የእርዳታ እህል የጫኑት መርከቦች የተጫኑትን ለማራገፍ ከአስር ሰዓታት እስከ 15 ቀናት በላይ እንደሚጠብቁ የጅቡቲ ወደብ አስተዳደር ድረ-ገጽ ይጠቁማል። የጅቡቲ ወደብ ላይ የተፈጠረው መጨናነቅ በኢትዮጵያ የገቢ ሸቀጦች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። ከጅቡቲ የሚጫኑ ሸቀጦች ወደ ኢትዮጵያ ለመድረስ የሚወስድባቸው ጊዜ ጨምሯል። የማጓጓዣ ዋጋውም ንሯል።

የጅቡቲ ወደብ ኮንቴነር የተጫኑ እና በብትን አሊያም ያለ ኮንቴነር የተጫኑ ዕቃዎች ማራገፊያ ሁለት አይነት የመርከብ መቆሚያዎች አሉት። በኮንቴነር የተጫኑ ዕቃዎች በዘመናዊ ማሽኖች የሚራገፉ በመሆኑ መጨናነቅ አልተፈጠረም። በድርቅ ለተጠቁ ወገኖች የተገዛው የእርዳታ እህል ጅቡቲ ድረስ በብትን ተጭኖ ከተጓጓዘ በኋላ የማሸግ ሥራው ይከናወናል። እንዲህ አይነት ሸቀጦች የጫኑ መርከቦች የሚቆሙባቸው የጅቡቲ ወደብ አገልግሎት መስጫዎች ጥቂት መሆናቸው ለመጨናነቁ አንዱ ምክንያት መሆኑን አቶ ኤርሚያስ ይናገራሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር መድህኔ ታደሰ ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን ለመጠቀም ይህን ያህል መዘግየት አልነበረባትም የሚል አቋም አላቸው። ይህን ወደብ መጠቀም ለኢትዮጵያ የገቢ እና የወጪ ንግድ የተሻለ አማራጭ መሆኑን የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር መድህኔ ታደሰ ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት አስዋጽዖው ከፍተኛ እንደሆነ ያምናሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከጅቡቲ ወደብ በተጨማሪ በርበራን እና የሱዳን ወደቦችን ካሁን ቀደሙ በተሻለ ለመጠቀም ማቀዱን አስታውቋል። በሁለተኛው የእድገት እና ለውጥ ዘመን ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ ከምታስገባቸው ምርቶች መካከል 30 በመቶውን በበርበራ፤ እንዲሁም 10 በመቶውን በሱዳን ወደቦች ለማድረግ ታቅዷል። ረዳት ፕሮፌሰር መድህኔ ታደሰ የጅቡቲ ወደብ እና የቀይ ባህር አካባቢ በልዕለ-ኃያላኑ እና የፋርስ ባህረ ሰላጤ አካባቢ አገራት የተለየ ትኩረት እየተሰጠው በመሆኑ ኢትዮጵያ አማራጭ ያስፈልጋታል ሲሉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ያቀደችውን ግልጋሎት ለማግኘት ግን የበርበራ ወደብ በሰው ኃይል አደረጃጀትም ይሁን በብቃት ያሉበትን ውስንነቶች መቅረፍ ይኖርበታል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ

Dschibuti Hafen
ምስል DW/J. Jeffrey
Dschibuti Hafen
ምስል DW/J. Jeffrey