1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡሩንዲው ሸምጋይ መሰናበታቸው

ዓርብ፣ ሰኔ 5 2007

ለቡሩንዲ ውዝግብ መፍትኄ ፍለጋ ፣ በሥልጣን ያለውን መንግሥትና ተቃዋሚዎችን እንዲሁም የሲቭሉን ማሕበረሰብ ተወካዮች ለማደራደር ይደረግ የነበረው ጥረት ተቋረጠ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፣ ለታላላቆቹ ኃይቆች አካባቢ በሸምጋይነት የመደባቸው አልጀሪያዊው ዲፕሎማት ሰዒድ ጅኒት፤ በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት ነው የሚያደሉት ተብለው ተወቅሰዋል።

https://p.dw.com/p/1FgPy
Burundi Proteste gegen Präsident Nkurunziza
ምስል Reuters/G. Tomasevic

[No title]

ለቡሩንዲ ውዝግብ መፍትኄ ፍለጋ ፣ በሥልጣን ያለውን መንግሥትና የተቃውሞውን ወገኞች፣ እንዲሁም የሲቭሉን ማሕበረሰብ ተወካዮች ለማደራደር ይደረግ የነበረው ጥረት ተቋረጠ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፣ ለታላላቆቹ ኃይቆች አካባቢ ሸምጋይ ይሆኑ ዘንድ የመደባቸው ልዩ ልዑክ ፣ አልጀሪያዊው ዲፕሎማት ሰዒድ ጅኒት፤ በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት ነው የሚያደሉት ተብለው ተወቅሰዋል። 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች ባገሪቱ ፍጹም ነጻና ፍትሓዊ ምርጫ ሊካሄድ እንደማይችል በመገምገም በትናንትናው ዕለት፣ ላለመሳተፍ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል።የቡሩንዲው ፕሬዚዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ፣ ለ 3ኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ቆርጠው መ ነሣታቸውን ካስታወቁበት ጊዜ አንስቶ በተለይም ከሚያዝያ 18,2007 ወዲህ ከሞላ ጎደል በየዕለቱ ነው በአንዳንድ የመዲናይቱ መዳረሻዎች ተቃዋሚዎች ሰልፍ ሲያሳዩ የቆዩት። በፖሊስ የኅይል ርምጃም 40 ያህል ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 100,000 ያህል የዚያች ንዑስ ሀገር ተወላጆች ወደ ጎረቤት ሃገራት መሰደድ ግድ ሆኖባቸዋል። በመሆኑም ፤ ከነገ በስቲያ የአፍሪቃ ሕብረት መሪዎች በጆሐንስበርግ በሚያካሂዱት ውይይት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለተባባሰው ፍልሰት ፣ አፍሪቃውያን ፤ በአፍሪቃውያን ላይ ጥላቻና ርኩስ ቅናት አድሮባቸው የፈጸሙትን በደል እንዲሁም የቡሩንዲን አሳሳቢ ሁኔታ አጀንዳ አስይዘው እንደሚመክሩባቸው ለመገንዘብ ተችሏል። የቡሩንዲ መንግሥት ፣ የአጎራባች ሃገራትን ምክርና ተግሣጽ ችላ ብሎ የወሰደው ርምጃም ሆነ ያሳለፈው ውሳኔ አገሪቱን እጅግ እንዳመሳት ነው።
የቡሩንዲ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ Innocent Muhozi እንዲህ ይላሉ።
«ይህ ውሳኔ ለሁላችን ትልቅ ችግር እንደሚያስከትል የሚያስረዳ መልእክት ነው ያለው።የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ከ ሁለት ሳምንት በፊት በዳሬሰላም ጉባዔ ያደረጉትን እናስታውሳለን። የቡሩንዲ መንግሥት ፣ የምርጫውን ጊዜ ወደፊት እንዲገፋው ጠይቀው ነበር ይህም ከ45 ቀናት እንዳያንስ ነበረ ያሳሰቡት ። መንግሥት ያኔ በውሳኔው ደስተኛ እንደነበረ ቢገልጽም አሁን ግን የምሥራቅ አፍሪቃ ማሕበረሰብ እንዲሁም የደቡባዊው አፍሪቃ የልማት ማሕበረሰብ ከጠየቁት ፍጹም የተለየ ነገር ማድረጉን ነው የታዘብነው።»
የተባበሩት መንግሥታት በሽምግልና ያሠማራቸው ሰዒድ ጅኒት ፣ ለቡሩንዲ መንግሥት ያደላሉ ተብለው በተቃውሞው ወገን ቢወቀሱም፤ ፈጽሞ አንደማይቀበሉት ነው እርሳቸው የገለጡት። እርግጥ የሽምግልናውን ተግባር አቋርጠዋል። የተባበሩት መንግሥታት ተተኪ ልዑክ እንዳልሠየመም በቡሩንዲ የተባበሩት መንግሥታት ሚሲዮን ቃል አቀባይ ቭላዲሚር ሞንቴሮ አስታውቀዋል።
የቡሩንዲ የተቃውሞ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ፣ ሕገ መንግሥቱን መጣስ ብቻ ሳይሆን በጎሣ ዎች መቀናቀን ሳቢያ ከእርስ በርስ ጦርነት አዘቅት ውስጥ ገብታ የነበረችው ሀገር፣ እ ጎ አ በ 2005 ፤ ሰላም ለመመሥረት የበቃችበትን ውል ፤ ለ 3ኛ ጊዜ ካልተመረጥሁ በማለት መቅኖ ሊያሳጡት ነው በማለት አጥብቀው ይቃወሟቸዋል።
ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ፣ የምርጫ ኮሚሽኑን አመሠራረትና አሠራር የሚመለከውን ሥርዓትና ደንብ ሁሉም መጣሳቸውን የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ Innocent Muhozi ይገልጻሉ።
«ሕጉ እንደሚለው፣ የምርጫ ኮሚሽኑ ሕልውና የለውም። ዛሬ ከፈለጉ ያሻቸውን ውሳኔ ማሳለፍ ይችላሉ። መጀመሪያ አባላቱ 5 ነበሩ። ውሳኔ ማሳለፍ የሚችሉ አምስቱ ወይም ዐራቱ ነበሩ ። አሁን ግን ሦስት ብቻ ናቸው የቀሩት። ስለዚህ ይህ ኮሚሽን ተግባሩን ለማካሄድ ፍጹም ብቁ አይደለም። የምርጫው ኮሚሽን ከአንግዲህ ሕልውና የለውም። ሕጉን ከተመለከቱ ይህን ነው የሚያስረዳ።»
በቡሩንዲ ሰኔ 22 ቀን 2007 የፓርላማ ምርጫ ፤ ሐምሌ 8 ደግሞ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ነው የንኩሩንዚዛ መንግሥት የደነገገው።

Burundi Sicherheitsmaßnahmen
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay
Burundi Proteste gegen Präsident Nkurunziza
ምስል Reuters/G. Tomasevic

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሀመድ