1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባህል መድረክ -ጀርመን

ሐሙስ፣ ግንቦት 16 2004

ሰምወኑን የዶቼ ቬሌ የባህል ድር-ገጽ ካተኩረባቸዉ ርዕሶች መካከል የብሪታንያዉ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሮቢን ጊብ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ፣ እንዲሁም የፊታችን ቅዳሜ አዘርባጃን መዲና ባኩ ላይ የሚካሄደዉ ዓመታዊ የአዉሮጳ የሙዚቃ ዉድድር ትርኢት ጉዳይ ዋናዎቹ ናቸው። እኛም በለቱ ዝግጅታችን በነዚሁ አርእስት ላይ አትኩረናል፤

https://p.dw.com/p/151fs
የካስፒያንን ባህር የተንተራሰችዉና በዘይት ሃብቷ በታወቀችዉ አዘርባጃን መዲና ባኩ
የካስፒያንን ባህር የተንተራሰችዉና በዘይት ሃብቷ በታወቀችዉ አዘርባጃን መዲና ባኩምስል picture-alliance/dpa

ሰምወኑን የዶቼ ቬሌ የባህል ድር-ገጽ ካተኩረባቸዉ ርዕሶች መካከል የብሪታንያዉ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሮቢን ጊብ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ፣ እንዲሁም የፊታችን ቅዳሜ አዘርባጃን መዲና ባኩ ላይ የሚካሄደዉ ዓመታዊ የአዉሮጳ የሙዚቃ ዉድድር ትርኢት ጉዳይ ዋናዎቹ ናቸው። እኛም በለቱ ዝግጅታችን በነዚሁ አርእስት ላይ አትኩረናል፤

መንትያ ወንድሙ ሞሪስ በጎርጎረሳዉያኑ 2003 ዓ,ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። አሁን ደግሞ ሮቢን ጊብ ከነቀርሳ በሽታ ጋር የጀመረዉን ትግል ተሸነፈና በስድሳ ሁለት አመቱ እሱም አሸለበ። የቀረዉ የባንዱ ጭንቅላት የሆነዉ እና ታላቅ ወንድሙ ቤሪ ብቻ ነዉ ይላል፣ ታዋቂዉ የብሪታንያ የፖፕ ሙዚቃ ቡድን «የቢጂስ» አባል ሮቢን ጊብ ከዚህ አለም በሞት በተለየ ማግስት ይፋ የሆነዉ ጽሑፍ። ሶስት ወንድማማች ብሪታንያዉያን የፖፕ አቀንቃኞችን ያካተተዉ ቡድን አባል ሮቢን ጊብ ባሳለፍነዉ ሳምንት መጨረሻ እሁድ እለት በነቀርሳ በሽታ ህመም ምክንያት በስድሳ ሁለት አመቱ በለንደን ከተማ ከዚህ አለም በሞት መለየቱ እንዲህ ነበር የተሰማዉ።

