1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሪታንያ ሙስሊሞችና ISIS

ዓርብ፣ ነሐሴ 30 2006

የናኘዉን ፅንፈኛ ቡድንን የእሥልምና ሐይማኖት መሪዎች ሲቃወሙ፤ እርምጃዎቹን ሲያወግዙ የብሪታኒያ ሙስሊም መሪዎች የመጀመሪያዎቹ አይደሉም።የግብፁ ዓል-አዝሐር ዩኒቨኒርስቲ መሪዎች ISISን አዉግዘዉ ነበር።ከግብፆች በፊት የሳዑዲ አረቢያ የሐያማኖት አባቶችም ቡድኑን አዉግዘዉት ነበር።

https://p.dw.com/p/1D6n8
ምስል picture-alliance/AP Photo

የብሪታንያ ሙስሊም መሪዎች (ኢማሞች) የኢራቁን ፅንፈኛ ደፈጣ ተዋጊ ሚሊሺያ ቡድን (ISIS) የሚከተለዉን መርሕና የሚወስደዉን እርምጃ አወገዙ።የብሪታንያ የተለያዩ መስጂዶች ኢማሞች፤ የሙስሊም ማሕበራት መሪዎች በጋራ በሰጡት ፈትዋ እንዳሉት ISIS በሌላ ሐይማኖት ወይም የሐይማኖት ሐራጥቃ ተከታዮች ላይ የሚወስደዉ እርምጃ የእስልምና አስተምሕሮቱትን የሚቃረን አብሮ የመኖር ባሕልንም የሚያደፈርስ ነዉ።የብሪታንያ ሙስሊሞች ቡድኑን እዳይደግፉ ኢማሞቹና የማሕበር መሪዎቹ ጠይቀዋል።ኬርስተን ክኒፕ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

አራት ናቸዉ። የሌስተር እና የማንቸስተር ከተሞች ኢማሙል-ከቢር፤የሊዲስ መካሕ መስጊድ ኢማም፤የብሪታንያ ሙስሊሞች አንድነት ማሕበር ተባባሪ ሐላፊ እና የታላቋ ብሪታንያ የእሥልምና ጉዳይ ጥናት ተቋም ሐላፊ።አራቱ መንፈሳዊ መሪዎች በፅሁፍ ባወጡት ፈትዋ የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) የተሰኘዉን ቡድን «ፅንፈኛ ድርጅት እና ሐራጥቃ» ይሉታል።የቡድኑን ምግባር ደግሞ «የእሥልምና አስተምሕሮትን የሚቃረን» በማለት አዉግዘዉታል።

ፈትዋዉን ያረቀቁት በታላቅዋ ብሪታንያ የእሥልምና ጉዳዮች ጥናት ተቋም ዑስማ ሐሰን ፈትዋዉ ከመሰጠቱ በፊት እንደሚሉት ISIS የሚከተለዉ ርዕዮተ-ዓለም ሁከትን ቀስቃሽ ነዉ።

Islamischer Staat Propaganda
ምስል picture alliance/abaca

«ፖለቲካዊ-እስልምና ሊባል የሚችል፤ በሐይማኖት የተነቃቃ ርዕዮተ ዓለም ነዉ።እሥልምና ሲበዛ ወደ ፅንፍ የገፋ እና እላማዊ መንግሥት ለመገንባት ሁከትና የሐይል እርምጃን እንደ ተገቢ ሥልት የሚከተል ነዉ።»

የአራቱ መንፈሳዊ መሪዎች በሰጡት ፈትዋ «መርዛማ» ያሉትን የፅንፈኛዉን ቡድን አስተሳሰብ የብሪታንያ ሙስሊሞች መታጋል አለባቸዉ።ከዚሕ በተቃራኒዉ ቡድኑን መደገፍ ግፍ «ሐራም ነዉ።»

ISIS ክርስቲናኖችን፤ ሺኦችን፤የዚዲዎችን፤ጋዜጠኝችን በመደዳ መግደሉን የመንፈሳዊ መሪዎቹ የፈትዋ ፅሁፍ ይዘረዝራል።ቡድኑ የሚቃወሙትን ወገኖች ልጆችና ሴቶችን በባርነት እንደሚገዛ-ይጠቅሳል።እነዚሕና መሠል ቅርምጃዎች የእስልምና አስተምሕሮትን የሚቃረን፤የሰዉ ልጅ እኩልነትን የተደነገገበትን የዤኔቫ ሥምምነትንም የሚጥስ ነዉ።

