1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦማን የሚገኙ የቤት ሠራተኞች የከፋ ችግር፤

ዓርብ፣ ሐምሌ 8 2008

ኦማን ዉስጥ በቤት ሠራተኝነት ሥራ የተሰማሩ የዉጭ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የመብት ጥሰት እንደሚፈፀም ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ሂዉመን ራይትስ ዎች አመለከተ። በደሉን ለኦማን መንግሥት በዝርዝር ያመለከተዉ ይህ ድርጅት፤ መንግሥት መብታቸዉን ለማስከበር ተገበዉን ርምጃ ባለመዉሰዱም ወቅሷል።

https://p.dw.com/p/1JPi9
Arbeitsbedingungen für Frauen Ethiopische Frau im Libanon bei der Arbeit
ምስል AP

[No title]

በየአረብ ሃገራቱ በቤት ሠራተኞች ላይ የሚደርሰዉን በደል ይፋ ማዉጣት አንዱ ሥራዉ የመሆነዉ ሂዉማን ራይትስ ዎች፤ ሀገራት ዜጎቻቸዉ ኦማንን ወደመሰሉ ሃገራት ከመሄዳቸዉ አስቀድመዉ ተገቢዉ መረጃም መስጠትም ሆነ ጥንቃቄ ካላደረጉ፤ እዚያ ከገቡ በኋላ የሚደርስባቸዉን ማስቆም እንደሚከብድ ነዉ የገለጸዉ።

«130 ሺህ ሴቶች ኦማን ዉስጥ በስደተኛ የቤት ዉስጥ ሠራተኝነት እንደሚገኙ እንገምታለን። በየቤቱም እነዚህ ሴቶች አብዛኛዉን ጊዜ የሚያዙት በመጥፎ ሁኔታ ነዉ፤ ይደበደባሉ፤ ይራባሉ፤ በቀን ለ21 ሰዓት እንዲሠሩ ይገደዳሉ፤ እናም ይዞታቸዉ በእርግጥ አስከፊ ነዉ። ከኦማን ዜጎች አንድ አራተኛ የሚሆነዉ የቤት ሠራተኛ እንዳለዉ ይገመታል። እናም ምናልባትም ቁጥራቸዉ ሊጨምር ይችላል።»

ይላሉ በመካከለኛዉ ምሥራቅ የሂዉመን ራይትስ ዎች የኮሙኒኬሽና የመብት ጉዳዮች ተመልካች ዳይሬክተር አህመድ ቤንቸምሲ። ድርጅታቸዉ ይፋ ባደረገዉ ባለ 68 ገፅ ዘገባ ኦማን ዉስጥ በቤት ሠራተኝነት የተሠማሩ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ካለባቸዉ የሥራ ጫና በተጨማሪ በቀጣሪዎቻቸዉ የወሲብ ጥቃት እንደሚፈፀምባቸዉ እና በሕገወጥ ዝዉዝር በባርነት እንደሚሸጡም ዘርዝሯል። አህመድ ቤንቸምሲ ቀጠሉ፤

Human Rights Watch Logo Flash-Galerie
ምስል Human Rights Watch

«የሚፈፀምባቸዉ ጥቃት የተለያየ ነዉ። ካፋላ በሚባለዉ ሰዎችን በኃላፊነት የማምጣት ስርዓት መሆኑ ነዉ፣ በኦማንም ሆነ ባጠቃላይ በባህረ ሰላጤዉ በሚገኙ ሃገራት የሚሠራበት ማለት ነዉ፤ እነዚህ ከሌላ ሃገራት የመጡ የቤት ዉስጥ ሠራተኞች ከቀጣሪዎቻቸዉም ሆነ ካስመጧቸዉ አካላት ዉጭ መንቀሳቀስ አይችሉም። ይህ ማለትም ሥራም ሆነ አሠሪያቸዉን መቀየርም አይችሉም፤ ሌላዉ ቀርቶ ቀጣሪዎቻቸዉ ካልፈቀዱ ከኦማን መዉጣት አይችሉም። ምክንያቱም አብዛኛዉን ጊዜ የጉዞ ሰነዳቸዉን በስልት ወስደዉ የሚይዙት እነሱ ስለሆኑ ማለት ነዉ።»

