1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

የርቀት ትምህርት ተከታታዮች እና ቅሬታቸው

ዓርብ፣ ግንቦት 18 2009

አንዳንድ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንደገለፁልን ትምህርታቸውን በአግባቡ በጊዜው ሊያጠናቅቁ አልቻሉም። ምክንያቱን ለማወቅ የወጣቶች ዓለም አዘጋጅ ልደት አበበ በዛሬው ጥንቅሯ ተማሪዎቹን እና የሚመለከተውን አካል አነጋግራለች።

https://p.dw.com/p/2db0K
Symbolbild Home Office
ምስል picture-alliance/dpa/M. Wuestenhagen

የርቀት ትምህርት ተከታታዮች እና ቅሬታቸው

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች አስተምሮ በየዓመቱ ያስመርቃል። ከነዚህ ተማሪዎች መካከል የርቀት ትምህርት ተከታታዮች ይገኙባቸዋል። አላማቸው ከስራ ጎን ለጎን እና ቃሉ እንደሚለው የግድ በየዕለቱ በከፍተኛው ተቋም  በአካል ሳይገኙ ትምህርታቸውን በርቀት ተከታትለው መመረቅ እና የግል የትምህርት ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ ነው። ይሁንና የዚህ የርቀት ትምህርት ተከታታይ የሆኑ ሶስት ተማሪዎች እንደገለፁልን ከተቋሙ ችግር ገጥሟቸዋል።
በባህርዳር ዩንቨርስቲ የርቀት ትምህርት ተከታታይ የሆነው መሀመድ የፊዚክስ ተማሪ ሲሆን የመጨረሻውን ፈተና የወሰደው ባለፈው ጥር ወር ነው። ይሁንና እስካሁን ውጤቱን አላወቀም። መሀመድ እንደሚለው ተቋሙ ውጤታቸውን በወቅቱ እንዲያሳውቃቸው እሱ እና ችግሩ የገጠማቸው ተማሪዎች በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። እሱም ይሁን ሌሎች ተማሪዎች በየጊዜው በአካል ተገኝተው ቅሬታቸውን ለተቋሙ ማሰማት አልቻሉም። ምክንያቱም የሚኖሩት 300 እና 400 ኪሎ ሜትር ርቀው በሚገኙት የወልድያ እና ሰቆጣ አካባቢዎች ነው። ስለሆነም መሀመድ ጥያቄውን ያቀረበው ዩኒቨርስቲው ወደነዚህ አካባቢዎች ተወካይ ሲልክ ነው።
እንደ መሀመድ መፍትሄ ሳታገኝ የተቀመጠችው ሌላዋ የርቀት ተማሪ ሰናይት ናት። «መመረቅ የነበረብኝ ከአንድ አመት በፊት ነበር» ትላለች። ሰናይት ስለደረሰባት ችግርም በተደጋጋሚ በግቢው ተገኝታ ለዩኒቨርስቲው አቤቱታ አቅርባለች። ያገኘችው ምላሽ ግን አስደሳች አልነበረም።
የርቀት ተማሪዎቹ እንደገለፁልን፤ በኢንተርኔት የሚለቀቁት እና በወረቀት ታትመው የሚለጠፉት የፈተና ውጤቶች የማይጣጣሙበት አጋጣሚም አለ።የርቀት ተማሪዎቹ ለትምህርት የሚከፍሉት ገንዘብ እንደእየትምህርት ክፍሉ እንደሚለያይ መሀመድ ገልጾልናል። በሴሚስተር በአማካይ  1000 ብር ድረስም ይከፍላሉ።  ሌላው የመሀመድ ሞክሼ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተማሪ ነው። እሱም እስካሁን መመረቅ ነበረበት። ይሁንና ውጤቱን እስካሁን አላወቀም።
በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የርቀት ትምህርት ላይ ያጋጥማሉ በሚል ተማሪዎቹ ስላቀረቧቸው ቅሬታዎች የዩኒቨርሲቲውን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ማተሬን አነጋግረን ምላሽ አግኝተናል።
የዶክተር ማተሬን ምላሽ እና ሶስቱ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የርቀት ተማሪዎች ያነሱዋቸውን ቅሬታዎች ከዚህ በታች በድምፅ መከታተል ይችላሉ።
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ

Tafel mit Bachelor
ምስል Fotolia/m.schuckart