1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡድን ስምንት ጉባኤና ተቃዋሚዎቹ

ሰኞ፣ ግንቦት 27 1999

ቡድን ስምንት የሚባሉት የስምንቱ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አገራት መሪዎች ዓመታዊ ጉባኤ ሊጀመር እነሆ ጥቂት ቀናት ቀርተዋል ። ጉባኤው የፊታችን ረቡዕ ነው በቦልቲክ የባህር ዳርቻዋ የሀይሊገንዳም መንደር የሚከፈተው ። እስከ ዛሬ ሳምንት አርብ የሚዘልቀው ይኽው ጉባኤ ብዙ ካሳሰቡና ለጉባኤተኞቹ ደህንነት ሲባልም ከፍተኛ ገንዘብ ከፈሰሰባቸው ጉባኤዎች ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ነው ።

https://p.dw.com/p/E0c3

ከባዱ የማስተናገድ ሀላፊነት የተጣለባት ጀርመን ጉባኤው ያለአንዳች እንከን እንዲካሄድ ከወራት አንስቶ መጠነ ሰፊ ዝግጅቶችን ስታደርግ ቆይታለች ። ከሁሉም በላይ የጀርመን መንግስት ልዩ ትኩረት የሰጠው ጉባኤው የዓለም ዓቀፉ የሽብር ጥቃት ዒላማ ሊሆን ይችላል የሚለው ስጋት ነበርና አደጋዎችን መከላከል የሚያስችሉ የቅድመ ጥንቃቄ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ነው የቆዩት ። ፖሊስ የሀይሊገንዳምን መንደር ለአንድ ዓመት ያህል ሲያጠና ቆይቷል ። ለፀጥታ ቁጥጥር አመቺ ያልሆኑ ግንባታዎች ፈርሰዋል ። የመሪዎቹ መሰብሰቢያና ማረፊያ ልዩ ልዩ የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎች በተገጠሙለትና አስራ ሁለት ሚሊዮን ዩሮ የሚልቅ ገንዘብ በፈሰሰበት ልዩ የብረት አጥር ተከልሏል ። የቡድን ስምንት መሪዎች ሲሰባሰቡ ከተለመደው የተቃውሞ ሰልፍ ጋር ተያይዞ ሊደርሱ ይችላሉ ተብለው የሚያሰጉ ረብሻዎችን ለመከላከል መንገዶች ተዘግተዋል ። ጉባኤው በሰላም ተጀምሮ በሰላም ይገባደድ ዘንድ የጀርመን መንግስት ከወራት አንስቶ ይህን የመሳሰሉ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያደርግ የጉባኤው ተፃፃሪ ወገኖች ደግሞ የበኩላቸውን ዓለም ዓቀፍ ፀረ ቡድን ስምንት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲያደራጀና ሲያኪሂዱ ነው የሰነበቱት ። እነዚህ ወገኖች የባለፀጎችን ጥቅም ለማስጠበቅ የቆመ ነው የሚሉትን ዓለም ዓቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር ሀሰብ የሚያራምደው የስምንቱ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አገራት መሪዎች ቡድን የሚከተለው መርህ ኢ-ፍትሀዊ ነው ሲሉ ይቃወማሉ ። ተቃውሞአቸውንም በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ሲገልፁ የቆዩ ሲሆን በጉባኤው መቃረቢያ ላይ ደግሞ ተከታታይ ፀረ ቡድን ስምንት ዕንቅስቃሴዎች በማካሄድ ላይ ናቸው ። የጀርመን ፖሊስም የተቃውሞ ዕንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ከወትሮው የጠበቀ ዕርምጃ በመውሰዱ ሰብዓዊ መሰረታዊ መብቶችን በመጋፋት እየተወቀሰ ነው ። ከወቀሳ አቅራቢዎቹ አንዱ “አታክ “የተባለው የቡድን ስምንትን አካሄድ የሚቃወመው የጀርመን ድርጅት ። ይኽው ድርጅት የቡድን ስምንት ዐብይ ትኩረት የሆነውን ዓለማቀፋዊው የኢኮኖሚ ትስስር ላይ የሚነሱ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን በአውሮፓና በዓለም ዙሪያ በጥልቀት ይመረምራል ። የአታክ መስራችና የጀርመን ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ፒተር ቫል ለዶይቼቬለ ራድዮ የአማርኛው ክፍል በሰጡት አስተያየት የጀርመን ፖሊስ ሰሞኑን የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ከመጠን ያለፈ ብለውታል ።
“የሚያደርጉት እጅግ የተጋነነ ነው ። የሚሰሩት ሁሉ እንደ አልቄይዳ የሚያደርሰው ዓይነት የሽብር ጥቃት ጉባኤውን የሚያሰጋው ያህል ነው ። ይህ በአጠቃላይ ትርጉም የየለውም ። ሰላማዊ ያልሆኑት ሰዎች አቅም ፣ በማናቸውም የጀርመን የእግር ክዋስ ግጥሚያዎች ወቅት ከሚታየው የበለጠ አይደለም ።”
ተደጋግሞ እንደሚነሳው አታክ ዓለማችን በኢኮኖሚ ዕንቅስቃሴዎችን መቀራረብዋን አይቃወምም ። ሆኖም የተለየ ዓላማ ላለው ፍትሀዊ ዲሞክራሲያዊና ለአካባቢ ትኩረት የሚሰጥ ዓለም ዓቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር እንነሳ ባይ ነው ። ይህን ሀሳቡንም በልዩ ልዩ መድረኮች ያራምዳል ።
ከአሁኑ የቡድን ስምንት ጉባኤ ጋር በተያያዘም ከዋዜማው አንስቶ የቡድን ስምንትን አካሄድና የወደፊቱን አዝማሚያ የሚቃወም ሰልፎች ሴሚናሮችና የጎዳና ላይ ትርዒቶች እንዲሁም የሙዚቃ ዝግጅት አሰናድቷል ። ጉባኤው በሚጀመርበት ዕለት በሀይሊገንዳም በሚካሄደው ሰልፍ ላይ
ከመቶሺህ በላይ የሚሆኑ ተቃዋሚዎች ይገኛሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው ። በዚህ የተነሳም ፖሊስ ከምን ጊዜም በላቀ ሁኔታ አቅሙን አጠናክሯል ። ሰባት ሺህ የጀርመን ፖሊስ ሀይሊገንዳም ገብቷል ። ተጨማሪ ዘጠኝ ሺህ ፖሊሶች ወደ ስፍራ ይሄዳሉ ። በአጠቃላይ አስራ ስድስት ሺህ ፖሊስ ነው በትንሽትዋ የሀይሊገንንዳም መንደር በጥበቃ የሚሰማራው ። ከዚያ አስቀድሞም የጀርመን ፖሊስ በአጠቃላይ የጉባኤውን ሂደት እንዳይታወክ ልዩ ልዩ የቁጥጥር የቁጥጥር ስልቶችን ዘርግቷል ። ፖሊስ የአንዳንድ ተቃዋሚ ቡድኖች መሪዎችን ቤቶች እና ቢሮዎች ከመፈተሹም በላይ አንዳንዶቹን ኮምፕዩተሮችና የሞባይል ስልኮች ወስዷል ። የመረጃ መረብ ግንኙነትንም በጣጥሷል ። ከዓመታት በፊት የቀረውን የድንበር ላይ የፓስፖርት ቁጥጥርም እንደገና ጀምሯል ። ከዚህ በላይ ከተቃዋሚዎች መሀል ሁከት በማስነሳት የሚጠረጠሩትን በጠረን የሚለዩ የሰለጠኑ ውሻዎች በሰልፎች ወቅት ይሰማራሉም ብሏል ። መንግስት በአንዳንድ ተጠርጣሪዎች ላይ የወሰዳቸውና ሊወስድ ያሰባቸው ዕርምጃዎች ተመጣጣኝም ሆነ ህጋዊም አይደሉም ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ነው ። ከተቃዋሚዎች ውስጥ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጀርመን ቢሮ ይገኝበታል ። የጀርመን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቃል አቀባይ ዳቪድ ባርቴልት
