1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡና ሽያጭን ለማሳደግ የቀረበው እቅድ

ረቡዕ፣ ጥር 18 2008

የኢትዮጵያ መንግስት በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. ለዓለም ገበያ የሚያቀርበውን የቡና መጠን በ45 ከመቶ ለማሳደግ ማቀዱን የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል። የቡና ግብይትን በቅርበት የሚያውቁ ባለሙያዎች ግን ውጥኑን ለማሳካት በርካታ ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል እያሉ ነው።

https://p.dw.com/p/1HkpT
Äthiopien Kaffeeanbau Illustration
ምስል Coffee Circle

የቡና ሽያጭን ለማሳደግ የቀረበው እቅድ

እቅዱ ከተሳካ ኢትዮጵያ 260, 000 ቶን ቡና ለደንበኞቿ ታቀርባለች። የገበያ ትስስሮችን በመፍጠር፣ ለቡና ላኪዎች እና አቀነባባሪዎች ብድር በማመቻቸት እና በተለያዩ የንግድ አውደ ርእዮች ቡና በማስተዋወቅ እቅዱን ለማሳካት ማቀዱን የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል።
እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ሚኒስቴር ከሆነ፣ በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ካቀረበችው 184,000 ቶን ቡና 780 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች። በዓለም ባንክ መረጃ መሰረት ደግሞ በዚሁ ዓመት ከኢትዮጵያ አመታዊ ምርት 50 በመቶውን የሸፈነው ቡና ነበር።

ባህላዊው የቡና አመራረት እና የማሳ ዝግጅት ውስን ማዳበሪያ እና ጸረ-ተባይ የሚጠቀም ሲሆን ተለቅሞ ታጥቦ ለገበያ እስኪቀርብ የሚያልፍበት ሂደትም ቢሆን በሰው ጉልበት ላይ የተመሰረተ ነው።

15 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በቀጥታ አሊያም በተዘዋዋሪ ከቡና ምርት ጋር በተያያዙ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ናቸው። አገሪቱ የቡና መገኛ እንደመሆኗ ለዓለም ገበያ በምታቀርበው የምርት መጠን ቀዳሚ ባትሆንም ከ7-10ኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ ጠፍታ አታውቅም። ብራዚል፤ቪየትናም፤ ኮሎምቢያ እና ኢንዶኔዥያ ከቀዳሚዎቹ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ኢትዮጵያ በዓለም ከሚጠጣው ቡና ከ7-10 በመቶ ያክሉን ታመርታለች። ኢትዮጵያ ከባህር ጠለል በላይ ባላት አቀማመጥ፤ የአየር ጠባይ፤ ለም አፈር እና አገር በቀል የአመራረት ሥልት በየዓመቱ የምታመርተውን የቡና መጠን ማሳደግ እንደምትችል ይነገራል። በቦን ዩኒቨርሲቲ የግብርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ግርማ ቄልሬቦ የቡና ምርትን ለማሳደግ አገሪቱ ብዙ መስራት ይጠበቅባታል ሲሉ ይናገራሉ።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