1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብራሰልሱ የሽብር ጥቃትና ምክንያቶቹ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 20 2008

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ብራሰልስ ቤልጂግን ያናወጡት የቦምብ ጥቃቶች ማነጋገራቸው ቀጥሏል የጥቃቶቹ መጠንና የተጣሉበት ቦታ የቤልጂግ የፀጥታ ጥበቃን ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል ። ጥቃቶቹ ዋና ከተማይቱ ብራሰልስ ላይ ያነጣጠሩበት ምክንያትም እንዲሁ እያነጋገረ ነው ።

https://p.dw.com/p/1ILWT
Belgien Brüssel Kerzen Trauer Terroranschläge
ምስል Getty Images/AFP/K. Triboullard

የአውሮፓ ማዕከል ብራሰልስ ካለፈው ሳምንቱ የአሸባሪዎች ጥቃት ገና አላገገመችም ። ህዝቧም በሃዘንና በስጋት ውስጥ ነው ያለው ። ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በብራሰልሱ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች ማስተናጋጃ እንዲሁም የአውሮጳ ህብረት ጽህፈት ቤት አቅራቢያ በሚገኘው የምድር ባባቡር መስመር ላይ የቦምብ ጥቃቶች የጣሉት ሦስት ጥቃት አድራሾች መሞታቸው ቢረጋገጥም የአንዱ ተጠረጣሪ ደብዛ ግን አሁንም እንደጠፋ ነው ። ምንም እንኳን ባለፈው አርብ ብራስልስ አዉሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ካደረሱት ሦስተኛዉ ነው የተባለ ግለሰብ ቢያዝም በቂ ማስረጃ አልተገኘበትም ተብሎ ተለቋል ። ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደው ራሱን እስላማዊ መንግሥት ወይም IS ብሎ የሚጠራው ቡድን ቤልጂግን እስልምናንና የእምነቱን ተከታይ በማጥቃት ወንጅሏል ። ተንታኞች እንደሚሉት ብራሰልስ የቡድኑ የጥቃት ዒላማ ውስጥ እንድትገባ ያደረጓት የተለያዩ ምክንያቶች ናቸው ። ክሎድ ሞኒክ የሽብር ጉዳዮች አዋቂ እና ብራሰልስ የሚገኘው የቤልጂግ ስለላና የደህንነት ማዕከል ሃላፊ ናቸው ። ርሳቸው እንደሚሉት ከምክንያቶቹ አንዱ ቤልጂግ የብዙ አሸባሪዎች መነኻሪያ መሆንዋ ነው ።
«ቤልጂግ እንደምታውቁት አሸባሪዎች በብዛት ወደ ሌሎች ሃገራት ለውጊያ ከሚሄዱባቸው የአውሮጳ ሃገራት አንዷ ናት ። በዚህ ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዘው ግን ፈረንሳይ ናት ። ከፈረንሳይ የሄዱ 2ሺህ ሰዎች በሶሪያው ጦርነት ተካፍለዋል።ከፈረንሳይ ቀጥሎ አሸባሪዎች በብዛት ለውጊያ የሚሄዱት ከቤልጂግ ነው ። እነዚህም ከ600 እስከ 1 ሺህ ይደርሳሉ ። ከትንሿ ቤልጂግ ህዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃጸር ከቤልጂግ ለውጊያ የሚሄዱ ሰዎች ከፈረንሳይ ከሚሄዱት ከ3 እስከ 6 እጥፍ ይበልጣል።ይህም በርካታ ሰዎች ለምን ሶሪያ ሊዋጉ እንደሄዱ እና አውሮጳ ውስጥም ለምን ጥቃት እንደሚያደርሱ ያስረዳል ። »
