1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበጀት ቀውስ ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 13 2003

የኤውሮ ምንዛሪ ዓባል ሃገራት መሪዎች በነገው የብራስልስ ጉባዔ ዋዜማ ለግሪክ የዕዳ ቀውስ መፍትሄ ለማፈላለግ እየጣሩ ነው።

https://p.dw.com/p/Rafw
ምስል picture alliance/ZB

ከሰሞኑ የኤውሮና የአውሮፓ የፊናንስ ገበዮች ውዥቀት በኋላ ለችግሩ መፍትሄ የማስፈኑ ግፊት ከቀን ወደ ቀን እየጠነከረ ሲመጣ ለግሪክ ምናልባትም በከፊል የዕዳ ምሕረት የማድረጉ ሃሣብ ተቀባይነት እያገኘ የሚሄድ ይመስላል። ከአትላንቲክ ባሻገር በዩ.ኤስ.አሜሪካም የበጀት ኪሣራውን ጣራ ከፍ ለማድረግ በተያዘው የመንግሥት ጥረት ከተቃዋሚዎቹ ሬፑብሊካኖች ጋር ጭብጥ ስምምነት አልተገኘም። መፍትሄው ተወደደም ተጠላ በፍጥነት መገንት የሚኖርበት ሲሆን የጀርመኑ የምጣኔ-ሐብት ምርምር ኢንስቲቲዩት ፕሬዚደንት ሃንስ-ቨርነር-ዚን እንዳሉት መጠኑ ይለያይ እንጂ ለአሜሪካም ሆነ ለግሪክ የችግሩ መንስዔ ከአቅም በላይ መኖሩ ነው።

በአሜሪካው የበጀት ውዝግብ የዕዳውን ጣራ አሁን ካለበት 14,3 ቢሊዮን ዳላር በጊዜው ከፍ ማድረግ ካልተቻለ አገሪቱ በጥቂት ሣምንት ውስጥ የመክፈል አቅም እንደምታጣ ነው የሚታመነው። ይህን ደግሞ በመሠረቱ ዴሞክራቶችም ሆኑ ሬፑብሊካኖች አይፈልጉትም። ስለዚህም በወቅቱ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የዕዳውን ጣራ በራሳቸው ከፍ የማድረግ መብት እንዲያገኙ በሚያደርግ አስታራቂ መፍትሄ ላይ ንግግር መያዙ ነው ከዋሺንግተን የሚነገረው። በሕጉ መሠረት ይህን ማድረግ የሚችለው ብሄራዊው ሽንጎ ነው።

በወቅቱ ትልቁ ችግር በተወካዮች ም/ቤት ውስጥ ብዙሃኑ ሬፑብሊካኖች ተቃውሟቸውን ማጠንከራቸው ነው። የዕዳውን ጣራ ከፍ ማድረጉ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ደጋግሞ እንደታየው ለነገሩ ብዙም አስቸጋሪ አልነበረም። ይህ የጀርመኑ የምጣኔ-ሐብት ምርምር ኢንስቲቲዩት ፕሬዚደንት ሃንስ-ቨርነር-ዚንም የሚያረጋግጡት ነው።

“እነዚህን መሰል ሁኔታዎች አሜሪካ ውስጥ ሁሌም የዕዳው ጣራ ተወስኖ የተቀመጠ በመሆኑ የተነሣ በየጊዜው ነበሩ። እንግዲህ አሁን ተቀናቃኞቹ ወገኖች ቢስማሙ እንኳ አንድ ቋሚ ገደብ ማስቀመጣቸው የማይቀር ነው። እናም ከዚህ ጣራ አንዴ እንደገና መደረሱና ድራማው አዲስ መጀመሩ የጊዜ ጉዳይ ይሆናል። ባለፉት ጊዜያት ሁሌም ስምምነት ማስፈን ተችሏል። አሁንም ይሄው ነው የሚሆነው”

በሌላ በኩል እርግጥ አሜሪካ የዕዳዋን ወለድ መልሳ መክፈል ባትችል ይህ መንግሥታዊ ኪሣራን ነው የሚያስከትለው። የዚህም ውጤት ምናልባትም ከሶሥት ዓመታት በፊት ተከስቶ ከነበረው የኤኮኖሚ ቀውስ ሊብስ እንደሚችል የፊናንስ አዋቂዎች ይናገራሉ። የዕዳ ጣራውን ከፍ በማድረግ የሚወሰድ የፖለቲካ ዕርምጃ በመሠረቱ ጊዜያዊ ችግርን ከማለዘብ አልፎ ዕዳውን በአንዲት ሣንቲም እንኳ ዝቅ የሚያድረግ አይሆንም። በዚህ በአውሮፓ በግሪክም ቢሆን ሃቁ የተለየ አይደለም። የአሜሪካ የዕዳ ቀውስ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ይሁን እንጂ ከግሪክ የሚዛመድበት ቢቀር አንድ ጭብጥ ሁኔታ አለ። ይሄውም ሃንስ-በርነር-ዚን እንደሚያስረዱት ሁለቱም ከአቅም በላይ የመኖራቸው ሃቅ ነው።