እንደሂዉመን ራይትስ ዎች ዘገባ፤ ኦማን ዉስጥ በቤት ዉስጥ ሠራተኝነት ከተሰማሩት ከመቶሺ በላይ የሚገመቱ ሴቶች መካከል አብዛኞቹ ከፊሊፒንስ፣ ከኢንዶኔዢያ፣ ከሕንድ፣ ከባንግላዴሽ፣ ከስሪ ላንካ፣ ከኔፓል እንዲሁም ከኢትዮጵያ የሄዱ ናቸዉ። ድርጅቱ 59ኙን በማነጋገር የሰበሰበዉ መረጃ እንደሚያመለክተዉ የግዳጅ ሥራ ከመሥራታቸዉ በተጨማሪ ልቅ በሆነዉ የሀገሪቱ ድንበር በመጠቀም ከተባበረዉ አረብ ኤሜሬት በሕገወጥ መንገድ ተገዝተዉ ያለ ዕረፍት ለሚያሠሯቸዉ ሰዎች ይሸጣሉ። አስማ ኬ በሚል ስሟ የተጠቀሰዉ የባንግላዴሽ ዜጋ ወደኤሜሬትስ ለሥራ ብትሄድም ሥራ እና ሠራተኛ አገናኞቹ ለአንድ ሰዉ ሸጠዋት ገዢዋ ፓስፖርቷን ቀምቶ ኦማን ይወስዳታል። ከዚያ በየቀኑ ለ21 ሰዓታት ያለ ደሞዝ 15 አባላት ባሉት ቤተሰብ ዉስጥ ያለ ዕረፍት እንድትሠራ ትገደዳለች። ምግብ የማይሰጣት ይህች መከረኛ በቃል ከሚደርስባት ጥቃት በተጨማሪ ለወሲብ ጥቃት መዳረጓን ዘርዝራለች። ከተለያዩ ሃገራት ተሰደዉ ኦማን የሚገኙት የቤት ሠራተኞች አያያዛቸዉ ቢመሳሰልም የሚያገኙት ክፍያ ይለያያል ይላሉ አህመድ ቤንቸምሲ፤

Logo von Human Rights Watch der UNO

«የበርካታ ሃገራት ዜጎች ኦማን ዉስጥ ይገኛሉ። አያያዛቸዉን ስንመለከት ብዙም ልዩነት ባይኖረዉም፤ በደሞዝ አከፋፈል ይለያያሉ። ነገሩ ግራ የሚያጋባ ቢመስልም ክፍያቸዉ በዜግነታቸዉ ላይ የተመሠረተ ነዉ። አብዛኞቹ የቤት ሠራተኞችን የሚመጡባቸዉ ሃገራትየለዜጎቻቸዉን መብት ለማስጠበቅ ቢያንስ ቢያንስ ሊከፈላቸዉ ይገባል የሚሉትን ክፍያ ወስነዋል። ለምሳሌ ለፊሊፒኖች በወር 400 ዶላር ነዉ፤ ለሲሪላንካ 220 ዶላር ነዉ፤ ለታንዚንያ ደግሞ 180 ዶላር ነዉ።»

ኦማንም በተለያዩ የአረብ ሃገራት ዉስጥ የቤት ሠራተኞች የሚደርስባቸዉን ስቃት የተከታተለዉ የኢንዶኔዥያ መንግሥት ዜጎቹ ወደዚያች ሃገር እንዳይሄዱ ከልክሏል። ሆኖም በሕገወጥ ሰዎችን ከሀገር ሀገር በሚያሸጋግሩት በኩል መጓዛቸዉ ስላልቀረ ለችግሩ መዳረጋቸዉ አልቀረም። በተለያዩ የአረብ ሃገራት በቤት ሠራተኝነት የሚገኙት ወገኖች የሚደርስባቸዉን የመብት ጥሰት ሂዉማን ራይትስ ዎች በተለያዩ ጊዜያት አደባባይ አዉጥቷል። በተቀጣሪዎቹ የሚደርስባቸዉን በደል ለፖሊስ ሲያመለክቱም መፍትሄ አያገኙም። አህመድ ባንቼምሲ በዚህ ረገድ በኦማን የሚታየዉ የከፋ እንደሆነ ነዉ የሚናገሩት።

«የካፋላ ሥርዓቱ በሌሎቹም የአረብ ሃገራት ያለ አሠራር በመሆኑ ብዙም ላይነፃፀር ይችላል። በተለያዩ የአረብ ሃገራት የቤት ሠራተኞቹ ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት ዓይነት በዝርዝር ተቀምጦ አልተመዘነም። ግን ደግሞ የፖሊስን አያያዝ እና የኦማንን የፍትህ ሥርዓት ስንመለከት በአንዳንድ ሁኔታዉ ከሌሎች ጎረቤት የባህረ ሰላጤዉ ሃገራት የከፋ ነዉ።»

የኦማንም ሆነ የሌሎች አረብ መንግሥታት የሠራተኛ መብት የሚከበርበት ሕግ እንዲኖራቸዉ እና የሚደርሰዉን ጥቃትም እንዲያስቆሙ ደጋግሞ ጠይቋል። ተጨባጭ መልስ ግን አላገኘም።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