1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባልካን ጎርፍ ያስከተለው መዘዝ

ረቡዕ፣ ግንቦት 13 2006

በባልካን አካባቢ ሃገራት ካለፈው ቅዳሜ አንስቶ በተከሰተ የጎርፍ መጥለቅለቅ የሟቾቹ ቁጥር እየጨመረ ነው። አንዳንድ ድርጅቶች ተጨማሪ የውሃ ሙላት አደጋ ሊከሰት እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው።

https://p.dw.com/p/1C3TF
ምስል picture-alliance/AA

በባልካን አካባቢ በሚገኙ ሃገራት በቦስንያ፣ ክሮሺያ እና ሰርቢያ ውስጥ የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ እስከ አሁን ድረስ ከ40 የማያንሱ ሰዎችን ወስዷል። በተለይ ሳቫ በሚባለው ወንዝ አቅራቢያ ያለው ሰሜናዊ የቦስኒያ አካባቢ ሰብረው በወጡ ወንዞች ተጥለቅልቋል። ሕንፃዎች ጎርፉ ባመጣው ማጥ እና የውሃ ሙላት ተውጠው ጣሪያዎቻቸው ብቻ ነው የሚታዩት። ቁጥሩ ከአንድ ሚሊዮን የሚልቅ ሕዝብ አደጋ ተጋርጦበታል። የሰርቢያ ነዋሪዎች ሌላ ተጨማሪ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ሊከሰትባቸው እንደሚችል ተተንብዮዋል። ጎርፉን ለመከላከል በሚልም ሳባች፣ ሚትሮቪቻ፣ ቤልግሬድ እና ኦብሬኖቫች በተባሉ አካባቢዎች በሚሊዮናት የሚቆጠሩ በአሸዋ የተሞሉ ከረጢቶች ተከምረዋል።

ሰኞ ማታ ከ25,000 የኦብሬኖቫች ነዋሪዎች 7000 ያህሉ ከተማዋን እንዲለቁ ተደርገዋል። ሠርቢያ መዲናም ጭንቅ ውስጥ ሆና ነዋሪዎቿ ከሠዓት ጋር ሩጫ ይዘዋል። ከ120 ዓመታት ወዲህ አደገኛው በተባለለት የባልካን የጎርፍ አደጋ ከከተሞች ባሻገር የገጠር አካባቢዎችም ከፍተኛ ጉዳት እንደተከሰተባቸው ተነግሯል። የሠብዓዊ ርዳታ ድርጅት ውስጥ የሚያገለግሉት ፍሪትስ ኖይበርግ፤

የባልካን ሃገራት የጎርፍ መጥለቅለቅ
የባልካን ሃገራት የጎርፍ መጥለቅለቅምስል Reuters/Dado Ruvic

«በጎርፉ የተነሳ ገበሬዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድተዋል። መኸራቸውን በሚቀጥሉት ሁለት ሣምንታት መሰብሰብ ይጠበቅባቸዋል። ዝናቡ መውረድ ከጀመረ አራት ሣምንታትን አስቆጥሯል፤ እናም በሚቀጥሉት ሣምንታት ካላባራ ምርት የሚባል ነገር አይኖርም። የቦስኒያ ከፍተኛ ገቢዋ ግብርና ነው። በእዚህ ዓመት የሚበቅል ነገር ከሌለ የሕዝቡ ቀለብ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ይቻላል።»

ጎርፉ አግበስብሶ ካመጣቸው የቆሻሻ ቁልሎች ባሻገር ውሃው በነዳጅ ዝቃጭ ተበክሏል። የውሃው መበከል እንደ ታይፎይድ እና የጉበት መመረዝ ዓይነት በሽታዎችን ሊያስከትል ይችላልም ተብሏል። ከእዚያ ባሻገር በሺህዎች የሚቆጠሩ ላሞች፣ አሣሞች፣ በጎች፣ ውሾች እንዲሁም ሌሎች እንስሳት በመሞታቸው ወረርሺኝ ሊከሰት ይችላል ሲሉም ተንታኞች ፍራቻቸውን ገልጠዋል። በአካባቢው የሚገኝ «ሄልፕ»የተባለው የሠብዓዊ ርዳታ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ክላውስ ሞክ ፍራቻቸውን እንዲህ ይገልጣሉ።

«የወረርሺኝ አደጋ ተደቅኗል። ምክንያቱም በርካታ እንስሳት ሞተዋል። ውሃው እየቀነሰ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ጊዜ የዓየር ሙቀቱ እየጨመረ ነው። እናም እነዚህ ነገሮች ወረርሽኝ እንዲቀሰቀስ ሰበቦች ናቸው።»

ከወረርሽኙ ባሻገር ሕዝቡ ሌላ አደገኛ ነገርም ተጋርጦበታል። በሺህዎች የሚቆጠሩ መሬት ውስጥ የተቀበሩ ፈንጂዎች ስጋት። እጎአ በ1990ዎቹ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ተቀብረው የቀሩ ፈንጂዎችን ጎርፉ አንድም እያጠበ ከመሬት በላይ እንዲያገጡ ሲያደርግ፤ በሌላ በኩል በርካታ ፈንጂዎችን ከነበሩበት ቦታ ወደ ተለያዩ ቦታዎች አንቀሳቅሷቸዋል። ይኽም ፈንጂዎቹ በካርታ ላይ ይገኙባቸው የነበሩ ጥቁምታዎች የተዛቡ እንዲሆኑ አድርጓል። ፍሪት ኖይበርግ፤

የሰርቢያ የጎርፍ መጥለቅለቅ ከሔሊኮፕተር ሲቃኝ
የሰርቢያ የጎርፍ መጥለቅለቅ ከሔሊኮፕተር ሲቃኝምስል picture-alliance/dpa

«ይኽ ማለት የፈንጂ ቃጣና ተብለው ካርታ ላይ ምልክት የተደረገባቸው መስኮች አሁን ተዛብተዋል። ምክንያቱም ጎርፉ ፈንጂዎቹን ከነበሩበት ቦታ አንቀሳቅሷቸዋል። እናም ሰዉ መንገድ ላይ ሲሄድ ፈንጂ ላይ ላለመቆም ጥንቃቄ ማድረግ አለበት።»

ፈንጂዎቹ ለጎረቤት ሃገራትም ስጋት መደቀናቸው አልቀረም። ከቦስኒያ የሚነሱ ወንዞች ፈንጂዎቹን ወደ ሌሎች ደቡብ አውሮጳ ሃገራት ይዘው እንዳይሄዱ አስግቷል። የፈንጂዎቹ ማቀጣጠያ በጎርፉ የተነሳ ርጥበት ስላጋጠማቸውም ባልተጠበቀ መልኩ ሊፈነዱ ይችሉ ይሆናል ተብሏል።

የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫዎችንም በጎርፉ የተወሰዱ ፈንጂዎች እንዳይመቱ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል። የጎርፉ አደጋ ለተጋረጠባቸው ነዋሪዎች የርዳታ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን፤ የጀርመን የርዳታ ድርጅቶች የቴክኒክ እገዛ እያደረጉ እንደሚገኙ ተጠቅሷል። ጀርመን እስካሁን ለጉዳቱ ሰለቦች የሚውል በሚል 350,000 ዩሮ ርዳታ እንደሰጠች ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