1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦኮሃራም ጥቃት መስፋፋት

ረቡዕ፣ ጥር 18 2008

ቦኮሃራም በመባል የሚጠራው የናይጀሪያው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የሚያደርሰውን ጥቃት አጠናክሮ ቀጥሏል ። ቡድኑ በተለይ በካሜሩን ባለፉት ሳምንታትና ቀናት ተከታታይ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶችን ጥሏል። ባለፈው ሰኞ ሦስት አጥፍቶ ጠፊዎች ካሜሩንና ናይጀሪያ ድንበር ላይ ባፈነዱት ቦምብ 32 ሰዎች ሲገደሉ 86 ደግሞ ቆስለዋል ።

https://p.dw.com/p/1HkkQ
Kamerun Anschlag in Maroua
ምስል Getty Images/AFP/Stringer

[No title]

ባለፈው ሳምንት ደግሞ ሰሜን ካሜሩንአንድ መንደር ውስጥ በሚገኝ መስጊድ ላይ በደረሰ ተመሳሳይ ጥቃት የ4 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል ። ናይጀሪያን የሚያሸብረው ቦኮሃራም የተባለው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ካለፉት ዓመታት አንስቶ ትኩረቱን ወደ ካሜሩን ኒዠርና ቻድ አድርጓል ። ቡድኑ በተለይ በጎርጎሮሳዊው 2016 በየቀኑ ሊባል በሚችል ሁኔታ ካሜሩን ውስጥ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶችን አከታትሎ እየጣለ ነው። ቦኮሃራም ጠንካራ ይዞታውን ሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያን የሚያዋስነውን ሰሜናዊ ካሜሩንን ማጥቃት የጀመረው ከጎርጎሮሳዊው 2013 ዓም እንስቶ ነው ። ከዚያን ወዲህም ቦኮሃራም ወደ 1200 የሚጠጉ ሰዎችን መግደሉን የካሜሩን መንግሥት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አስታውቋል ። የሃገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር እንደተናገሩት አሸባሪው ቡድን ቦኮሃራም በዚህ ጊዜ ውስጥ 1098 ሰላማዊ ሰዎችን 67 ወታደሮችንና ሶስት የፖሊስ ባለሥልጣናትን ነው የገደለው ። ሚኒስትሩ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት እንዳሉት ከ2013 ዓም አንስቶ ቦኮሃራም ካሜሩን ላይ ከ30 በላይ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች አድርሷል ። በአሁኑ ጊዜ የቦኮሃራም ጥቃት ከናይጀሪያ ይልቅ በካሜሩን የመጠናከሩ ምክንያት እያነጋገረ ነው ። «ሬድ 24» በተባለው ጥናት ተቋም የትንተና ክፍል ሃላፊ ርያን ከሚንግስ ምክንያቱን ለዶቼቬለ ተናግረዋል ።
«በመጀመሪያ የናይጀሪያ መንግሥት ጦር በሰሜን ምሥራቅ የሃገሪቱ ክፍል በቦኮሃራም ላይ የሚያካሂደውን ፀረ ሽብር ዘመቻ አጠናክሮ ቀጥሏል ። ይህ እርምጃ ምናልባትም በአካባቢው የቦኮሃራም ጥቃት እንዲቀንስ ያደረገ ይመስለኛል ። ከዚህ በተጨማሪም ህዝብ በብዛት ከሰፈረባቸው እና የናይጀሪያ ጦር ከተቆጣጠራቸው አካባቢዎች በ2015 መጀመሪያ ላይ እንዲወጡም አስገድዷቸዋል ። በዚህ የተነሳም ቦኮሃራም ወደ ካሜሩን እንዲገፋ ተደርጓል ። ቡድኑ በአካባቢው የፀረ ሽብር እርምጃ አቅም መዳከሙን በመጠቀም በተለይ በሰሜን ካሜሩን የፀጥታ ተቋማትንና የሲቪል ይዞታዎችን እያጠቃ ነው ።»
ካለፈው ህዳር ወዲህ የካሜሩን ጦር በናይጀሪያ ድንበር ላይ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የቦኮሃራምን ኃይል ለማዳከም ያለመ ዘመቻ አካሂዶ ነበር ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጭዎች እንደተናገሩት ዘመቻው በርግጥም የቦኮሃራምን አቅም አዳክሟል ። በዚህ የተነሳም አማጺው ቡድን ከካሜሩን ጦር ጋር ቀጥተኛ ውጊያ ከማካሄድ ይልቅ በአጥፍቶ ማጥፋት ጥቃት ተሰማርቷል ። የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት አድራሾቹ ደግሞ በአመዛኙ ሴቶችና ልጃገረዶች ሆነዋል። ቦኮሃራም በካሜሩን የሚጥለው ጥቃት የሃገሪቱን ኤኮኖሚ ከማናጋቱም በላይ ህዝቡን አለመረጋጋት ውስጥ ከቷል ። የቡድኑ ጥቃት በግብርናና በገበያ ላይ ባሳደረው ተጽእኖ ሰበብ ወደ 2.2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለምግብ ችግር እዲጋለጡ አድርጓል ። ከመካከላቸው 15 ከመቶ የሚሆኑት ህጻናት ናቸው ። ከምንም በላይ አሳሳቢ የሆነው ደግሞ ቡድኑ ወጣቶችን እየሳበ መምጣቱ ። ወጣቶች ለተሻለ ህይወት መስዋዕት እንዲሆኑ በመቀስቀስ ከጎኑ እያሰለፋቸው ነው። ቦኮሃራምን ለመውጋት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት በጋራ ተነስተናል ቢሉም የቡድኑ እንቅስቃሴ ግን እየተስፋፋና መልኩንም እየለዋወጠ ቀጥሏል ። መፍትሄ ፍለጋው ያልተሳካው ከሚንግስ እንደሚሉት፣ በሃገራቱ መካከል መተማመን በመጥፋቱ ነው ።
«ቦኮሃራም በአካባቢው የሚካሄደውን የደፈጣ ውጊያ ማስፋፋቱ እና በቅርቡም በካሜሩን ያደረሳቸውን ጥቃቶች ስንመለከት፣ በናይጀሪያና በጎረቤቶቿ መካከል ያለው የሁለትዮሽ እና ብዙዎቹን የሚያቅፈው ግንኙነት እንዳለ ሆኖ፣ ትኩረቱ ለችግሩ የተባበረ ምላሽ መስጠት መሆን እንደነበረበት መገመት ይቻላል ። ይሁንና፣ አሁንም በነዚህ ሃገሮች መካከል የፖለቲካ አለመተማመኑ ጎልቶ የሚታይ ይመስላል ።
የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት ቦኮሃራም ላይ በተናጠልም ሆነ በጋራ የተለያዩ ዘመቻዎች ቢከፍቱም፣ ቡድኑ አሁንም የናይጀሪያውን የሳምቢሳን ደን ፣ ናይጀሪያና ካሜሩን ድንበር ላይ የሚገኙትን የማንዳራ ተራራዎችንና ቻድ ሐይቅ ላይ የሚገኙትን በርካታ ደሴቶች እንደተቆጣጠረ ነው ።

Kamerun Soldaten Anti Boko Haram
ምስል picture-alliance/dpa/N. Chimtom
Anschlag in Maiduguri Nigeria Archiv Juli 2014
ምስል AFP/Getty Images

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