“ሰዎችን ካለአንዳች ምክንያት እየያዙ ለተወሰኑ ሰዓታት የማሰሩ ሀሳብ በአጠቃላይ ሲታይ በኛ አመለካከት ህጋዊ አይደለም ለዕርግጠኝነት በአንድ ማንነቱ በታወቀ ሰው ተጨባጭ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል መረጋገጥ ይኖርበታል ። ይህ ደግሞ በነፃነት የመናገር መብታቸውን ለመጠቀም ከሌሎች አገራት በሚመጡ ሰዎች ላይ የሚደርስ ተመሳሳይ ድርጊት ነው ። ይህ ተገቢ ዕርምጃ አይደለም ለሰልፈኞቹ መካከል አንዳንዶቹ አዋኪ ዕንቅስቃሴዎችን ሊያደርጉ የሚሞክሩ ይሆናሉ ። ሆኖም ብዙሀኑ ተቃዋሚ በነፃነት የመናገር መብቱን በሰላማዊ መንገድ የሚጠቀም መሆኑ ግልፅ ነው ። ስለዚህም ሰልፈኞቹን በሙሉ በአንዳንድ ሁከት መጫር በሚፈልጉ ግለሰቦች ምክንያት አጠቃሎ መወንጀል አይገባም ። “
ተቃዋሚዎች በዚህ መልኩ የፖሊስን ድርጊት ሲያወግዙ መንግስት በበኩሉ የፖሊስን የጥንቃቄ ዕርምጃ ትክለኛነት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከማስረዳት ወደ ኃላ አላለም ። የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል የፀጥታ የማስጠበቁ ዕርምጃ ትክለኛ መሆኑን ሰላማዊውን ተቃውሞም እደግፋለሁ ባይ ናቸው ።
“እኔ የምለው የሀይል ዕርምጃን የሚወስድ ለውይይት ወይም ለንግግር በር የሚዘጋ ነው ። እንደገና በግልፅ መናገር የምፈልገው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ፀጥታ የማስከበርን ዕርምጃ የሚነቅፉት ወገኖች ሁከት ሲፈጠር የፀጥታ ሀላፊዎች ጥንቃቄ አላደረጉም ብለው በመጀመሪያ የሚወቅሱ እነዚህ ወገኖች ናቸው ። እናም ቃላችንና ተግባራችን የሚጣጣሙ ሊሆን ይገባል ። ከዚህ አንፃር ደግሞ በሌላ በኩል ያለ አንዳች ማቅማማት በግልፅ ሊነገር የሚገባው አለ ። እርሱም በሰላማዊ መንገድ የሚቃወሙ ወገኖች መብታቸው ብቻ ሳይሆን እኛም በጥሞና የምናዳምጠው ይሆናል “

የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቮልፍ ጋንግ ሾይብል ደግሞ ወንጀል ይሰራሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎችን ጠረን በመመርመር ማንነታቸውን ለማወቅ ፖሊስ የሚወስደው ዕርምጃ ተገቢ ነው ብለዋል ። የቁጥጥር ዘዴው ከቡድን ስምንት ጉባኤ ጋር አያገኝም ሲሉ ነው ባለፈው ሳምንት በአንድ የጀርመን ቴሌቪዢን የተናገሩት ።
“ዕርምጃ የሚወሰደው በደል የፈፀሙ ሰዎችን በህጋዊ መንገድ ለማደን ነው ። የሚፈለጉትን ሰዎች በተለይም ሆኖ ብለው የሆነ ንብረት ባማቃጠል ወይም ተመሳሳይ ከባድ ወንጀል በመፈፀም የሚጠረጠሩትን ፈልጎ ለመያዝ ሲባል ። ነገር ግን ይህ በምንም ዓይነት በሀይሊገንዳም የስምንቱ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሀገራት መሪዎች ከሚሰበሰቡበት ጉባኤ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ።”
መንግስት ፀጥታ ለማስጠበቅ የወሰዳቸውን ዕርምጃዎች ትክክለኛነት በዚህ መልኩ ሲያስረዳ የመንግስት ድርጊት ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ደግሞ መንግስት ሀላፊነት እንዳለበት የሚረዱ ቢሆንም ሊቀበሉት ያልቻሉት ሀላፊነቱን የሚወጣበትን መንገድ ነው ። የጀርመን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቃል አቀባይ ዳቪድ ባርቴልት
