1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡሩንዲ የፖለቲካ ውጥንቅጥ

Eshete Bekeleሰኞ፣ ጥቅምት 29 2008

ከምስራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል አገራት አንዷ በሆነችው ቡሩንዲ መንግስት የጦር መሳሪያ አሰሳ እያካሄደ ነው። በአገሪቱ በተቃዋሚዎችና በፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ጅምላ ፍጅት እንዳያመራ አስግቷል።

https://p.dw.com/p/1H2U0
Burundi Polizei Sicherheitskräfte Militär Symbolbild
ምስል picture-alliance/AA/N. Renovat

የቡሩንዲ የፖለቲካ ውጥንቅጥ

የቡሩንዲው ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ «ህገ-ወጥ» ያሏቸውን የጦር መሳሪያዎች ዜጎች እንዲያስረክቡ ያስቀመጡት ቀነ-ገደብ በዕለተ ቅዳሜ ተጠናቆ የቤት ለቤት አሰሳ በአገሪቱ ፖሊስ ተጀምሯል። የፕሬዝዳቱ ተቃዋሚዎች ጠንካራ ይዞታዎች በተባሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ሁለት ሰዎች በዋና ከተማዋ ቡጁምቡራ መገደላቸው ተሰምቷል። የጦር መሳሪያ ፍለጋው በተለይ በዋና ከተማዋ ሙታኩራ የተሰኘ አካባቢ ላይ አተኩሯል።

ፕሬዝዳንቱ «ወንጀለኞች» ያሏቸው የጦር መሳሪያ ባለቤቶች «የአገሪቱ ጠላቶች» ተብለው ተፈርጀዋል። የቤት ለቤት አሰሳው በመቶ የሚቆጠሩ የፖሊስ ሰራዊት አባላትና ወታደሮችን ያካተተ ነው። ግጭት ያስመረራቸው የቡሩንዲ ዜጎች በበኩላቸው የመኖሪያ ቀያቸውን ጥለው መሸሸጊያ ፍለጋ ስደትን መርጠዋል። በእለተ ቅዳሜ ምሽት በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት 9 ሰዎች ተገድለዋል። ወደ መጠጥ ቤት ጎራ ያለው የጥቃቱ ፈጻሚ ዒላማዎቹ ከመሬት እንዲተኙ ካስገደደ በኋላ ግድያውን መፈጸሙን የአይን እማኞች ለአዣንስ ፍራን ፕሬስ ተናግረዋል። የቡጁምቡራ ከንቲባ ፍሬዲ ምቦኒምፓ የገዳዩን ማንነት ለማጣራት ምርመራ መጀመሩን አስታውቀዋል።ከንቲባው የጦር መሳሪያ አሰሳውም ቢሆን «ሙያዊ» በሆነ መንገድ እየተካሄደ እንደሆነ ተናግረዋል።

የቡሩንዲው ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ የአሰሳ ትዕዛዙን ያስተላለፉት ባለፈው ሰኞ በፖሊስና ታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ስምንት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው። አገሪቱ የገጠማትን ቀውስ ለመፍታት የሄደችበት መንገድ ግን ወደ ባሰ ማጥ እንዳይከታት የቀጣናውን አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት አስግቷል። ምክንያቱ ደግሞ የቡሩንዲ መንግስት ከተቃዋሚዎቹ ጋር የገባበትን ፍጥጫ ለመፍታት ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛም ያለ ህዝባቸው ፈቃድ በስልጣን ለመቆየት የመረጡት መንገድ ነው። ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች አሁን ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ የመረጡት የጦር መሳሪያን በጉልበት የመሰብሰብ ሂደት አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ለሚለውና ለወራት ለዘለቀው ግጭት ማቀጣጠያ እንዳይሆን ስጋት አላቸው። ለመሆኑ ትጥቅ የሚፈታው ማን ነው?

Tansania Flüchtlinge aus Burundi
ምስል DW/P. Kwigize

ቡጁምቡራ ማንነታቸው የማይታወቅ ታጣቂዎች የሚገኙባት ከተማ እንደሆነች ይነገራል። የታጣቂዎቹና የፖሊስ ተደጋጋሚ የምሽት ግጭቶች የተለመዱ ቢሆኑም የከተማዋ ነዋሪዎች ሁልጊዜም ስጋትና ፍርሐት እንደተጫናቸው ነው። መንግስት «ከተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት አላቸው።» ሲል የሚከሳቸውን ታጣቂዎች የጦር መሳሪያ እንዲያስረክቡ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ለከተማዋ መረጋጋት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን የቡሩንዲን ፖለቲካ የሚከታተሉ ተንታኞች ይስማማሉ። በጥንቃቄ ካልተደረገ ግን ወደ ባሰ ምስቅልቅልና ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል ይናገራሉ። ታጣቂዎቹ ይገኙባቸዋል በሚባሉት እንደ ሙታኩራ አይነት የመኖሪያ መንደሮች በኃይል የሚሞከር ዘመቻ በሲቪል ዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት ከማስከተል አልፎ በበርካቶች ዘንድ ቅሬታ ሊፈጥር ይችላል የሚል አስተያየትም ይደመጣል።

የፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ የዴሞክራሲ ተከላካይ ብሄራዊ ካውንስል ፓርቲ (National Council for the Defense of Democracy) የራሱ ታጣቂዎች አሉት። እድሜያቸው ከ35 አመት በታች የሚገኙ ወጣቶችን በአባልነት ያቀፈው ‘ኢምቦኔየኩሬ’ የፓርቲው የወጣቶች ክንፍ ሲሆን በቡጁምቡራ ግድያዎችና አፈናዎች ይፈጽማል እየተባለ ይታማል። የፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚዎች ታጣቂ ቡድኑ የፖሊስና የአገሪቱ ጦር የደንብ ልብሶችን በመልበስ ጥቃት ይፈጽማል ሲሉ ይከሱታል። የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪው ሪቻርድ ንዞ ሙንጌ አሁን የሚካሄደው የትጥቅ ማስፈታት ዘመቻ ኢምቦኔየኩሬ ታጣቂ ቡድንን እንደሚጨምር ተስፋ አድርገዋል።

«የጦር መሳሪያ ያነገተው ኢምቦኔየኩሬ ታጣቂ ቡድን የፖሊስና የአገሪቱ ጦር የደንብ ልብሶችን በመልበስ ህዝቡን እያሸበረ ይገኛል። ይህን በሚገባ እናውቃለን። እና የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን እንደሚፈቱ ተስፋ እናደርጋለን። በአንጻሩ የተለያዩ ተቃዋሚዎች አሉባቸው በሚባሉ ሰፈሮች ሰዉን እንዲያስፈራሩ ሽብር እንዲነዙ ፈቃድ አግኝተዋል ብለን እናምናለን። የፖሊስና ወታደሩን መለዮ ለብሰው የሽብር ተግባራቸውን መቀጠላቸው አይቀርም። ይህን እናውቃለን።»

የቡሩንዲ መንግስት ባለስለስልጣናት በአሰሳው ጅማሮ ያደረጓቸው ንግግሮች የዘር ግጭት እንዳይፈጥር አስግቷል። ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ተቃዋሚዎቻቸውን «የአገር ጠላቶች» እና «ሽብርተኞች» እያሉ ሲጠሯቸው ተደምጠዋል። የቡሩንዲ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሬቬርየን ንዲኩርዮ «ዛሬ ፖሊስ በጥይት እግር ይመታል።» አሉ ባለፈው ሳምንት። ቀጠሉ ሰውየው «ነገር ግን ቀኑ ሲደርስ ፖሊሶች እያለቀሱ መምጣታቸውን እንዲያቆሙ፤ ስራችሁን ስሩ ስንል እንነግራቸዋለን።» ሲሉ ተደመጡ። «ስራ ስሩ» የሚለው ቃል በጎርጎሮሳዊው የ1994 ዓ.ም. የሩዋንዳ ፍጅት ሑቱዎች በቱትሲዎች ላይ ግድያ እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ የሚያስተላልፉበት ነበር። የሹማምንቱ ንግግሮች እንደ አለም አቀፉ የቀውስ ተመልካች ቡድን ያሉ ተቋማትን አስግቷል። በዓለም አቀፉ ቀውስ ተመልካች ቡድን የአፍሪቃ ክፍል ሐላፊ ኮንፈርት ኤሮ የፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ አቋም ለአገሪቱ ስጋት ነው ባይ ናቸው።

nach Putschversuch - Präsident Pierre Nkurunziza zurück im Amt
ምስል Reuters/G. Tomasevic

«በ1990ዎቹ ይባል ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነገር እያየን በመሆኑ አደገኛ ነው ብዬ አስባለሁ። ወደ ንግግር ለመምጣት ፈቃደኛ አይደሉም። የሌላ ወገን ሃሳብ ለመስማት ፈቃደኛም አይደሉም። ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በአገራቸውም ይሁን ከአገራቸው ውጪ የሚሰሙ የለውጥ ድምጾችን ለማድመጥ ዝግጁ አይደሉም።»

አሰሳውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የቡሩንዲ ፖሊስና ጦር አገኘሁ ያለውን የጦር መሳሪያ ለእይታ አቅርቧል። የጦር መሳሪያ አሰሳው ከመጀመሩ ቀደም ብሎ በተቀሰቀሰው ግጭት እዚህም እዛም ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከእነዚህ መካከል የፕሬዝዳንቱ ተቺ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፒየር ክላቨር ምቦኒምፓ ልጅ የሆነው ዊሊ ንዚቶንዳ መገደሉን የሲቪል ተቋማት አስታውቀዋል። ንዚቶንዳ ራሱ በእስር ላይ ለሚገኙ ሰዎች ላይ የሚሰራ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማህበር ሰራተኛ ነበር።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የሆኑት ሳማንታ ፓወር የቡሩንዲ መንግስት ውሳኔዎችን አጥብቀው ተችተዋል። አምባሳደሯ የጦር መሳሪያ አሰሳውም ቢሆን በመላ አገሪቱ ግጭት እንዳይቀሰቅስ ስጋት እንዳላቸው አስታውቀው ነበር። የቡሩንዲ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ሪቻርድ ንዞ ሙንጌ ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ተቃውሞና ግጭቱን እያባባሱት ነው ሲሉ ይከሳሉ።

«የጦር መሳሪያ ማስረከቡ ገደብ ካለፈ በኋላ መንግስት ተቃዋሚዎችን ማጥፋቱን ይቀጥላል። ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ውዝግቡን በማብረድ ፈንታ በህዝቡ ዘንድ ፍርሐት እንዲስፋፋ ነው ያደረጉት። ተቃዋሚዎች በሚኖሩባቸው ሰፈሮች ሁሉ ፍርሃት መስፋፋቱን ብቻ ነው ልናገር የምችለው።»

ቡሩንዲን ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ለመምራት ፒየር ንኩሩንዚዛ መወሰናቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው አለመረጋጋት ያሳሰበው ግን የቀጣናውን አገራት ጭምር ነው። የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ «ሰዎች በየቀኑ እየተገደሉ ሬሳቸው በየጎዳናው እየተጣለ ነው። የአገሪቱ መሪዎች ሰዎችን በመግደል ጊዜያቸውን እያጠፉ ነው።» ሲሉ የንኩሩንዚዛን መንግስት ተችተዋል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ቃል-አቀባይ ማኖህ ኢስፒሱ በበኩላቸው በቡሩንዲ የተቀሰቀሰው ቀውስ የሚያሰጋው የምስራቅ አፍሪቃን በሙሉ እንደሆነ ተናግረዋል። ቃል አቀባዩ የቡሩንዲው አለመረጋጋትና ግጭት ለቀጣናው ኢኮኖሚ ከፍተኛ ስጋት መሆኑን ጠቁመው የፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛን ንግግርና እርምጃ ተችተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቡሩንዲ የተገደሉ ሰዎች በቅርብ ርቀት በተተኮሰ ጥይት መሆኑን አሊያም ከመሞታቸው በፊት በግርፋትና እንግልት ውስጥ ማለፋቸውን የሚያሳይ ምልክት በሰውነታቸው ላይ መኖሩን ባወጣው ዘገባ አትቷል።በዓለም አቀፉ ቀውስ ተመልካች ቡድን የአፍሪቃ ክፍል ሐላፊ ኮንፈርት ኤሮ አሁን በብሩንዲ እየተፈጸመ ከሚገኘው ግድያና ከሚታየው አለመረጋጋት ይበልጥ የወደፊቱ ያሰጋቸው ይመስላል።

«የአሁኑ መንግስት ከዚህ በላይ በመላ አገሪቱ የመሳሪያ አሰሳ ሊጀምር እንደሚችል ምልክት ነው። ሌላው ደግሞ ተቃዋሚዎች በመንግስት ላይ ጥቃት ሊጀምሩ ይችላሉ። ወይም አንዱ ማህበረሰብ ከሌላው ማህበረሰብ ከዚህ በባሰ ሁኔታ በመላ አገሪቱ ሊጋጭ ይችላል።»

