1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቢሊዮን ዓመት ጉዞ፥ የስበት ኃይል ሞገዶች

ረቡዕ፣ የካቲት 9 2008

የምንኖርባትን ምድር ጨምሮ ፍጥረተ-ዓለም (Universe) እንደምን ተዘረጋ፤ እንዴትስ ተከሰተ? ሃይማኖት እና ሣይንስ የእየራሳቸው መልስ አላቸው። ሣይንስ ፍጥረተ-ዓለም ከ14 ቢሊዮን ዓመታት በፊት በተከሰተ አንዳች ኃያል ፍንዳታ «ዕውን ኾነ» ይላል። ፍጥረተ-ዓለም ሲከሰት የነበረውን ቅጽበት መመርመር የሚያስችል ብልሃት መገኘቱም ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/1Hwhv
Deutschland Max-Planck-Institut Gravitationswellen
ምስል picture-alliance/dpa/M. Hanschke

የቢሊዮን ዓመት ጉዞ፥ የስበት ኃይል ሞገዶች

ከወደ ዩናይትድ ስቴትስ የተነገረው የሰሞኑ ዜና ግን ፍጥረተ-ዓለም ሲከሰት የነበረውን ቅጽበት መመርመር የሚያስችል ግኝት ላይ መደረሱን ይፋ አድርጓል፤ በስበት ኃይል ሞገዶች በመታገዝ። ስነ-ፈለክ ላይ ምርምር የሚያከናውኑ ጠቢባን የስበት ኃይል ሞገዶችን (Gravitational waves) ለመጀመሪያ ጊዜ ያለአንዳች መዛነፍ መለካት መቻላቸውንም ይፋ አድርገዋል።

የሰው ልጅ በዘመኑ ከዋክብቱን፤ ፀሓያቱን፤ ኅዋን፤ ምድርን በአጠቃላይ ፍጥረተ-ዓለም ለመቃኘት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዋናነት የተለያዩ ብርሃናት ጥገኛ ነበር። ዛሬ ግን ሥነ-ፈለክ ምርምሩ አዲስ መሥመር እንደያዘ ተበስሯል። ከእንግዲህ ፍጥረተ-ዓለም (ዩኒቨርስ) በስበት ኃይል ሞገዶች በመታገዝ በሚከወን ሥነ-ፈለክ ምርምርም ይቃኛል ሲሉ ሣይንቲስቶቹ ተኩራርተዋል። ለመኾኑ በሣይንሱ ዘርፍ በተለይም በ«አስትሮ-ፊዚክስ» ከፍተኛ እመርታ የተባለለት ይኽ ግኝት ምንድን ነው? ዶ/ር ያብባል ታደሠ በአውሮጳ የኅዋ ተቋም የጠፈር አፈጣጠር ምሥጢርን ለመፍታት አሠሣ በሚያደርገው ሳተላይት የሚሰበሰቡ መረጃዎችን የሚተነትኑ ሣይንቲስት ናቸው። በሮም ቶርቨር ጋታ ዩኒቨርሲቲ የፕላንክ ሣተላይት መረጃንም ይተነትናሉ።

Gravitationswellen Schwarze Löcher verschmelzen
የስበት ኃይል ሞገድ ገጽታምስል S. Ossokine/A. Buonanno/Max-Planck-Institut für Gravitationsphysik/W. Benger/Airborne Hydro Mapping GmbH/dpa

«ይኽ የተገኘው ነገር እንግዲህ የስበት ኃይል ሞገድ ወይንም ደግሞ (Gravitational waves) ነው።» ያሉት ያብባል ተመራማሪው ዶክተር ስለሞገዶቹ በአልበርት አንሽታይን ነባቤ-ቃል ከመቶ ዓመት በፊት ተተንብዮ የነበረ ቢኾንም፤ እስከዛሬ ግን «በቀጥታው አልተረጋገጠም ነበር» ብለዋል።

«በአሜሪካ እና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ የፊዚክስ ሊቃውንት አንድ ላይ ለረዥም ጊዜ ሲሠሩበት ነበር። አኹን ባለፈው ሣምንት ይኼንን በቀጥታ በማረጋገጣቸው የአንሽታይን ትንታኔዎች ሙሉ በሙሉ ትክክል እንደኾኑ አረጋግጠዋል። ስለዚህ ይኽ የስበት ኃይል ሞገዶች ልኬት ነው።» ሲሉም አክለዋል።

