1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባህረሠላጤው ቀውስና አፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 27 2009

በዐረብ ባህረ ሠላጤ ሀገራት መካከል የተፈጠረው ቀውስ አንደምታ አፍሪቃም ውስጥ እየታየ ነው። ሳውዲ አፍሪቃውያት ሀገራት ከካታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጤኑት እና በካታር ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንዲደግፉ ማሳሰቢያ ሰጥታለች። የሳውዲን ጥያቄ ሁሉም አልተቀበሉትም። ይህም ከሳውዲ ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ ውጥረት መፍጠሩ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/2jEP3
Infografik Golfkrise in Afrika DEU

«የዐረባውያት ሀገራት ውዝግብ የአፍሪቃ ሀገራትን አዳጋች ምርጫ ላይ ጥሏቸዋል።»

ሳውዲ ዐረቢያ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤሚሬቶች፣ ግብፅ እና  ባህሬን ባለፈው ሰኔ ወር  ከካታር ጋር ዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸውን አቋርጠው፣ የሚያዋስናቸውን የጋራ ድንበርም መዝጋታቸው ይታወሳል። የካታር መንግሥት  ሽብርተኝነትን ይደግፋል በሚል ወቀሳም በዚችው ሀገር ላይ ማዕቀብ እና እገዳ ጥለዋል።  ካታር ከሙስሊም ወንድማማች ማህበር ጋር ግንኙነቷን እንድታቋርጥ እና በሀገሯ የሚገኘውን የቱርክ ጦር ሰፈርን፣ እንዲሁም፣ የዜና ማሰራጪያ ድርጅት፣ አል ጀዚራንም እንድትዘጋ  ጠይቀዋል። የካታር ኤሚር ሼኽ ታሚም ቢን ሀሚድ ኧል ታኒ  ይህ የሀገራቸውን የግዛት ሉዓላዊነት የሚጋፋ ነው በሚል ጥያቄውን አጣጥለውታል። የባህረ ሠላጤ ሀገራት ውዝግብን ተከትሎ አፍሪቃውያት ሀገራት ሞሪታንያ፣ ጋቦ፣ ኒዠር፣ ኮሞሮስ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊላንድ፣ ቻድ እና ሴኔጋል አንድም ዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል ወይም ወደ ዝቅተኛ ደረጃ አውርደዋል። 
ካታር እና ሌሎቹ በነዳጅ ዘይት ሀብት የበለጸጉት የባህረ ሠላጤው ሀገራት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ተጽዕኗቸውን ለማስፋት ሲጥሩ ታይቷል። ይኸው ሙከራቸው የጦር ሰፈሮች ማቋቋም፣ የወደቦች አስተዳደርን መረከብ እና ለወዳጅ ሀገራትም የውጭ ርዳታ መስጠት በያዙበት በአፍሪቃ ቀንድ በተለይ ጎልቷል። በተቀናቃኞቹ ዐረባውያት ሀገራት መካከል ተጽዕኖ የማጠናከር ፉክክሩም የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራትን አዳጋች ምርጫ ላይ እንደጣላቸው የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። ለምሳሌ ፣ ሶማልያ  እስካሁን ከካታር ጋር እንደወትሮው ጥሩ ግንኙነት አላት። ሳውዲ ዐረቢያ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤሚሬቶች፣ ግብፅ እና  ባህሬን ግን በሞቃዲሾ የሚገኘው የሶማልያ መንግሥት ይህንኑ ግንኙነቱን እንዲያቋርጥ ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ፣ በአምስቱ ዐረባውያት ሀገራት መካከል ከተፈጠረው ቀውስ ራሷን በማራቅ ገለልተኛ አቋም እንደያዘች የምትገኘው ሶማልያ ለአራቱ ዐረባውያት ግፊት ለመንበርከክ እንደማትፈልግ ግልጽ አድርጋለች፣ በዚህ ፈንታ  የሶማልያ ፕሬዚደንት መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ ቀውሱ የሚመለከታቸው አምስቱ ሀገራት ለውዝግባቸው በድርድር መፍትሔ እንዲፈልጉልት ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህ አልፈውም፣ ምንም እንኳን እነ ሳውዲ ዐረቢያን ቢያስቆጣም፣ የካታር አይሮፕላን በሶማልያ የአየር ክልል እንዲበር ፈቃድ ሰጥተዋል። እነ ሳውዲ ይህንኑ የሶማልያ ርዕሰ ብሔር ርምጃ በካታር ላይ የጣሉትን ማዕቀብ የሚያዳክም አድርገው ተመልክተውታል።  
እንግዲህ፣ በተቀናቃን ዐረባውያት ሀገራት መካከል ሁኔታዎች ይህን በመሰሉበት ባሁኑ ጊዜ ነው የሶማልያ ገለልተኛ አቋም ፈተና ላይ የወደቀው። ሶማልያ እስከ አሁን ድረስ ከሳውዲ ዐረቢያ ጋር መልካሙ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ ዐረባዊቱ ሀገር ትልቋ የንግድ አጋሯ ናት። ከዚህ በተጨማሪም፣ ሳውዲ ዐረቢያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤሚሬቶች ለሶማልያ ዋነኛ የገንዘብ ርዳታ ሰጪ ሀገራት ናቸው። የሶማልያ መንግሥት አሁን በካታር ላይ በተጣለው ማዕቀብ ላይ ተሳታፊ ከሆነም ተጨማሪ 68 ሚልዮን ዩሮ እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል።   ያም ቢሆን ግን፣ የሶማልያ ፕሬዚደንት መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ ከካታር ጎን መቆማቸውን ለመቀጠል ወስነዋል። ለዚሁ የሶማልያ ፕሬዚደንት ውሳኔ  እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል አንድ ጉዳይ አለ ብለው እንደሚያምኑ ዶይቸ ቤለ የአማርኛው ክፍል ያነጋገራቸው ሶማልያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ሙሄዲን አህመድ ሮብሌ ጠቁመዋል። 