ከዚህ ሌላ ሞኒክ እንደሚሉት ቤልጂግ ከሚኖሩ ሙስሊሞች የተወሰኑት በእምነታቸውና በባህላቸው ምክንያት ከህብረተሰቡ መገለላቸው ሌላው ለጥቃት የሚያነሳሳ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ። አንዳንድ ሙስሊም ወጣቶች በትምህርታቸው መግፋት አለመቻላቸው ፣ የኑሮአቸው ደረጃ ዝቅተኛነት ና ተስፋ መቁረጥ ይህን ሊያስከትል እንደሚችል ይገመታል ። ከዚህ በተጨማሪ ቤልጅግ በዓለም ዓቀፉ ፀረ ሽብር ትግል ውስጥ ያላት ተሳትፎና የአውሮጳ ማዕከል መሆንዋም ለጥቃት ከዳረጓት ምክንያቶች ውስጥ ይደመራል እንደ ሞኒክ ።
«ቤልጂግ የዓለም ዓቀፉ የፀረ ሽብር ጥምረት አካል ናት ። ቤልጂግ በፊትም አሁንም ኢራቅን ትደበድባለች ። አሁን ደግሞ የቤልጂግ ባህር ኃይል ፣ሻርል ደጎል የተባለውን ዳይሽን ወይም IS ን የሚደበድቡ የፈረንሳይ የጦር አውሮፕላኖች ተሸካሚ መርከብን ያጅባል ። የመጨረሻው ነጥብ ደግሞ ብራሰልስ የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅትና የአውሮጳ ህብረት መቀመጫ ናት ። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ቤልጂግን ለጥቃት ተመራጭ አድርገዋታል ።»
የማክሰኞው ጥቃት የደረሰው የቤልጂግ ፖሊስ በህዳሩ የፈረንሳይ የሽብር ጥቃት ሲፈለግ የነበረው አብድስላም የተባለውን ዋነኛ ተጠርጣሪ ብራሰልስ ውስጥ ከያዘ ከ 4 ቀናት በኋላ ነው ። ለዓለም ዓቀፉ ፀረ ሽብር ዘመቻ ብዙ አስተዋፅኦ የምታደርገው የቤልጂግ ፖሊስ አፍንጫው ስር ሲወጣ ሲገባ የቆየውን ይህን ተጠርጣሪ ለወራት መያዝ ባለመቻሉ ክፉኛ ሲወቀስ ቆይቷል ። ከዚህ ሌላ ካለፈው ሳምንቱ ጥቃት አድራሾች አንዱ አጥፍቶ ጠፊ ቱርክ ከዚህ ቀደም ይዛ ወደ ኔዘርላንድስ የመለሰችውና ይህንኑም የቤልጂግ ባለሥልጣናት የሚያውቁት ጉዳይ መሆኑ የሃገሪቱን የፀጥታ ሃላፊዎች በቸልተኝነት እያስተቸ ነው ። ይኽው ኢብራሂም ኤል ባኩሪ የተባለው በብራሰልሱ ባቡር ጣቢያ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ያደረሰው ግለሰብ ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር ቱርክና ሶሪያ ድንበር ላይ ተይዞ ወደ ኔዘርላንድ ቢባረርም የኔዘርላንድስ ባለሥልጣናት ከቤልጂግ በኩል «እሰሩት» የሚል ትዕዛዝ ስላልደረሳቸው ለቀውታል ። በአጠቃላይ በቤልጂግ በሃገር ውስጥ ሙስሊሙ የህብረተሰብ ክፍል ተገሎ መቆየቱ እና መንግሥትም አሸባሪነትን ለመዋጋት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ድክመት ሃገሪቱን ለባለፈው ሳምንቱ የሽብር ጥቃት ካደረጓት ምክንያቶች ውስጥ በዋነኝነት የሚነሱ እንደሆኑ የሚናገሩ አስተያየት ሰጭዎችም አልጠፉም ። የሽብር ጉዳዮች አዋቂው ሞኔክ ደግሞ ችግሩን ከአቅም ማነስ ጋርም ያያዙታል።
