1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባልካን መስመር መዘጋት ያስከተለው ስጋት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 4 2008

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ስደተኞች በብዛት ወደ አውሮጳ የገቡበት የባልክን መስመር መዘጋት በሜዲቴራንያን ባህር በኩል አውሮጳ ለመምጣት የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል የሚል ስጋት አለ ። በዚህ የተነሳ አንዳንድ የኢጣልያ ጎረቤቶች የድንበር ቁጥጥሩን ለማጥበቅ አቅደዋል ።

https://p.dw.com/p/1ITTt
Flüchtlinge auf Mittelmeer
ምስል picture-alliance/Bundeswehr/S. Hoder

[No title]

ካለፈው ዓመት አንስቶ የአውሮጳ ህብረት አብይ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ የዘለቀው የስደተኞች ቀውስ ለጊዜው ጋብ ያለ ቢመስልም አሁንም በርካታ ችግሮች መከሰታቸው አልቀረም ። ስደተኞች በብዛት ወደ ሰሜን አውሮጳ ሃገራት የተሻገሩበት የባልካን ሃገራት መስመር ሲዘጋ መንገድ ላይ የነበሩ ስደተኞች ወዳሰቡባቸው ሃገራት ማለፍ ሳይችሉ በደረሱበት እንዲቆዩ መገደዳቸው አንዱ ጎልቶ የሚታይ ችግር ነው ። በአሁኑ ጊዜ ግሪክ ውስጥ ብቻ ወደ 50 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ። ከመካከላቸው ወደ ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት የመሻገር እቅዳቸው የተጨናገፈባቸው ከየካቲት አንስቶ መቄዶንያ ድንበር ላይ ባለችው በግሪክዋ ኢዶሜኒ የሚገኙት ቁጥራቸው ወደ 11ሺህ የሚጠጋ ስደተኞች ያሉበት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ተጠቃሽ ነው ።የባልካን መስመር መዘጋት ካስከተለው ከዚህን መሰል መፍትሄ ያልተገኘለት ችግር በተጨማሪ ፣ወደ አውሮጳ ለመምጣት የሚፈልጉ ስደተኞች ፊታቸውን ወደ አደገኛ የጉዞ መስመሮች እንዲያዞሩ ያደርጋል የሚል ስጋትም አስከትሏል ። የአውሮጳ ህብረት እና ቱርክ በባልካን ሃገራት በኩል ወደ አውሮጳ የሚገባውን ስደተኛ ለማስቆም ስምምነት ላይ ከደረሱ ወዲህ በተለይ በሜዲቴራንያን ባህር አድርገው ከሊቢያ ወደ ኢጣልያ ደሴቶች የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር ይጨምራል የሚል ግምት አለ ። በዚህ መስመር ኢጣልያ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁት ስደተኞች ቁጥር ከአምናው በእጥፍ የጨመረ እንደሚሆንና እስከ 300 ሺህ ሊደርስ እንደሚችልም ይነገራል ። በዚህ ስጋትም የኢጣልያ ጎረቤት ኦስትሪያ ከወዲሁ የድንበር ቁጥጥርዋን ለማጥበቅ አቅዳለች ።በአደገኛ የባህር ጉዞ የሚሰደዱ ወጣቶችን የሚረዳው መቀመጫውን ኢጣልያ ያደረገው ኤጀንስያ አበሻ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት መስራችና ሃላፊ አባ ሙሴ ዘርዓይ ስደተኞች አደገኛውን የባህር ጉዞ እንዲመርጡ የሚገደዱት የተሻለ ምርጫ በማጣታቸው ነው ይላሉ ።ከዚሁ ጋርም የወቅቱ የአካባቢው የአየር ንብረት እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ መሆኑንም ያስረዳሉ ።በቱርክ በኩል ወደ ግሪክ ተሻግረው በባልካን አገራት አቆራርጠው ወደ ሰሜን አውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞችን ጉዞ ለማስቆም የአውሮጳ ህብረትና ቱርክ ባለፈው መጋቢት መጀመሪያ ላይ በደረሱበት ስምምነት መሠረት ግሪክ ውስጥ ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ወይም ደግሞ የጥገኝነት ማመልከቻ ያላስገቡ ስደተኞችን በግዳጅ ወደ ቱርክ መመለስ ተጀምሯል ። በምትኩ ቱርክ የተጠለሉ የሶሪያ ስደተኞች ወደ ተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት እየተወሰዱ ነው ። አባ ሙሴ ለቱርክ ጠቀም ያለ ገንዘብ ያሰጠውን ይህን የአውሮጳ ህብረትና የቱርክ ስምምነት ስደተኞችን ለአደገኛ ጉዞ የሚዳርግ ብቻ ሳይሆን መብታቸውንም የሚጋፋ ሲሉ ኮንነውታል ።አባ ሙሴ እንደሚሉት ግሪክ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞችም ለዚህ ዓይነቱ ችግር ከታጋለጡት መካከል ይገኙበታል ። በስምምነቱ መሠረት ወደ ቱርክ የሚመለሱ ስደተኞች ጉዳያቸው እየተጣራ በህጋዊ መንገድ ወደ አውሮጳ እዲገቡ ይደረጋል ቢባልም ይህ በትክክል ተግባራዊ መሆኑን ይጠራጠራሉ ።አባ ሙሴ ችግሩን ለማቃለል የአውሮጳ ሃገራት ካናዳን የመሳሰሉ ሃገራት እንደሚያደርጉት ስደተኞችን በሰፈራ መርሃ ግብሮች እንዲወስዱ ይመክራሉ ።

Italien Flüchtlinge Rettung Mittelmeer
ምስል picture alliance/dpa/C. Fusco
Italien Flüchtlinge Rettung Mittelmeer
ምስል picture-alliance/dpa

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