Qatar Airways
ምስል picture alliance/dpa/epa/Stringer

« የሶማልያ ፕሬዚደንት መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ ሁሌም ካታርን ይደግፋሉ፣ ምክንያቱም የፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዘመቻ ወጪን የሸፈነችላቸው ካታር ነበረች፣ የሶማልያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እያንዳንዱ እጩ ለሀገሪቱ ሕዝብ ተወካዮች፣ ብሎም፣ ለላዕላይ እና ታህታይ ምክር ቤት በሚሰጠው የገንዘብ መጠን ነው የሚወሰነው። እና ካታር ባትረዳቸው ኖሮ መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ የሶማልያ ርዕሰ ብሔር ባልሆኑም ነበር። የማሸነፍ እድላቸው በጣም ዝቅተኛ በበረበት እና ማንም ያሸንፋሉ ብሎ ባልጠበቃቸው ሰዓት ካታር ስለረዳቻቸው ይህችኑ የባህረ ሰላጤ ሀገር ባለውለታቸው አድርገው ይመለከቱዋታል። መሀመድ አብዱላሂ መሀመድን በመጀመሪያ ከካታር ጋር ያገናኙዋቸው የፕሬዚደንቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፕሬዚደንቱ ገለልተኛ አቋም እንደያዙ እንዲቆዩ አግባብተዋቸዋል።  »
የተባበሩት ዐረብ ኤሚሬቶች በተለይ፣ በሰሜን ምስራቃዊ ሶማልያ ሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር ባቋቋመችው ፑንትላንድ እና ሶማልያ እንደ ግዛቷ በምትመለከታት ነፃ መንግሥት ባወጀችው ሶማሊላንድ ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሯ ሶማልያን አስቆጥቷታል።  የተባበሩት ዐረብ ኤሚሬቶች በዚያ ወደብ እየገነባች ሲሆን፣ የጦር ሰፈርም የመትከል ፍላጎት አላት። የሶማሊላንድ መንግሥት እና የፑንትላንድ አስተዳደር እንደወደፊት የገንዘብ ርዳታ ሰጪ ከሚመለከቱዋት ሳውዲ ዐረቢያ ጋር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ይፈልጋሉ።  እርግጥ ይህ ፖለቲካ ጨዋታ ፕሬዚደንቱን አላስደሰተም፣ ይሁንና፣ ብቻቸውን ውሳኔ መውሰድ አይኖርባቸውም፣ ይህ ዓይነቱ የተናጠል አካሄድ በአካባቢው የፖለቲካ አለመረጋጋት  ሊፈጥር ይችላልና።
« የሶማልያ ፌዴራል መንግሥት ገለልተኛ አቋም የመያዝ ውሳኔውን ከመድረሱ በፊት ከአካባቢው መንግሥታት ጋር አለመምከሩ ትልቅ ስህተት የሰራ ይመስለኛል። ምክንያቱም እነዚህ ወገኖች ከካታር ይበልጥ ከሳውዲ ዐረቢያ እና ከተባበሩት ዐረብ ኤሚሬቶች ጋር ጠንካራ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም አላቸው። »
የዐረባውያቱን ሀገራት ውዝግብ ተከትሎባለፈው ሰኔ ወር  እልባት ያላገኘው በኤርትራ እና ጅቡቲ መካከል የተፈጠረው የድንበር ውዝግብ እንደገና የተቀሰቀሰበት ድርጊት በአፍሪቃ ቀንድ ውጥረቱን አካሮዋል። እንደሚታወቀው ካታር ላለፉት ሰባት ዓመታት ሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን በአወዛጋቢው ድንበር አሰማርታ ነበር። ከባህረ ሠላጤው ቀውስን ተከትሎ ካታር 450 ሰላም አስከባሪዎቿን ከዚሁ ድንበር አካባቢ በማስወጣት በኤርትራ እና ጅቡቲ መካከል ይዛው የቆየችውን የሸምጋይነት ሚና አብቅታለች። ይህን ከደረገች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኤርትራ ሰው የማይኖርበትን ከጅቡቲ በስተሰሜን ምሥራቅ የሚገኘውን አወዛጋቢውን የድንበር አካባቢ ይዛለች ተብሏል። ይህም በሀገራቱ መካካከል ውጥረቱን ይበልጡን ሊያካርረው እንደሚችል ሮቤሌ ገምተዋል። ምክንያቱም  በአፍሪቃው ቀንድ ካሉት ሀገራት መካከል ኤርትራ እና ጅቡቲ ከሳውዲ እና ከተባበሩት ዐረብ ኤሚሬቶች ደግፈዋል፣ ሶማልያ እና ኢትዮጵያ ደግሞ ገለልተኛ አቋም ይዘዋል። እርግጥ፣ በአካባቢው በሚታየው ፖለቲካ ጨዋታ ላይ ሳውዲ እና ኤሚሬቶች ከካታር የተሻለ ጠንካራ አቋም ቢኖራቸውም፣ እንደ ሮቤል አስተያየት፣ ካታር ከሶማልያ ጋር ጥሩ ግንኙነት በቀጠለችው ጥሩ ግንኙነት ታካክሰዋልች። 

