1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብራስልስ የቡድን ሰባት ጉባዔ

ሐሙስ፣ ግንቦት 28 2006

በብራስልስ የሁለት ቀናት ጉባዔ ያካሄዱት ሰባቱ በዓለም የበለፀጉት ኢንዱስትሪ መንግሥታት ለዩክሬይን ውዝግብ በቀጥታ ከሩስያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ጋ በመነጋገር መፍትሔ ለማፈላለግ እንደሚሹ አስታወቁ።

https://p.dw.com/p/1CBvV
G7 Gipfel in Brüssel
ምስል Reuters

የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ኦሎንድ እና የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካምረን ከፕሬዚደንት ፑቲን ጋ በዩክሬይን ጊዚያዊ ሁኔታ ላይ በዛሬው ዕለት ምክክር እንደሚያካሂዱ ተገልጾዋል። የቡድን ሰባት አባል ሀገራት መሪዎች ሩስያ ለዩክሬይን መረጋጋት ተጨባጭ ርምጃ እንድትወስድ ፣ ብሎም፣ ከሥዩሙ የዩክሬይን ፕሬዚደንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ ጋ ተባብራ እንድትሰራ፣ በምሥራቃዊ ዩክሬይን የሚዋጉትን ዓማፅያንመርዳቷን እና የጦር መሳሪያ ማስታጠቋን እንዳድታቆም፣ የጋዝ አቅርቦት ዋስትና እንድትሰጥ እና በዩክሬይን ድንበር ያለውን ጦሯን በጠቅላላ እንድታስወጣ ጥሪ አስተላልፈው፣ ይህን ካላደረገች ግን ማዕቀብ እንደሚጠናከርባት ትናንት ሌሊት አስገንዝበዋል። ሀገራቱ ለዩክሬይን ወደፊትም ድጋፋቸውን እንደማያቋርጡ የጀርመን መራሒት መንግሥት አንጌላ ሜርክል አስታውቀዋል።

G7 Gipfel Brüssel Obama und Cameron 05.06.2014
ምስል Reuters

« አዲስ ፕሬዚደንት ከተመረጠ በኋላ ዩክሬይንን መርዳት የምንችልበትን፣ ሁለተኛ፣ መወሰድ ስላለባቸው ርምጃዎች ከሩስያ ጋ ወደፊት ንግግሩን የምንቀጥልበትን፣ ሦስተኛም፣ ይህ ሁሉ ጥቅም ካላስገኘ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣል እንደሚቻል ግልጽ የምናደርግበትን ሁኔታ እናጤነዋለን።»

የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኾዜ ማኑዌል ባሮዞም ኮሚሽኑ ዩክሬይንን ለመርዳት ሁለት ዘርፎች ያሉት ፖሊሲ እንደሚከተል አረጋግጠዋል።

« ዩክሬይን ትረጋጋ እና በኤኮኖሚውም ታገግም ዘንድ ለመንግሥቱ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ርዳታ በመስጠት ድርሻ ማበርከት፣ እንዲሁም፣ ሩስያም በዩክሬይን ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን እና ተገንጣይ ኃይላትን የጦር መሳሪያ ማስታጠቋን እንድታቆም ተጨባጭ ግፊት ማሳረፋችንን መቀጠል ይሆናል። »

ይህ በዚህ እንዳለ ፣ የሩስያ ጠቅላይ ሚንስትር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ የቡድን ሰባት አባል ሀገራት የዩክሬይን ጦር በመንግሥቱ አንፃር በሚዋጉት ዓማፅያን ላይ የሚወስደውን የኃይል ርምጃ ለዘብተኛ ነው ማለታቸው ላካባቢው ሕዝብ ክብር እንደሌላቸው ያሳየ ነው ሲሉ በጥብቅ ነቅፈዋል።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሐመድ