1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡሩንዲ ቀውስ እና የፈረንሳይ ሚና

ቅዳሜ፣ ግንቦት 22 2007

ፈረንሳይ ከቡሩንዲ የፀጥታ ኃይላት ጋ የምታደርገውን ትብብር ማቋረጧን አስታወቀች፣ የፈረንሳይ ዜና ወኪል «አ ኤፍ ፔ» በቡሩንዲ መዲና ቡጁምቡራ የሚገኙ ዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የፈረንሳይ

https://p.dw.com/p/1FZDu
Burundi Bujumbura Proteste gegen Präsident Nkurunziza Demonstration Polizei Tränengas
ምስል Reuters/G. Tomasevic

[No title]

መንግሥት ይህን ውሳኔ የወሰደው የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን በዕጩ ተወዳዳሪነት መቅረባቸውን በመቃወም በሀገሪቱ በቀጠለው አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የሀገሪቱ ፖሊስ ግዙፍ የኃይል ርምጃ በመጠቀሙ ምክንያት ነው።

ከኔዘርላንድስ፣ ከቤልጅየም እና ከጀርመን ጎን ከምሥራቅ አፍሪቃ ውጭ በሚካሄዱ የሰላም ማስከበሪያ ተልዕኮዎች ውስጥ በመጠናከር ተሳታፊ የሆኑትን የቡሩንዲን ፖሊሶችን እና ወታደሮች ከብዙ ዓመታት ወዲህ የምታሠለጥነው ፈረንሳይ ይህን ውሳኔ መውሰዷን ያካባቢውን ሁኔታ የሚከታተሉ በሀምበርግ የሚገኘውን በምህፃሩ «ጊጋ» በመባል የሚታወቀው የጀርመን የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ዩሊያ ግራውቮግልን የመሳሰሉ ታዛቢዎች መልካም ቢሉትም ርምጃው ዘግይቷል በሚል ተችተዋል።

Burundi Militärputsch
ምስል Reuters/G. Tomasevic

« ባንድ በኩል ለብዙ ዓመታት ያሠለጠነችው ፖሊስ አሁን በተቃዋሚዎች ላይ ከባድ የኃይል ርምጃ መውሰድ መጀመሩን ፈረንሳይ ቀስ በቀስ የተረዳች ሲሆን፣ ተደጋጋሚ የመፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባትን እና ፖሊስም የፈላጭ ቆራጭ መንግሥት መሳሪያ ሆኖ ያገለገለባትን ሀገር ፖሊስ እና የጦር ኃይል ማጠናከሩን ጥቅሙ ምን ይሆናል በሚል ማጠያየቅ ይገባታል። »

Burundi Proteste
ምስል Reuters/G. Tomasevic

ባለፉት ሳምንታት በዋና ከተማይቱ በቡጁምቡራ በተካሄዱት ተቃውሞ ሰልፎች ላይ በፖሊስ ኃላፊ አንድሬ ንዳያማባዤ የተመራው የፖሊስ ቡድን ተቃውሞውን በኃይል ተግባር መበተኑ የሚታወስ ሲሆን፣ በመገናኛ ብዙኃን ዘገባ መሠረት፣ በዚሁ ወቅት ፈረንሳውያን የፀጥታ አማካሪዎች ከፖሊሱ ኃላፊ ጎን ቆመው ነበር። ቡሩንዲ ውስጥ ፈረንሳይ እንደ ቀድሞ ቅኝ ገዢ ቤልጅየም ትልቅ ሚና ባይኖራትም፣ አንዳንድ አጠራጣሪ ርምጃዎች መውሰዷን ግራውፎግል ገልጸዋል። በሀገሪቱ ከተካሄዱ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በቡጁምቡራ የሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ለፖለቲካ ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ከለላ መስጠቱን ግራውፎግል እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል። ለውዝግቦች የመፍትሔ ሀሳብ የሚጠቁመው የ« ዓለም አቀፉ ክራይስስ ግሩፕ» ተንታኝ ቲየሪ ቨርኩሎም የፈረንሳይ በቡሩንዲ በታየው ክስተት አኳያ ርምጃ ለመውሰድ ያመነታችበትን ድርጊት ወቅሰዋል።

« ፈረንሳይ ትብብሯን ያቋረጠችው በጣም ዘግይታ ነው። ለምን ይህን ማድረጓ በውል ባላውቅም፣ ከጠቅላላ አውሮጳውያት ሀገራት መካከል ስለ ቡሩንዲ ስለቀጠለው ቀውስ ለረጅም ጊዜ ድምፅዋን ሳታሰማ የቆየች ሀገር ናት። ይሁንና፣ ይህን አቋም ለብዙ ጊዜ ይዛ ለመቀጠል አልቻለችም። ምክንያያቱም ይህ አቋሟ ከአውሮጳ ህብረት ጋ ያላትን ትብብር ሊጎዳ ይችላልና። »

ቀውሱን ምክንያት በማድረግ ቀደም ሲል የአፍሪቃ ህብረት እና የአውሮጳ ህብረት ቡሩንዲ ምርጫውን ወደ ሌላ ጊዜ እንድታስተላልፍ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ቡሩንዲ ምክር ቤታዊውን ምርጫ በአስር ቀን ወደፊት በመግፋት እአአ ለሰኔ አምስት አስተላልፋዋለች፣ ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ግን እንደበፊቱ እንደታቀደው እአአa ሰኔ 26 ይካሄዳል። የአውሮጳ ህብረት የማስፈራራት ድባብ በሚታይበት ሁኔታው አመቺ ባለመሆኑ የታዛቢ ቡድን እንደማይልክ አስታወቋል። ዩኤስ አሜሪካም ቀውሱ ካላበቃ ጠንካራ ርምጃ ልትወስደ እንደምትችል አስጠንቅቃለች።

ቴሬዛ ክሪኒንገር/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