ይህን ማንም አይፈልገውም። እንደ ፖለቲካ ተንታኞች እምነትም ይሁን እንደ ቀጣናው መሪዎች አስተያየት ንኩሩንዚዛ አገራቸው እየገባችበት ያለውን ማጥ ማየት ተስኗቸዋል። ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ «የት እንዳለ የሚያውቅ ማንም የለም። ማንም ሊያናግረው አይችልም። እንዴት ነው ህዝቡን በመምራት ላይ የሚገኘው?» ሲሉ የንኩሩንዚዛን አመራር ተችተዋል። የዓለም አቀፉ ቀውስ ተመልካች ቡድን የማዕከላዊ አፍሪቃ ፕሮጀክት ኃላፊ ቴሪ ቬርኮሎን በበኩላቸው «በስልጣን ላይ የሚገኙት ሰዎች ጽንፈኞች ሲሆኑ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ጽንፈኛ አቋም ይዘዋል።» ሲሉ በምሬት ተናግረዋል። ፖለቲከኞቹን «ማድመጥ አይፈልጉም» ሲሉም ተችተዋቸዋል።

Burundi Soldaten Sicherheitskräfte Militär
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kuroawa

የቡሩንዲ መንግስት በበኩሉ በአገሪቱ የከፋ ደም መፋሰስ ሊከሰት ይችላል የሚለውን ዓለም አቀፍ ስጋት ያጣጥላል። የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ዊሊ ኒያሚትዌ በብሩንዲ «ጦርነትም ሆነ የጅምላ ጭፍጨፋ አይኖርም።» ሲሉ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ነግረዋል። የመንግስታቸውን የጦር መሳሪያ አሰሳ ዘመቻ በሶማሊያ በአሸባብ ላይ ከሚደረገው የጸረ-ሽብርተኝነት ዘመቻ ጋርም አመሳስለውታል።

የአገሪቱን መንግስት ከተቃዋሚዎች ጋር ለማስታረቅ የሚደረገው ሙከራ ፍሬ አላፈራም። የእርቁን ሂደት በቅርብ የሚከታተሉት የዩጋንዳው የፖለቲካ ተንታኝ አሊ ሙታሳ ለመዘግየቱ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ይናገራሉ።
«የመሸምገሉ ሂደት አልተቋረጠም። ይሁንና ታንዛኒያ ምርጫ ላይ ስለነበረች ስለ ቡሩንዲው ሁከት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባ ነበር። ዋና አደራዳሪው ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና ምክትላቸውም ለዳግም ምርጫ ዝግጅት ላይ ናቸው። በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የተጨናነቀው የአደራዳሪዎቹ የጊዜ ሰሌዳ የውይይቱን ሂደት አጓቶታል።»

የቡሩንዲ አለመረጋጋትና ቡጁምቡራን ያመሰው ቀውስ ወደ ዘር ግጭት እንዳያመራ ስጋት ቢኖርም ዋንኛ ምክንያቱ ግን ፖለቲካዊ መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ። ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛና ፓርቲያቸው ተቺም ሆነ ተፎካካሪ አይፈልጉም። ሪቻርድ ንዞ ሙንጌ «ስልጣን ላይ ያለው መንግስት (MSD) ከተቋቋመ አንስቶ ስብሰባ እንዳናካሂድ አባሎቻችንን ከማሰር፤ከመከታተል፤ለስደት ከመዳረግ ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም። የፕሬዝዳንቱን 3ኛ ዘመነ ስልጣን የተቃወመ የመጀመሪያ የኛ ቡድን ነው። በዚህ የተነሳ በተለያዩ ቦታዎች ለሚታዩ ሁከትና ግጭት ተቃዋሚዎችን ተጠያቂ እያደረገ ነው።» ሲሉ የፒየር ንኩሩንዚዛ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለተቃዋሚዎች መዝጋቱን ይናገራሉ።

ሁኔታው ያሳሰበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት ዛሬ በኒውዮርክ ሊመክር እቅድ ይዟል። አለም አቀፉ ተቋም የምስራቅ አፍሪቃ ቀጣናን ስጋት ውስጥ ለጣለው የብሩንዲ ቀውስ አፋጣኝ መፍትሄ ለማግኘቱ ግን ማረጋገጫ የለም።አመፁ ከጀመረበት ሚያዚያ ወር አንስቶ ከ 210,000 በላይ ሰዎች ተጠናክሮ የቀጠለውን ዓመፅ ሽሽት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ከ200 በላይ ደግሞ ተገድለዋል። የሟቾቹ አስከሬን ከመንገድ ዳር በሚገኙ የውሃ መፍሰሻዎች ውስጥ በየቀኑ ተጥሎ መገኘቱ የአገሪቱን ዜጎች ሰቀቀን ውስጥ ከቶ ይኸው ብሩንዲ ለአዲስ ትርምስ ዳር ዳር እያለች ትመስላለች።
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