Somalia | Mohamed Abdullahi Farmajo
ምስል REUTERS/F. Omar

የባህረ ሰላጤው ቀውስ ምዕራብ አፍሪቃንም ነክቷል።  የሳህል አካባቢ ሀገራት አቋም እንዲይዙ ጠይቃለች። ቻድ ሳውዲን በመደገፍ፣ በመዲናዋ የሚገኘው የካታር ኤምባሲ እና ሰራተኞቼ ሀገሩን በአስር ቀን ለቀው እንዲወጡ አዛለች፣  የራሷን ዲፕሎማቶችም ከካታር መልሳለች። ቻድ መረጋጋቷን ጠብቆ ለማቆየቱ ተግባር ቅድሚያ እንደሰጠች በበርሊን የሚገኘው የላይብኒትስ ፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ አብዱላይ ሱናይ ገልጸዋል። 
«  ቻድ በሀገሯ አለመረጋጋት እንዳይፈጠር ሰግታለች። ይህ ስጋቷ ካለ ምክንያት የመጣ አይደለም። እንደምናውቀው፣ በሊቢያ የሚንቀሳቀሱት ፅንፈኞቹ ሙስሊሞች የሚረዱት በካታር ነው። ቻድ ከነዚህ ቡድኖች ጥቃት ሊሰነዘር የሚችልበት  ወይም ከነዚሁ ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው ዜጎችዋ ዓመፅ የሚያነሱበት ስጋት ተደቅኖባታል። እና ውስጣዊ መረጋጋትዋን ለመጠበቅ የምትፈልገው ቻድ በማሊ እየሆነ ያለው ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መገኘት አትፈልግም። »
በቻድ አንፃር አምባሳደሯን ከዶሀ በመመለስ ከካታር ጋር የብዙ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረውን መልካሙን ግኝኙነት ወደ ዝቅተኛ ደረጃ አውርዳ የነበረችው ሴኔጋል አሁን እንደገና ዲፕሎማቲክ ግንኙነት አድሳለች። በዚህ ርምጃዋ የባህረ ሠላጤው ሀገራት ውዝግባቸውን መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ለማበረታት መፈለጓን ገልጻለች። የሴኔጋል ጉዳይ ለየት ያለ ነው የሚሉት ተንታኙ ሱናይ  ይህችው ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር በሀገሯ ከሚንቀሳቀሰው የካታር ባለሀብቶች ገንዘብም ብዙ ትርፍ ታገኛለች። በዚህም የተነሳ የባህረ ሠላጤውን ውዝግብ በተመለከተ ሴኔጋል በያዘችው አቋም በመጠቀሙ እና ጥቅሟንም በማስጠበቁ ረገድ ከሌሎች አፍሪቃውያት ሀገራት የተሻለ ቦታ ላይ ትገኛለች። በአንፃሯ የሳህል አካባቢ ሀገራት ከሳውዲ ዐረቢያ ጋር ግንኙነታቸውን ቢያቋርጡ ብዙ ጥቅም ሊያጡ ይችላሉ። ስለሆነም ፣ ከካታር ጋር ሳይሆን፣ ከብዙ አሰርተ ዓመታት ወዲህ ከሳውዲ ዐረቢያ ጋር የሚያደርጉትን ትብብር ለመቀጠል ወስነዋል። 

Mali Soldaten
የማሊ ወታደር በሰሜን ጋው ምስል picture-alliance/AP Photo

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