Robin Gibb gestorben
ሮቢን ጊብምስል AP

እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር 1958 ዓም ቤሪ ጊብ,ሞሪስ ጊብ እና ሮቢን ጊብ በመባል የሚታወቁት ሶስት እንግሊዛዉያን ወጣቶች በአዉስትራልያ የሙዚቃዉን መድረክ አሃዱ በማለት ይጀምራሉ። ከስምንት አመት በኋላ የጊብ ቤተሰቦች ልጆቻቸዉን ይዘዉ ወደ ትዉልድ አገራቸዉ እንግሊዝ ይመለሳሉ። ወደ ብሪታንያ እንደተመለሱ ወጣቶቹ «ቢጂስ» በሚል ስያሜ ከአንድ የጀርመን የሙዚቃ አሳታሚ ድርጅት ጋር ዉል ከተዋዋሉ በኋላ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ታዋቂነትን እንዳገኙ ጽሑፎች ይጠቁማሉ። እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር 1969 ቢጂስ የሚል የሙዚቃ ቡድን ስያሜን የያዙት ወንድማማች እንግሊዛዉያን አቀንቃኞች በጥል ተለያይተዉ በየግላቸዉ ሙዚቃን በመድረክ መጫወት ጀምረዉ እንደነበር ይታወሳል። ግን ያ አልሳካ በማለቱ በቢጂስ የሙዚቃ ቡድንነታቸዉ ጸንተዉ እና ዳግም ተገናኝተዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1977 ዓ,ም በጋራ ወደ መድረክ በመመለስ «ሳተርደይ ናይት ፊበር»የተሰኘዉን በፊልም የተደገፈዉን ሙዚቃቸዉን እንዲሁም በ1987 ዓም የተሰኘዉን በአለም የሙዚቃ አፍቃሪ ዘንድ የተወደደዉን « ዩ ዊን አጌን» የተሰኘዉን ሙዚቃቸዉን አቅርበዉ ከፍተኛ ዝናን ያተርፋሉ። ሮቢን ከወንድሞቹ በሪ እና ሞሪስ በ60 ዎቹ እና 70 ዎቹ ዓመታት በአለም የሙዚቃ አፍቃሪ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆኑ እና የማይረሱ ሙዚቃዎችን አቅርበዋል። የዲስኮ ሙዚቃ ተብለዉ የሚጠሩላቸዉና ዝናን ካተሩፍላቸዉ ሙዚቃዎች መካከልም « ስቴይ አላይፍ» « ናይት ፊበር» የተሰኙት ሙዚቃዎቻቸዉ ይገኙበታል። ቢጂስ የሙዚቃ ባንድ እነዚህን ተወዳጅ የሙዚቃ አልበሞች ከ 200 ሚሊዮን እትም በላይ በመሸጥ በአለም ታዋቂ እና ዝናን ካተረፉት ሮሊንግ ስቶንስ፣ ቢትልስ ፤ አባ፣ ፒንክ ፍሎይድ ከተሰኙት ዝነኛ የሙዚቃ ባንዶች ተርታ እንደሚሰለፍሙ ተዘግቦላቸዋል።

Bee Gees
ቢጂስ-የሚል የሙዚቃ ቡድን ስያሜን የያዙት ወንድማማች እንግሊዛዉያን አቀንቃኞችምስል Reuters

ባሳለፍነዉ እሁድ ከዚህ አለም በሞት የተለየዉ የ62 አመቱ የጊብ ቤተሰብ ወይም ቢጂስ በመባል የሚታወቀዉ የሙዚቃ ቡድን አባል ሮቢን የዛሪ ስድስት ወር ግድም በአንጀት ህመሙ ምክንያት ቀዶ ጥገና ማድረጉን፣ በህክምናዉ ወቅት ኃይለኛ የሆነ የነቀርሳ በሽታ እንዳለበት ታወቀ። በመቀጠል ከህመሙ አገግሞ ባለፈዉ የካቲት ወር ላይ ሮቢን እንደተሻለዉ በመገናኛ-ብዙሃን ቀርቦም አስታዉቆ፣ የያዘዉን በሽታ መርታቱን በደስታ ተናግሮ ነበር። ግን በርግጥ ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ እንደገና ታሞ የአልጋ ቁራኛ ሆነ። የብሪታንያዉ እዉቁ ታይታኒክ መርከብ የሰመጠበትን 100ኛ ዓመት በማስመልከት ከወንድ ልጁ ሮቢን ጆን ጋር ለንደን ላይ ለማቅረብ ባሰበዉ የሙዚቃ ዝግጅት በህመሙ ምክንያት መካፈልም ሆነ መገኘት አልቻለም። ሮቢን በቢጂስ የሙዚቃ ባንድ አባልነቱ ና በታዋቂ ሙዚቃዎቹ ብቻ ሳይሆን በአለም ታዋቂ ሙዚቀኞች ለዲያና ሮዝ፣ ለባርባራ ስትራይሰንድ፣ ለኬኒ ሮጀርስ እና ለዶሊ ፓርተን የዜማ ግጥም ድርሰት በመጻፉም ይታወቃል። ቢጂስ የሙዚቃ ቡድን በተለይ እንደጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 1977 ዓ,ም ካሳተሙት የሙዚቃ አልበም መካከል «ሳተርደይ ናይት ፊበር» የተሰኘዉን ሙዚቃ ከ 40 ሚሊዮን ቅጂ በላይ በመሸጡ ተወዳጅነትንና ዝናን ማትረፉ እሙን ነው። ሮቢን ጊብ ባለፈዉ እሁድ ግንቦት 12 ቀን ከዚህ አለም በሞት ተለየ። ሮቢን አራት ልጆች አባት ነበር። በብሪታን የሚታተመዉ «ዘ ሰን» የተሰኘዉ ጋዜጣ ዘገባ መሠረት አንጋፋዉ የቢጂ ሙዚቃ ቡድን አባል የሮቢን ጊብ ቀብር ሥነ-ሥርዓት በዓለም የሚገኙ ከያንያን በተገኙበት እንደሚፍጸም ባለቤቱ «ድዊንን» ጠቅሶ አትቷል።

ESC in Baku Tag 2
ምስል DW

ሁለተኛዉ ርሳችንም እንዲሁ በሙዚቃ ዙርያ በአዉሮፓ ያቆየናል፣ በያዝነዉ ሳምንት መጨረሻ «ይሮ ቪዥን ሶንግ ኮንቴስት» በመባል የሚታወቀዉ የአዉሮጳ ሃገራት የሙዚቃ ዉድድር መድረክ በቀድሞዋ የሶብየት ህብረት ሪፐብሊክ ግዛት በነበረችዉ በአዘርባጃን ለ 57 ኛ ግዜ ይካሄዳል። በአዘርባጃን የሚታየዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የተጓደለ የዲሞክራሲ እንቅስቃሴ እና አፈና ለአለም ህዝብ ለማሳየት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይህንን ግዙፍ የሙዚቃ ዉድድር መድረክ መጠቀም ይፈልጋሉ። በዚህም በአዛርባጃንም ሆነ በሌሎች ሃገራት ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅትን የመሳሰሉ የመብት ተሟጋቾች ድምጻቸዉን ማሰማት ጀምረዋል። ለዲሞክራሲ ዘምሩ « ሲንግ ፎር ዶምክራሲ» በተሰኘ በተለያዩ የአዉሮጳ ከተሞች በርሊንን ጨምሮ እየተዘዋወሩ በአዘርባጃን የዲሞክራሲ አፈና አና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቀር ድምጻቸዉ ለአለም ህዝብ እንዲሰማ በመጣር ላይ ናቸዉ።

እንዲሁም ሆኖ የአለም የሙዚቃ አፍቃሪዎች የካስፒያንን ባህር የተንተራሰችዉና በዘይት ሃብቷ በታወቀችዉ አዘርባጃን መዲና ባኩ ላይ የሚደረገዉን ዉድድር እዚያዉ ባኩ ከተማ በመገኘት አልያም በቀጥታ የቴሊቭዝን ስርጭት ለመከታተል ዝግጅታቸዉን ያጠናቀቁ ይመስላል። ጀርመንን ወክሎ በመድረኩ ሙዚቃዉን ይዞ የሚቀርበዉ የ 21 አመቱ ሮማን ሎብ በዚህ መድረክ ለመሳተፍ የበቃዉ «የኛ ኮከብ ሙዚቀኛ ለባኩ የዉድድር መድረክ» በተሰኘ በጀርመን ተዘጋጅቶ የነበረዉን የሙዚቃ ዉድድር ካሸነፈ እና በርካታ ሰፊ መድረኮች ላይ የሙዚቃ ድግሱን ካሳየ እና ከተለማመደ በኋላ ነዉ።

Unser Star für Baku Roman Lob
ምስል dapd

« ላይት ዮር ፋየር» በተሰኘ መርህ ዘንድሮ አዘርባጃን ባኩ ላይ ለመካሄድ የበቃዉ ይህ የአዉሮጳ አገራት የሙዚቃ ዉድድር ዘንድ አዉሮጳዉያን አቆጣጠር 2010 ዓ, ም ፣ ኦስሎ ፤ ኖርዊይ ላይ በተደረገዉ ዉድድር ጀርመናዊትዋ ወጣት ሌና ማየር ላንድሩት ባዜመችዉ ሳተላይት በተሰኘዉ ሙዚቃዋ ማሸነፍዋ የሚታወስ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ በጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓ,ም ጀርመን ባዘጋጀችዉ የአዉሮጳ የሙዚቃ ዉድድር ላይ የአዘርባጃኖቹ ከያኔዎች በማሸነፋቸዉ ነበር ዘንድሮ አዘርባጃን የዉድድሩ አዘጋጅ ለመሆን የበቃችዉ። ለዉድድሩ ባጠቃላይ የቀረቡት 42 ሃገራት ሲሆኑ የግማሽ ማጣርያ ባለፈዉ ማክሰኞ የተካሄደ ሲሆን ሁለተኛዉ ማጣርያ ዉድድር ዛሬ ምሽት ከተካሄደ በኋላ ቅዳሜ ዕለት ለፍጻሜ ያለፉ ሃገራት ለዉድድሩ ይቀርባሉ። በአለም ያሉ አገራት ከአፍሪቃ ደቡብ አፍሪቃ እና በአንዳንድ ሰሜን አፍሪቃ አገራት የሙዚቃ ዉድድሩ በቀጥታ የቴሌቭዝን ስርጭት ይተላለፋል። በቦታዉ በቀጥታ የሚከታተለዉ ታዳሚ ወደ 37,000 መቀመጫ መዘጋጀቱ ተነግሮአል።