«በርግጥ ችግሩ የቤልጂግ የደህንነት ተቋማት በሙሉ አቅማቸው አይንቀሳቀሱም ። የፖሊስና የደህንነት ሠራተኞች ቁጥር አነስተኛ ነው ። በዚህ ሰበብም አገልግሎታቸው ተወስኗል ። የአገልግሎት ሰጭ ቁጥር አነስተኛ በሆነበት ተዐምር ሊሰሩ አይችሉም ። ሆኖም ጥሩ ሊባል የሚችል ስራም እየሰሩ ነው ። የቅርብ ጊዜውን ታሪካችንን ስንመለከት ከመስከረም 1994 ቱ የአሜሪካን የሽብር ጥቃት ወዲህ ባለፉት 15 ዓመታት የቤልጂግ ፖሊስ አሰሳ እያካሄደ ከአልቃይዳ ከIS እና ከሌሎችም አሸባሪ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ያላቸውን አሸባሪዎች አስሯል ።በነገራችን ላይ የቤልጂግ የደህንነት መሥሪያ ቤት በርካታ አውሮጳውያን በጎ ፈቃደኞች በሶሪያው ጦርነት ለመዋጋት እንደሚሄዱ በማወቅ የመጀመሪያው ነው ።»
ያም ሆኖ የቤልጂግ ባለሥልጣናት አቅም በማጣት ብቻ ሳይሆን ይበልጡን በቸልተኝነትም መወቀሳቸው አልቀረም ። ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በጎ ፈቃደኛ ተዋጊዎች ከሶሪያ ወደ ቤልጂግ እንደተመለሱ የሚጠቁሙ መረጃዎች ቢደርሷቸውም ምንም ዓይነት እርምጃ ባለመውሰድ ይተቻሉ ። ሞኒክ ግን የቤልጂግ ፖሊስ ቸልተኛ መባሉን ሙሉ በሙሉ አይቀበሉም ።
«በርግጥ ፍላጎት ማጣት ወይም ቸልተኝነት የለም ይህ ግልጽ ነው ። ሆኖም የአቅም ማነስ ችግር አለ ለምሳሌ የቤልጂግ ፖሊስ የሚያስፈልገው ተጨማሪ 3500 የሰው ኃይል እጥረት አለበት ። ችግሩ ይበልጥ የአቅም ማነስ ነው ። ፍላጎቱ አለ አቅሙ ግን አናሳ ነው ። »
ሞኒክ የፖሊስና የደህንነት ሠራተኞች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አላስቻላቸውም ሲሉ ያነሱት የህግ ማዕቀፍም ይገኝበታል ። ለዚህና ለሌሎችም ችግሮች መፍትሄ ብለው ካነሷቸው ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል ።
«ተጨማሪ የሰው ኃይልና ገንዘብ የመፍትሄው አካል ነው ። ከዚህ ሌላ እንደ ልብ የሚያንቀሳቅስ የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ነው መሥራት ያለባቸውለምሳሌ የቤልጂግ ደህንነት መሥሪያ ቤት የተጠርጣሪዎችን ስልኮች ጠልፎ መቅረፅ የቻለው በጎርጎሮሳዊው 2012 ወይም በ2013 ዓም ነው ከመስከረም አስራ አንድ አንድ 2001 ዱ የአሜሪካን የአሸባሪዎች ጥቃት፣ ከ11 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው ።የቤልጂግ የደህንነት መሥሪያ ቤት በሃገሪቱ ህግ ምክንያት የተጠርጣሪዎች የስልክ የመልዕክት ልውውጦች መመዝገብ ያልቻለ ብቸኛዋ የአውሮጳ የደህንነት መሥሪያ ቤት ነው ።ስለዚህ የህግ ማዕቀፉ መሻሻል አለበት ። መሥሪያ ቤቱ መሠረታቸው ከአረብና ከቱርክ የሆነ ተጨማሪ የሰው ኃይልም ያስፈልገዋል ። »
