1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡና መለያ ኮድ ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 26 2008

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አገሪቱ ወደ ውጪ በምትልከው ቡና ላይ ለደንበኞች መረጃ ማቀበል የሚችል መለያ ኮድ(bar code) መጠቀም ጀምሯል። ለደንበኛ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን የሚይዘው ባርኮድ ለጊዜው በቡና ይጀመር እንጂ በሌሎች ምርቶች ላይም የሚተገበር ይሆናል።

https://p.dw.com/p/1Ihk5
Kaffeebohnen
ምስል imago/Westend61

[No title]

የኢትዮጵያ ቡና ደንበኞች ሲዳማ፤ጅማ፤ነቀምቴ እና ይርጋጨፌ ተብለው የሚታወቁት ዝርያዎችን ሲገዙ ካሁን ቀደም ከነበረው የተለየ መረጃ ያገኛሉ። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በእነዚህ አራት የቡና ዝርያዎች ላይ በዘመናዊው የግብይት ስርዓት አስገዳጅ እየሆነ የመጣውን ባርኮድ ማስቀመጥ ጀምሯል። በመደዳ የተደረደሩ ጥቋቁር ዘንጎች እና ከግርጊያቸው በተደረደሩ ቁጥሮች የሚታወቀው ባርኮድ የአንድን ምርት የህይወት ታሪክ የሚዘረዝር መረጃ በውስጡ ይይዛል። አቶ ኤርሚያስ እሸቱ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።
በዓለም አቀፍ የግብይት ሥርዓት ይህን የመረጃ መለዋወጫ መንገድ መጠቀም አስገዳጅ የሆነ ይመስላል። ከእንቁላል እና የሥጋ ምርቶች ጀምሮ እስከ ውስብስብ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና የመከላከያ እና ጦር መሳሪያዎች ድረስ ባርኮድ ይለጠፍላቸዋል። በዓለም የቡና ምርት እና ግብይት ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው አገራት መካከል ቀዳሚ የሆኑት ብራዚል እና ካምቦዲያ ይህን የመረጃ ማቀበያ ዘዴ መጠቀም ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ኢትዮጵያ ዘግይታም ቢሆን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎችን ተቀላቅላለች።

Äthiopien Bonga Kaffee Äthiopien 9
ምስል DW/J. Jeffrey

የቡና አምራቹ ማንነትን እና የአመራረት ሒደትን ለገዢዎች ማሳወቅ፣ ደንበኞች በኢትዮጵያ የቡና ገበሬ ላይ ያላቸውን እምነት ከማሳደግ በተጨማሪ አምራቾች ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኙ እንደሚያስችል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ያምናሉ።
የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ቡና፤ሰሊጥ እና ቦሎቄን በማገበያየት ይታወቅ እንጂ ሲቋቋም ዋንኛ ትኩረቱ እነዚህ ምርቶች ብቻ አይደሉም። ተለምዷዊውን የግብይት ሥርዓት ለመቀየር የሚታትረው ተቋም «ዳዴ እያለ ያለ ትንሽ ገበያ» ይሉታል አቶ ኤርሚያስ እሸቱ። ይሁንና በስምንት አመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎች ምርቶችን ማገበያየት ችሏል። ከኢትዮጵያ ተሻግሮ ናይጄሪያን ለመሳሰሉ የአፍሪቃ አገሮች ቀና የቅናት መንፈስም አሳድሯል። አቶ ኤርሚያስ ምርት ገበያው ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ የገበያ ሥርዓት ተዋናዮችን አቅም ማጎልበት ላይ አተኩሮ መስራቱን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚጠቀምበት አዲሱ ኤሌክትሮኒክ የመረጃ ማቀበያ ሥልት በ«አይቢኤም» የጀርመን ቢሮ እና የዩናይትድ ስቴትሱ «አይሪስ ቴክኖሎጂ» አማካኝነት የሚቀርብ ነው። ቴክኖሎጂውን ወደ ተግባር በማሸጋገሩ ረገድ «ዩኤስኤይድ» እና «ሰስተነብል ኮፊ» ፕሮግራም ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ተቀናጅተዋል።

የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ምክር በቅርቡ ባጸደቀው መመሪያ መሰረት ምስር፤ቀይ ቦሎቄ እና ቀይ ቦሎቄ የምርት ገበያውን የሚቀላቀሉ ይሆናል። አቶ ኤርሚያስ ወደ ፊት ጤፍ እና ሽንብራም ዘመናዊውን ግብይት እንደሚቀላቀሉ ይናገራሉ።
እንደ የአፍሪቃ ልማት ባንክ መረጃ ከሆነ ባለፉት 25 ዓመታት በ28 የአህጉሪቱ አገራት የምርት ገበያ ተቋማት የማቋቋም ሃሳብ እየተነሳ ሲወድቅ ቆይቷል። በአፍሪቃውያኑ አገሮች በአብዛኛው ሃሳቡን የሚያቀርቡት፤ጥናት ሰርተው ወደ ውይይት መድረኮች የሚያደርሱትም የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ናቸው። ነገር ግን ከሁለት አገራት ውጪ ሃሳቡም ሆነ ውይይቱ ተቀባይነትን አግኝቶ ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም። በባንኩ መረጃ መሰረት ከአፍሪቃ አገራት መካከል ተግባራዊ ግብይት ላይ የተሰማራ በአንጻራዊነትም ስኬታማ የሚባል የምርት ገበያ ማቋቋም የቻሉት ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪቃ ብቻ ናቸው።
ብቁ፤ ዘመናዊ ፤ ግልጽ፤ አስተማማኝና የተቀላጠፈ የምርት ገበያ ከ70% በላይ ለሚሆኑ አፍሪቃውያን የስራ እድል የፈጠረውን የግብርና ዘርፍ ለማሳደግ እና ምርታማ ለማድረግ ሁነኛው መንገድ እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይወተውታሉ። የኢትዮጵያ የምርት ገበያ መስራች እና የመጀመሪያዋ ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ዶ/ር እሌኒ ገብረ-መድህን የዚህ ጽንሰ-ሃሳብ አቀንቃኝ ናቸው። ዶ/ር ኢሌኒ በኢትዮጵያ የምርት ገበያ የነበራቸውን ኃላፊነት አስረክበው የራሳቸውን ኩባንያ ካቋቋሙ በኋላ በጋና፤ካሜሩን፤ኬንያ እና ታንዛኒያ ተመሳሳይ እቅድ ላይ በመስራት ላይ ናቸው። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አፍሪቃውያን በሒደት እና በእርጋታ ጠንካራ የምርት ገበያ ተቋማትን ማቋቋም ከቻሉ የአህጉሪቱን ማሳደግ እንደሚቻል ያምናሉ።
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Äthiopien Bonga Kaffee Äthiopien 1
ምስል DW/J. Jeffrey