«ይሮ ቪዥን ሶንግ ኮንቴስት» የተሰኘዉ የሙዚቃ ዉድድር አዉሮጳዉያን እርስ በርስ ጦርነትን አቁመዉ ለጋራ መተሳሰር እና መግባባት እና በመደጋገፍ የጀመሩት የጋራ መድረክ ሲሆን ሁለተኛ አለም ጦርነት በተጠናቀቀ በአስራ ሁለተኛ አመቱ እንደ አዉሮጳዉያን አቆጣጠር 1956 የአዉሮጳ የራድዮ ሥርጭት ማኅበር ለመጀመርያ ጊዜ ያቋቋመዉ የሙዚቃ ዉድድር እንደሆነም ጽሁፎች ይጠቁማሉ። ነገሩ አዉሮጳዉያን ተሰኘ እንጂ የራድዮ ማህበር አባል ሃገራት ሁሉ የሚሳተፉበት ሲሆን የማህበሩ አባላት እስራኤልን የእስያ አገራትን እንዲሁም የሰሜን አፍሪቃ አገራትንም ያጠቃልል። እስከዛሪ በዚህ ዉድድር ከአፍሪቃ ሞሮኮ እ,ጎ,አ 1980 አ.ም የተሳተፈች ሲሆን ከአዉሮጳዉ የራድዩ ስርጭት ማህበር በዚህ የሙዚቃ ዉድድር እስከዛሪ ያልተሳተፉ አገራት አልጀርያ ቱኒዚያ ሊቢያ ግብጽ ዮርዳኖስ እና ሊባኖስ ይገኙበታል። የአዉሮጳ የራድዩ ስርጭት ባህበር አባላት ባጠቃላይ ሰባ አምስት ሲሆኑ ሃምሳ ስድስቱ አዉሮጳ ዉስጥ የሚገኙ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ሰሜን አፍሪቃ እና እስያ ዉስጥ የሚገኙ አገሮች ናቸዉ። ዘንድሮ አዘርባጃን ይህንን ዉድድር ለ 57ኛ ግዜ ታዘጋጃለች።
እ.አ 1965 አ.ም ለመጀመርያ ግዜ በኦስትርያ ሉጋኖ ዉስጥ የተካሄደዉ ይህ የአዉሮጳ የሙዚቃ ዉድድር መድረክ በአለም ዙርያ ተወዳጅ የሆኑ ሙዚቀኞችን አፍርቶአል። ለምሳሌ በአለም ታዋቂዋ የፖፕ የሙዚቃ ተጫዋች ሰሊን ዲዮን የአዉሮጻዉ የዉድድር መድረክ ለሰላሳ ሶስተኛ ግዜ ባቀረበዉ የዉድድር መድረክ ላይ ተሳትፋ ባቀረበችዉ የፈረንሳይኛ ሙዚቃ ነዉ። የአለም የሙዚቃ መድረክ ኮከብ ለመሆን የበቃችዉ።
የስዊድኑ የፖፕ ሙዚቃ ባንድ አባ በ 1977አ.ም «ዋተር ሉ» የተሰኘዉን ሙዚቃቸዉን በዉድድር መድረኩ በማቅረባቸዉ ነዉ አሸናፊነትን ይዘዉ በአለም የሙዚቃ አፍቃሪ ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኙት።