“አዎን፤ ትክክል ነው። ግን እንበል አሁን በዕዳ ግደባው ረገድ የሚታየው ድራማ የፖለቲካ መንስዔ ያለው ነው። በሌላ የዕዳ ደረጃም መልሶ ሊነሣ ይችላል። እርግጥ ሃቁ አሜሪካውያን ከባድ ዕዳ ላይ መውደቃቸው ነው። ዕዳው ባለፈው ዓመት መጨረሻ 94 በመቶ ሲደርስ ዘንድሮ እንዲያውም ከመቶ በመቶ በላይ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው። ግሪክ በዓመቱ መጨረሻ 150 ከመቶ ደረጃ ላይ የምትደርስ ሲሆን የርሷ ደግሞ ይብስ ከፍተኛ ነው። ግን አሜሪካ ግዙፍ የውጭ ዕዳዋ እንደሚያሳየው ለዓመታት ከአቅሟ በላይ ነው የኖረችው። አሜሪካውያን ቤት መሥራት እንዲችሉ ገንዘብ ለማቅረብ በያመቱ ከግብር ነጻ 800 ሚሊያርድ ዶላር የሚያወጡ የፊናንስ ሰነዶች ሲሸጡ ኖረዋል። ይህ ደግሞ ዕዳቸውን መልሰው መክፈል የማይችሉትን ጭምር የሚጠቀልል ነው”

አሜሪካውያን እንግዲህ ከዚህ ቤት ሰራሽ ችግር መውጣት እንዲችሉ ቁጠባ በጣሙን ነው አሰፈላጊ የሚሆነው። ሃንስ-ቨርነር-ዚን እንደሚሉት ከሆነ የግብር ጭማሮ ግድ ይሆናል ማለት ነው።

“አዎን፤ ግብር ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ግን ዴሞክራቶችና ሬፑብሊካኖች የሚወዛገቡት በዚሁ ጉዳይ ነው። ሬፑብሊካኑ ግብር ጭማሮ ከኛ ጋር የለም፤ መንግሥት ወጪውን መቀነሱ ነው መፍትሄው ባዮች ናቸው። እንግዲህ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተያዘው የክፍፍል ክርክር ነው። ቅራኔው በቀላሉ አይታረቅም። እንደሚታወቀው የኦባማ መንግሥት የጤና ጥበቃ ዋስትና ያሰፈነው በቅርብ ሲሆን ይህንኑ ደግሞ አሁን ለመቁረጥ እንደማይፈልግ ግልጽ ነው”

የግሪክን የዕዳ ችግር በተመለከተ አንዳንድ ጠበብት ዕዳው በመመለሱ ሃሣብ ላይ ብቻ ማተኮሩ ተገቢ እንዳልሆነ ያመለክታሉ። ታዲያ ለግሪክ በከፊልም ሆነ በሙሉ የዕዳ ምሕረት ማድረጉ አማራጭ እየሆነ መሄዱ አልቀረም። ሰሞኑን ይህን ሃሣብ የሚደግፉት ወገኖች ድምጽ እየጎላ ሲሄድ በጉዳዩ ግትር ሆኖ መቀጠሉ የሚቻል ነገር አይመስልም።

“አይቻልም!/ ግሪክ ካለፈው ዓመት ሚያዚያ 28 ወዲህ በክስረት ላይ ነው የምትገኘው። በዕለቱ የግሪክ የመንግሥት ዕዳ ወለድ ወደ 38 በመቶ ነበር ከፍ ያለው። ከዚያን ወዲህ የተደረገው በዓለም ሕብረተሰብ ገንዘብ የክስረቱን ሂደት ማጓተት ብቻ ነበር። የፊናንሱ ገበዮች ደግሞ ለግሪክ ገንዘብ ማቅረብ ከተዉ ቆይተዋል። እንዲያውም የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ገንዘብ ባያቀርብ ኖሮ ግሪክ ቀድማም በከሰረች ነበር። ከ 2008 ዓ.ም. ወዲህ ጠቅላላው ወደ አገር የሚገባው ምርትም የሚከፈለው በዕዳ ነው። የሌሎች አገሮች የግል አበዳሪዎችም ገንዘብ አያስገቡም። እና አገሪቱ ከአቅሟ በላይ ነው የምትኖረው። የግሪክ አጠቃላይ የኤኮኖሚ ፍጆታ ከሕዝቡ የገቢ አቅም ሲነጻጸር 17 በመቶ ከፍ ያለ ነው። ይህ እንግዲህ ዘለቄታ የሚኖረው ችግር እንጂ በአንዴ በሚወሰድ የፊናንስ ገበዮች ዕርምጃ የሚወገድ አይደለም። የፊናንስ ገበዮቹ ችግሩን ከማለዘብ ሊያልፉ አይችሉም”