“በዕርግጥም ይህ ሀላፊነት አለባቸው ። ነገር ግን በተጨማሪ መሰረታዊ የሆኑ ሰብኣዊእና ህገ መንግስታዊ መብቶችን የማክበር ግዴታም አለባቸው ይህንንም አሳማኝ በሆነ መንገድ ሊያከናውኑት ይገባል ። ፖሊሶች የሁከት ተቆጣጣሪ ነው ። ሁከትንደግሞ ተመታጣን በሆነ መንገድ የመቋቋም ሀላፊነት አለባቸው ። ይህ አሰራርም ብጥብጥና ሁከትን ለመከላከል ፖሊስ የሚከተለው ዋነኛ መርህ ነው ። ስለዚህ ቁጥጥሩ ከተፈራው አደጋ ጋር የተመጣጠነ ሊሆን ይገባል ። ሆኖም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ይልተስተካከለ ዕርምጃ ነው የሚወስዱት “
በቡድን ስምንት ዓመታዊ ጉባኤ ወቅት የማይቀሩት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉባቸው የተቃውሞ ሰልፎች እንደ ቀድሞዎቹ ጉባኤዎች ከመሪዎቹ መሰብሰቢያ በቅርብ ርቀት ላይ ሊካሄዱ አይችሉም ። በመጀመሪያ የዘንድሮው ዓመታዊ ጉባኤ የሚስተናገድባት ከጀርመን ዋና ከተማ ከበርሊን ሁለት መቶ ሀምሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዋ ታሪካዊትዋ የሀይሊገንዳም መንደር ያለ ምክንያት ለጉባኤው አልተመረጠችም ። ተፈጥሮ ያደላት ይህች መንደር የተገለለች በመሆንዋ የተቃውሞ ዕንቅስቃሴን ለመቆጣጠር አመቺ ናት ። ስብሰባው ወደ ሚካሄድበት ሆቴል የሚያመራው መንገድ አንድ ብቻ ነው ። ይህም አንዱ የፖሊስን ስራ የሚያቀል ነው ተብሏል ። ጉባኤው የሚካሄድበት ሆቴል ሰልፈኛ ዝር እንዳይልባት ተደርጎ ተከልሏል ። ግንባታው ከስድት ወራት በፊት በተጀመረ አስራ ሁለት ኪሎሜትር ርዝመት ባለው የመከላከያ ግንብ ተከልለው ነው የስምንቱ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት አገራት የአፍሪቃና የእስያ መሪዎች ጉባኤ የሚቀመጡት ። ቁመቱ ሁለት ሜትር ተኩል የሚጠጋው ይኽው ግንብ ልዩ ልዩ ዘመናዊ የደህንነት መቆጣጠሪያዎችና ዕንቅስቃሴ መከታተያ መሳሪያዎችም ተገጥመውለታል ። ፀረ ቡድን ስምንት አቋም ያላቸው ወገኖችም ተቃውሞአቸውን መሰንዘር የጀመሩት ገና የአጥሩ ግንባታ ሲጀመር ነበር ። አጥሩን ሁለቱ ጀርመኖች ሲዋሀዱ ከፈረሰው የበርሊኑ ግንብ ጋር እያነፃፀሩ ነበር ትርጉም የለሽነቱን የገለፁት ። በወቅቱም ለዘመኑ የሽብርተኞችና የታጣቂዎች ጥቃት አይኛችንን ጨፍነን አንቀመጥም ሲል ነበር የጀርመን ፖሊስ የዕርምጃውን ትክክለኛነት ሊያስረዳ የሞከረው ። ለግንቡ ስራ ከአስራ ሁለት ሚሊዮን ዩሮ በላይ መውጣቱ ብዙዎች አስቆጥቷል ። ከግንቡ ስራ ተቃዋሚዎች ተቃውሞውች አታክ ነው ። የድርጅቱ መስራች ፒተር ቫል ይህን ይላሉ ።
“ፖሊስ የፀጥታ ቀጣናውን የሚከልል አጥር አስገንብቷል ። አስራ ሁለት ሚሊዮን ዩሮ ነው የፈጀው ልዩ የብረት አጥር ነው ። ይህም በቡድንስምንት ጉባኤ ላይ የሚገኙ ኃያሎች እና ባለፀጎችን ከህዝቡ የመከላከያ ምልክት ነው ። ይህም በጉባኤው ስፍራ ለህዝብ ታዛዥነት እንደሌለ አመልካች ነው ። “
ጉባኤተኖቹን ከጥቃት ለመከላከል በሚል ሰበብ የጀርመን ፖሊስ ተቃዋሚዎች ለደህንነት ከተገነባው ግንብ እስከ አምስት ኪሎሜትር ርቀት ባለው ክልል ውስጥ ዝር እንዳይሉ አግዶ ነበር ። ሆኖም ጉዳዩ የቀረበለት ሰሜን ምስራቅ ጀርመን የሚገኘው የሽቬሪን ፍርድ ቤት እገዳውን ውድቅ በማድረግ የሰልፈኞቹን ፍላጎት የደገፈ ብይን አሳልፏል ። ፍርድ ቤቱ በብይኑ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ለመጠበቅ ከተሰራው አስራ ሁለት ኪሎሜትር ርዝመት ካለው አጥር