የፈትዋዉ አርቃቂ ኡስማ ሐሰን እንደሚሉት ISIS እስልምናን ሽፋን አደረገ እንጂ ድርጊቱ የጨካኝ ፖለቲከኞች፤ እዉነኛ ግቡ ሥልጣን ነዉ።

«አንዳዴ ከዓል ቃኢዳ ጋር ይተባበራሉ።ሌላ ጊዜ ዓል ቃኢዳን ያወግዛሉ።ለምሳሌ የዉጪ ሐይላትንና የሺዓ ጦርን ለመዋጋት ሐይማኖታዊ ካልሆኑ ሐይላት ጋር ግንባር ይፈጥራሉ።ሥለዚሕ ሥልጣን ለመያዝ ፖለቲካን ከሐይማኖት ቀይጠዉ ይጠቀሙበታል።»

የኢራቅን ትላልቅ ከተሞች ሲቆጣጠር መጥፎ-ምግባር፤ ሥም ዝናዉ በዓለም የናኘዉን ፅንፈኛ ቡድንን የእሥልምና ሐይማኖት መሪዎች ሲቃወሙ፤ እርምጃዎቹን ሲያወግዙ የብሪታኒያ ሙስሊም መሪዎች የመጀመሪያዎቹ አይደሉም።የግብፁ ዓል-አዝሐር ዩኒቨኒርስቲ መሪዎች ISISን አዉግዘዉ ነበር።ከግብፆች በፊት የሳዑዲ አረቢያ የሐያማኖት አባቶችም ቡድኑን አዉግዘዉት ነበር።የቡድኑን እርምጃ ግን የገታዉ የለም።GIGA በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የጀርምን ጥናት ተቋም የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ አጥኚ ስቴፋን ሮሲኒ ISIS ለእስካሁኑ አይደለም ተጨማሪ ፈትዋም ቢሰጥ «ደንታዉ አይደለም» አይነት ባይ ናቸዉ።

«የእስላማዊ መንግሥት (ISIS) ተዋጊዎችና አባላት እንዲሕ አይነቱን ፈትዋ በጭራሽ አይቀበሉትም።በእነሱ አመለካከት «የእስላማዊ መንግሥት» ኸሊፋን የማይቀበል ሙስሊም በሙሉ ከሐይማኖቱ ያፈነገጠ ወይም መናፍቅ ነዉ።ይሕ ማለት ፈትዋዉን የሰጡትም መናፍቅ ናቸዉ።»

ፅንፈኛዉ ቡድን በሚቆጣጠራቸዉ አካባቢዎች ሁለኛዉ የኸሊፋ አስተዳደር ወይም መንግሥት የሚል ሥርዓት መመስረቱን አስታዉቋል።የመጀመሪያዉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ከ632 እስከ 661 ፀንቶ የቆየዉ የሙስሊሞች ከሊፋዊ አስተዳደር መሆኑ ነዉ።ጀርመናዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ልክ እንደ ብሪታንያዊ የሐይማኖት ተቋም መሪ እንደ ዑስማ ሐሰን ሁሉ ISIS ሐገር የመግዛት ግቡን ፖለቲካን ከእስልምና ሐይማኖትን በደባለቀ ሥልት ገቢር ማድረግ ይሻል።

Screenshot Anti IS Facebook Seite Satire
ምስል Screenshot

የቡድኑን ሁለት ድብልቅ ሥልት መግታት ጨካኝ እርምጃዉን ማስቆም የሚቻለዉ የፖለቲካ ተንታኝ ሮዚኒ እንደሚሉት በሁለት መንግድ ነዉi

«እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ISISን ለማስቆም ሁለት ሥልቶች መከተል አስፈላጊ ነዉ።አንደኛዉ ቡድኑ ያገኘዉን ወታደራዊ ድል መግታት፤ ሁለተኛዉ ከሐማይኖታዊዉ እስተምሕሮት መቃረኑን የማጋለጡን (ዘመቻ) ማጠናከር።»

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