ስለ የስበት ኃይል ሞገዶች ምንነት ከማጤናችን በፊት መሠረታዊ የኾነውን የስበት(gravity) ትርጓሜ ማስታወስ ያሻል። በደቡብ አፍሪቃ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪ እና መምህር ዶክተር አማረ አበበ ፍጥረተ-ዓለም ላይ ጥናት እና ምርምር የሚያከናውኑ ሳይንቲስት ናቸው። የዘመናዊ ሣይንስ አባት የሚባለው አይዛክ ኒውተን እና የሃያኛው ክፍለ-ዘመን ታላቁ ሣይንቲስት አልበርት አንሽታይን ስለ ስበት ምንነት ያሰፈሯቸውን ትንታኔዎች ይጠቅሳሉ። በአይዛክ ኒውተን ቅመራ መሠረት ስበት የሚፈጠረው ሁለት ክብደት ባላቸው ነገሮች ሲኾን፤ ነገሮቹ በክብደታቸው ብቻ የመሳሳብ ኃይል አላቸው። «ያ የመሳሳብ ኃይል በኒውተን አገላለጥ ስበት ይባላል።» ብለዋል ዶክተር አማረ። በአልበርት አይንሽታይን ቅመራ መሠረት ደግሞ ስበት በሁለት ክብደት ባላቸው ነገሮች የሚፈጠር ሳይኾን «ነገሮች ወደታች የሚወድቁት ቦታ ጊዜ ስለሚሰረጎድ ነው» ሲሉ አብራርተዋል።

እስኪ ነገሩን በምናባችን የበለጠ ለማፍታታት እንሞክር። አንድ ነጠላ አለያም ኩታ በአራቱም አቅጣጫ በሚገባ ወጥረው ከመሬት ከፍ አድርገው ይዘርጉ። ነጠላውን እንደ በአልበርት አይንሽታይን ማብራሪያ መሠረት ምድርን ጨምሮ ጠፈር ሁሉ የተሞላበት የቦታ ጊዜ ጥምረት (space time) የማይታይ እና የማይዳሰስ ምናባዊ ገጽታ ተምሳሌት ነው ብለው ይቁጠሩት። እላዩ ላይ ከበድ ያለ የብረት ሉል ይጣሉ። ሉሉ ባረፈበት አቅጣጫ ነጠላው አለያም ኩታው ወደታች መሰርጎዱ አይቀርም።

የኖቤል ተሸላሚው የፊዚክስ ሊቅ እና ፈላስፋው አልበርት አይንሽታይን
የኖቤል ተሸላሚው የፊዚክስ ሊቅ እና ፈላስፋው አልበርት አይንሽታይንምስል picture alliance/CPA Media Co. Ltd

አኹን ከብረት ሉሉ በክብደት ያነሱ ነገሮችን በነጠላው ዙሪያ ይኮልኩሉ። የዱባ ፍሬ፤ ብርቱካን ወይንም የሾላም ፍሬ ሊኾን ይችላል፤ አለያ ደግሞ ከወደ ጠርዙ ሎሚ ይወርውሩ። የወረወሯቸው ቁሶች በአጠቃላይ የብረት ሉሉ ወዳሰረጎደው የነጠላው ዝቅተኛ ወለል እየተግተለተሉ መውረዳቸው አይቀርም። ይኽ ነው እንግዲኽ ቁሳዊ አካላትን ከቦታ ጊዜ ጋር በአንድነት ያጣመረው የአልበርት አይንሽታይን የስበት ኃይል ትንታኔ በሌላ መልኩ ሲብራ።

ያለ አንዳች ስህተት ተለክተዋል የተባሉት እነዚህ የስበት ኃይል ሞገዶች፤ ጽልመታዊ ጉድጓዶች (black holes)ወይንም ኒውትሮን ከዋክብት ከ1,3 ቢሊዮን ዓመታት በፊት እርስ በርስ ተሽከርክረው ሲላተሙ የተፈጠሩ ናቸው እንደ ሣይንስ ማብራሪያ። ሞገዶቹ በብርሃን ፍጥነት ተጉዘው ምድር የደረሱትም እጅግ ተዳክመው ነው። ለመኾኑ እነዚህ ምድር ደረስው ተለክተዋል የተባሉት የስበት ኃይል ሞገዶች ምንድን ናቸው?