BdT Deutschland Rockpop Celine Dion in Berlin
ታዋቂዋ የፖፕ የሙዚቃ ተጫዋች ሰሊን ዲዮንምስል AP

ከወዲያኛው ሰሞን ፣ በአለም ተደናቂ የሆኑ የሙዚቃ ከዋክብቶች ከዚህ አለም በሞት የተለዩበት ነዉ፤ ስራቸዉ ግን ለዘላለም ህያዉ ያደርጋቸዋል። የዲስኮ ንግስት በመባል የምትታወቀዋ ጥቁር አሜሪካዊት ዶና ሳመር ባሳለፍነዉ ሳምንት ሃሙስ ግንቦት 9 እለት ነበር በሳንባ ነቀርሳ በሽታ ለብዙ ግዜ ታማ በ63 አምትዋ ከዚህ አለም በሞት መለየትዋ የተሰማዉ። ዶና ሳመር በቦስተን ማሳቹሰትስ ከ10 አመትዋ ጀምሮ የታወቀች የጎስፐል ዘማሪ ነበረች። ጀርመን ሙኒክ ከተማ ከሚገኝ የሙዚቃ አሳታሚ ድርጅት ጋር ዉል ተፈራርማ በጀርመንዋ ባየር በ20 አመትዋ ለአለም የዲስኮ ንግስትነት ያበቃትን ዘመን የማይሽራቸዉን ሙዚቃዎችዋን ለአለም አቀረበች። በሃያ አመትዋ ሙዚቃ የማሳተም እድል አግኝታ ከዪናይትድ ስቴትስ ወደ ጀርመን ባየር ሙኒክ ከተማ ስትመጣ ወላጆችዋ ባውጡላት ላዶና አድሪያን ጋኒስ በሚለው ስም ነበረ የምትታወቀው። በዚሁ ስያሜዋ በርካታ ሙዚቃዎችን አዚማ በአለም የሙዚቃ መድረክ ብቅ ማለት የጀመረችዉ ላዶና አድሪያን የጥርስ ሃኪሙን ኦስትሪያዊ ሄልሙት ሰመርን አግብታ ነበር መጠርያ ስምዋ ላ ዶና ሰመር የተባለችዉ። ከዝያም « ላቭ ቶ ላቭ ዩ ቤቢ» «አይ ፊል ላቭ» እንዲሁም « ሺ ዎርክስ ሃርድ ፎር ዘ መኒ» የተሰኙት ዜማዎችዋን አዚማ የዲስኮ ንግስት የሚል መጠርያን አገኘች። በአለም የሙዚቃ መድረክ ተወዳጅ ያደረጓት ዘመን የማይሽራቸዉ ዜማዎችዋ አሁንም ህያዉ ሆነዉ በወጣቱ ተወዳጅ ናቸዉ። በታዋቂ የሙዚቃ መድረኮች በስራዎችዋ የወርቅ እና ፕላቲን ሽልማቶችን አግኝታለች። በሰባዎቹና በሰማንያዎቹ በአለም ታዋቂ የሆኑት ሙዚቀኞች እንደ ማይክል ጃክሰንና፣ ማዶና የመሳሰሉ ከያኒዎች የስዋን ፈልግ ተከታዮችና አድናቂዎች እንደነበሩ ይነገራል ፤ ስለነበራት ታላቅ ችሎታ፤ እነርሱ ራሳቸው መሥክረውላታል። «የዲስኮ ንግሥት!» የሚለው የማሞካሻ ማዕረግ ፤በሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ገኖ ቢነገርም፤ እርሷ ራሷ፣ ታላቅ የሙዚቃ ክህሎቷን የሚያቃልል እንዳይሆን ሥጋቱ ነበራት፤ ዶና ሳመር የዲስኮ ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ስልቶች ተወዳጅ ሙዚቃዎችን ትደርስ የነበረች ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰው መሆንዋን የሚመሠክሩላት አርቲስቶች ጥቂቶች አይደሉም። የሶስት ልጆች እናት የነበረችዉ የዲስኮ ንግስት ዶና ሰመር ትናንት በዪናይትድ ስቴትስ ናሽቪል ፤ ቴነሲ ቤተሰቦችዋ እና የቅርብ ጓደኞችዋ በተገኙበት የቀብሯ ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሞአል።

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