እንደ ጀርመኗ ቻንስለር እንደ ወሮ/አንጌላ ሜርክል ከሆነ የዕዳ ምሕረቱ ጎጂ ተጽዕኖ ሊኖረው የሚችልም ነው።

“አሁን የሚጠቀሰው የዕዳ ምሕረት ጎጂ ገጽታም አለው። ችግሩ ያለባቸው አገሮች ቸልተኛ እንዲሆኑ ሊያደርግ ይችላል። እኔ በበኩሌ ይሄን ግቤ አላደርግም። አጥብቀን መጣር ያለብን ከዚህ የባሰ ነገር እንዳይከተል ለማድረግ ነው። የግሉን ዘርፍ ማካተታችን ራሱ የሚያሳየው ግሪክ ውስጥ እጅግ ከባድ ችግር እንዳለ መሆኑ መዘንጋት የለበትም”

ከወቅቱ ሁኔታ አንጻር የማይመስል ቢሆንም የኤውሮ ክልል አገሮች ግሪክን በማዳኑ በኩል መስማማታቸው ገና አስተማማኝ አይደለም። ባይሆንስ፤ ሃንስ-ቨርነር-ዚን እንደሚሉት ግሪክ የከፋው ከመጣ ምናልባትም የውርቅ ተቀማጯን በመሸጥ ዕዳዋን ለመቀነስ አንድ አማራጭ ልትጠቀምበት ትችል ይሆናል።

“አዎን፤ በእርግጥ ትችላለች። የወርቅ ተቀማጭ አላት። ብዙ መሬትም አላት። ለዚህም ነው በዚህ መንገድ ገንዘብ ለማግኘት ለግሪክ አንድ ባላደራ ተቋም እንዲመሰረት የተጠየቀው። ግን ነገሩ ቀላልም አይደለም። መሬቱን ሁሉ በአንዴ መሸጥ አይቻልም። ከሆነ ዋጋው በጣም ነው የሚያቆለቁለው። እርግጥ በመያዣነት መጠቀም ይቻላል። በአጠቃላይ እንግዲህ ግሪክ ዕዳዋን በራሷ ለመወጣት ገና የመፍትሄ አማራጭ አላት። ግን መጀመሪያ የዓለም ሕብረተሰብ የሚያቀርበውን የፈውስ ዕቅድ መጠበቁ ነው የሚመረጠው”

ለማንኛውም የኤውሮ ዞን ሃገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሰሞኑን ዛሬም በብራስልስ ለሐሙሱ ጉባዔ የስምምነት ሃሣብ ለማስፈን ያልተቋረጠ ንግግር በማድረግ ላይ ናቸው። ለግሪክ የሚቀርበውን ሁለተኛ የዕርዳታ ፓኬት በመቋጠሩ ረገድ የግሉን ዘርፍም ለማሳተፍ ለሣምንታት ከተካሄደ ትግል በኋላም በምንዛሪው ክልል ባንኮች ላይ ግዴታ ለመጣል አሁን ከሃሣብ መቀራረብ ተደርሷል። እንደ ጀርመኗ ቻንስለር እን ወሮ/አንጌላ ሜርክል ከሆነ ደግሞ ችግሩን ለመቋቋምና ኤውሮንም በጋራ ምንዛሪነት ሕያው አድርጎ ለማቆየት የዓባል ሃገራቱን የፉክክር ብቃት ማጠናከር ግድ ነው። የጋራ ምንዛሪው ዕርጋታም መጠበቅ’ አለበት።

“ከሁሉም በላይ ኤውሮ እንደምንዛሪ ተረጋግቶ እንዲቀጥል ለማድረግ እንጥራለን። ለነገሩ ኤውሮ እንደምንዛሪ ቀውስ ላይ አልወደቀም። ችግሩ በአንዳንድ አገሮች የዕዳ ቀውስ መኖሩ ነው። በመካከላችን በፉክክር ብቃት፤ እንበል በያንዳንዱ አገር በኤኮኖሚ ቀደምት የመሆን አቅም ረገድ ብዙ ልዩነት አለ። ይህ ደግሞ ዕዳን በመቀነስና የፉክክር ብቃትን በማጠናከር ሊሻሻል ይገባል። እነዚህ ሁለት መሟላት ያለባቸው ነገሮች ሲሆኑ በተቀረ ጀርመን ኤውሮን ትፈልገዋለች”

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