አውሮፓውያን በክፍለ ዓለሙ የሚደርሱ የተለያዩ የሽብር ጥቃቶችን አስቀድመው መከላከል እንዴት ተሳናቸው የሚለው በአሁኑ ጊዜ ተደጋግሞ የሚነሳ ጥያቄ ነው ። ሞኒኬ የምዕራባውያን የስለላና የደህንነት ተቋማት በአንዳንድ አጋጣሚዎች የሽብር ጥቃቶች ከመድረሳቸው በፊት መከላከል ያልቻሉበትን ምክንያት ከተቋቋሙባቸው ዓላማ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ ።
«የአውሮጳ የደህንነት መሥሪያ ቤቶች የተመሠረቱት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ነው ። እነርሱም የሠለጠኑትና የተቋቋሙት ከሶቭየት ህብረት የሚመጣ አደጋን ለመከላከል ነው ። ስለዚህ ተግባራቸው አንዲት ሃገር ሶቭየት ህብረትን የኮምኒስት ፓርቲውን ፖሊት ቢሮ የስለላ መስሪያ ቤቱን ኬጂቢን ቀዩ ጦርንና የመሳሰሉትን መከታተል ነው ።ዛሬ ግን ሁሉ ነገር ተቀይሯል ። ቤልጂጎች አሁን ዓለም ዓቀፉን ስዕል ለመረደዳት ጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ።የዳይሽን እንቅስቃሴ ያውቃሉ ። ሆኖም የግለሰቦችን አደገኛነት ለይቶ በማወቅ ረገድ ግን ድክመት አለባቸው ።በአውሮጳ ምናልባትም 10 ሺህ የሚደርሱ ግለሰቦችን መከታተል ማጥናት ይኖርባቸው ይሆናል ። ግን ይህን ማድረግ አይችሉም ።በዚህ በኩል ጥሩ ሥራ አልተሰራም ። »
በሞኒክ አባባል ይህ ችግር የቤልጂግ የደህንነት መሥሪያ ቤት ችግር ብቻ ሳይሆን ፈረንሳይ ውስጥም የሚታይ ነው ። ፈረንሳይም በጎርጎሮሳዊው ጥር 7 2015 በሻርሊ ኤብዶ ጋዜጣ ሠራተኞች ላይ የደረሰውን ጥቃት እንዲሁም በዚያው ዓመት በህዳር ወር ፓሪስ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የተጣሉትን የሽብር ጥቃቶች መከላከል አልቻለችም ።ይህ ሊሆነን የቻለውም የሽብር ጉዳዮች አዋቂው ሞኒኬ እንዳሉት ሁኔታዎችን በጥልቀት ያለመፈተሽና በተገቢው መንገድ ያለመከታተል ችግር በመኖሩ ነው ። ከዚህ ሌላ በርሳቸው አስተያየት በሃይማኖት ነፃነት ስም የፅንፈኖች እንቅስቃሴ ችላ መባሉን ችግሩን አባብሶታል ። ሞኒኬ በሃይማኖት ነፃነት ስም ሳላፊስቶች ራሳቸውን እንዲያደራጁ መለቀቃቸው በቤልጂግ በፈረንሳይና በሌሎችም የአውሮፓ ሃገራት አሁን የሚታየውን እርሳቸው «ለህብረተሰቡና ለሙስሊሙም ካንሰር ሆኗል ያሉትን ችግር አስከትሏል ።

Belgien Brüssel Flughafen Zaventum Terminal Halle Rauch
ምስል picture-alliance/AP/Ralph Usbeck
Belgien Terroranschläge in Brüssel - Flughafen Zaventem
ምስል picture-alliance/dpa/D. Waem
Belgien Terroranschläge in Brüssel Fahndung Verdächtige
ምስል picture-alliance/dpa/Federal Police

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