ጠፈር የተሞላበት የቦታ ጊዜ ድር በቁሶች እንቅስቃሴ የሚፈጥረው ስርጉዳት የሚያስከትለው ርግብግቢት እየሰፋ የሚኼድ ነው። ልክ ወኃ ላይ ጠጠር ቢጣል በክብ ቅርፅ እየተርገበገበ እንደሚሰፋው ኹሉ ማለት ነው። ጀርመናዊው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አይንሽታይን ይኽን ሐሳቡን ያፈለቀው ከዛሬ አንድ መቶ ዓመታት በፊት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1916 ዓመት ነበር።

ኅዋ ላይ ክብደት ያለው ማንኛውም ቁስ አካል እንደ እንዝርት እየሾረ ወጥ ባልኾነ መልኩ በፍጥነት የሚዘውረውን ሌላ አካል እሱም የሚዞረው ከኾነ ያኔ የስበት ኃይል ሞገዶች ይፈጠራሉ። አልበርት አይንሽታይን እነዚህ የስበት ኃይል ሞገዶች ስለመኖራቸው ትንታኔ ከሰጠ አንድ ክፍለ-ዘመን ተቆጥሯል። ታዲያ ሞገዶቹ እስከ አኹን ድረስ ስለምን ሣይገኙ አለያም ሳይለኩ ቀሩ?

ይኽ በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ (LIGO) ማለትም፦ በረቂቅ የብርሃን ልቄት የስበት ኃይል ሞገዶች መለኪያ መሣሪያ መፈብረኩ የስበት ኃይል ሞገዶችን ቅንጣት ታኽል ሳያዛባ ለመለካት አስችሏል። የስበት ኃይል ሞገዶችን ለመለካትም ከላይ ሲታዩ የ«ረ» ፊደል ቅርጽ ይዘው የተዘረጉ፥ በሁለቱም አቅጣጫ አራት ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ እጅግ በረቀቀ መልኩ የተገነቡ ቱቦዎችን ዋሽንግተን እና ሉዊዚያና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሣይንቲስቱ ተጠቅመዋል።

በሁለቱ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ በተተከሉት የላይጎ መሣሪያዎች እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር መስከረም 14ቀን 2015 ዓመት የተለካው የስበት ኃይል ሞገድ ውጤት መቶ በመቶ ትክክለኛ እንደኾነ ተገልጧል። ግኝቱ ባለፈው ሣምንት ለዓለም ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ ግን የተሰበሰበው መረጃ የግድ በጥንቃቄ መመርመር ነበረበት። ለመኾኑ የስበት ኃይል ሞገዶች ያለአንዳች ሣንካ በተሳካ መልኩ የመለካታቸው ነገር ፍጥረተ-ዓለም ላይ እንድምታው ምን ይኾን?

ዶክተር አማረ አበበ በልዩ የማጉያ መነፅር ወይንም ቴሌስኮፕ ማየት የማንችላቸውን የኅዋ አካላት ወደፊት በስበት ኃይል ሞገዶች መለካት እንደሚቻል ግኝቱ መጠቆሙ ታላቅ እመርታ ነው ብለዋል። ዶ/ር ያብባል ታደሠ በበኩላቸው ግኝቱ ሁለት ነገሮችን እንደሚያበስር ገልጠዋል። አንድም የአልበርት አይንሽታይን ነባቤ-ቃል ትክክለኛ መኾኑን፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ፍጥረተ-ዓለም በሌላ ዐይን መታየት እንደሚቻል ጠቅሰዋል። ሞገዶቹን በለካው ላይጎ ልዩ መሣሪያ ከ1000 በላይ ሣይንቲስቶች ተሳትፈዋል። ምርምሩ 1 ቢሊዮን ዶላር አስወጥቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

የላይጎ መሣሪያ ውስጥ ያለው ረቂቅ አንፀባራቂ መስተዋት
የላይጎ መሣሪያ ውስጥ ያለው ረቂቅ አንፀባራቂ መስተዋትምስል Courtesy Caltech/MIT/LIGO Laboratory
የላይጎ መሣሪያ ከላይ ወደታች ሲታይ
የላይጎ መሣሪያ ከላይ ወደታች ሲታይምስል Courtesy Caltech/MIT/LIGO Laboratory

ኂሩት መለስ