በሁለት መቶ ሜትር ርቀት ላይ እንዲሰለፉ እንዲፈቀድላቸው የወሰነው ። የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችና ሌሎችም የፖሊስ ዕገዳ ተቃዋሚዎች ቀድሞውንም ቢሆን ተቃዋሚዎቹ ከአምስት ኪሎሜትር በላይ ርቀው ይሰለፉ መባሉ አስገራሚ ውሳኔ እንደነበር ነው የገለጹት ። መልዕክቱ እንዲተላለፍላቸው የሚፈለጉት መሪዎች ሊያዩዋቸው በማይችሉት ርቀት ላይ ተቃዋሙ መባሉ በራሱ ትርጉም የሌለው ፈቃድ ነበር ብለውታል ። ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኃላ የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ህዝቦች መብታቸውን መንገድ ለማስከበር መነሳሳታቸውን እንደሚደግፉ ነገር ግን ኃይልን መጠቀሙ ሊታሰብ የሚገባ እንዳልሆነ ነበር የተናገሩት
ኦቶን................ሜርክል ፪
“አውቃለሁ ብዙ ሰዎች የቡድን ስምንት ጉባኤ ውጤት ያስገኛል አያስገኝም ብለው በጉጉት እንደሚጠባበቁ ለአፍሪቃ ክፍለ ዓለም በጎ ለማድረግ መነሳሳታችንን ለዓለም የዓየር ንብረት መጠበቅ እንደምንተጋ ገደብ የለሹ የኢኮኖሚ ትስስር ከሰብዓዊነት መንፈስ የራቀ እንዳይሆን እንደምንጥር ብዙዎች ያውቃሉ ። ብዙ ሰዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ለፍትሀዊና ሰብዓዊ አጥናፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር ተግተው መነሳሳታቸው መብት መሆኑን አውቃለሁ በደስታ የምቀበለውም ጉዳይ ነው ። ነገር ግን አንድ ነገር ግልፅ መሆን አለበት ። የፖለቲካ ዓላማን ለማራመድ የኃይል ዕርምጃ መሳሪያ ሊሆን አይችልም ። ስለሆነም የኃይል ዕርምጃ እንዳይወሰድ ማረጋገጥ አለብን ። ሰብዓዊነትን ለተላበሰው ዓለም ዓቀፉ አፅናፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር ለቆሙት ወገኖች ሁሉ አደራ የምለው የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ተቃውሞን በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ ተሰሚነት እንደሚኖረው ነው ነገር ግን የኃይል ዕርምጃ ሊታሰብ አይገባውም ። “
የቡድን ስምንት ጉባኤን በግንባር ቀደምትነት የሚቃወመው አታክ የፊታችን ቅዳሜ በሮስቶክ ውስጥ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ያካሂዳል ። ሮስቶክ ሀይሊገንዳም አቅራቢያ የምትገኝ ከተማ ናት ። ዕሁድ ደግሞ ሴሚናሮችና የጎዳና ላይ ትርዒቶች ይታያሉ ። በጉባኤው ዋዜማም ከየአህጉራቱ የሚመጡ ታዋቂ ሰዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ ይከፈታል ። ጉባኤው እስከ ሀሙስ ይቀጥላል ። የቡድን ስምንት ጉባኤ በሚከፈትበት ዕለት ረቡዕ ደግሞ በሚከፈትበት ዕሮብ ዕለት ደግሞ ዋነኛዎቹ ልዑካን በሚገቡበት አውሮፕላን ማረፊያ ና ጉባኤተኞቹን ለመጠበቅ በተሰራው ግንብ አቅራቢያ ሰላማዊ ሰልፎች ይካሄዳሉ ። የተቃውሞው ዕንቅስቃሴ የሚያበቃውም ታዋቂ አቀንቃኞች በሚሳተፉበት የየሙዚቃ ዝግጅት ነው ።
በዚህ ወቅት በጀርመን ከቡድን ስምንት ጉባኤ ጎን ለጎን የሚካሄዱት የተለያየ ዓላማ ያላቸው የተቃውሞ ዕንቅስቃሴዎች ለሀገሪቱ ፀጥታ አስከባሪዎች ከባድ ፈተና እንደሚሆን ነው የሚገመተው ።