1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦኮ ሀራም ሽብር ረሀብን ማባባሱ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 9 2010

በሰሜን ምሥራቅ  ናይጀሪያ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ከአሸባሪው ሚሊሺያ የቦኮ ሀራም ቡድን ጋር ውዝግቡ ቀጥሏል። ምንም እንኳን የናይጀሪያ ጦር ባለፉት ጊዚያት ቡድኑን በመምታት ረገድ የተሳካ ወታደራዊ ርምጃ ማስመዝገቡን ቢገልጽም፣ በሽብርተንነት አንጻር የጀመረው ትግሉ ገና አላበቃም።

https://p.dw.com/p/2mBRN
Bauer Goni Issa Abba besprüht in Rann sein kleines Feld mit Pflanzenschutzmittel
ምስል DW/A.Kriesch

ቦኮ ሀራም በሰሜን ናይጀሪያ ባስፋፋው ሽብር ረሀብ ተባባሰ።

በየጊዜው የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት ይፈጸማል፣ ከቡድኑ ነፃ ሆነዋል በሚባሉት አካባቢዎችም እንኳን ፍርሀት እንደነገሠ ነው። ባንዳንድ አካባቢዎችም የሰብዓዊው  ቀውስ ተባብሷል። ሁኔታው እዚህ ደረጃ የደረሰበትን ምክንያት ለማወቅ የዶይቸ ቤለ ዘጋቢ ወደ ራን ከተማ ተጉዞ ነበር።
በሰሜን ምሥራቃዊ ናይጀሪያ የዝናብ ወራት በመሆኑ በግብርና ሙያ የተሰማሩት  በራን ከተማ አቅራቢያ የሚገኙት ጎኒ አባ ማሳቸውን ለቀጣዩ ዘር ለማዘጋጀት እና ፀረ ተባይ መድሀኒት ለመርጨት ወደዚያው ሲያመሩ ነበር ያገኘናቸው። ግን በፀጥታ ስጋት ምክንያት ስራቸውን አዳጋች እንዳደረገው ነው የገለጹት።
« በቦኮ ሀራም ሽብር የተነሳ ራቅ ብለው የሚገኙትን ማሳዎች በጠቅላላ መተው ተገደናል።  እርግጥ፣ እዚህ አስተማማኝ ነው፣ ይሁንና፣ ለሁላችን የሚሆን በቂ መሬት የለም። » 
ለነገሩ ፣ አባ ከብዙ ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መዝራት መቻላቸውን ይናገራሉ። የልጆች አባት የሆኑት አባ ባለፈው ዓመት የሆነ ጊዜ ላይ ሳይበሉ ያለፉበትን ቀን መቁጠር ማቆማቸውን ያስታውሳሉ። ለቀጣዩም ዓመት ቢሆን ብዙም ተስፋ የላቸውም።
« የሚሰበሰበው መኸር ብዙም ሩቅ አያስሄደኝም። ሁለት ሚስቶች እና ዘጠኝ ልጆች መመገብ አለብኝ። ኑሮን እንደነገሩ ለመግፋት ቢያንስ በዓመት 40 ጆንያ ማሽላ ያስፈልገኛል።  ሆኖም የእኔ መሬት ከዚህ በጣም ርቆ ነው የሚገኘው። እንዲያም ቦሆን  ግን አያቴ ይህችን መሬት ስለተወልኝ እኔ እድለኛ ነኝ፣ »    
የራን ከተማ ጥበቃ አሁን በናይጀሪያ ጦር ስር ሲሆን፣ የከተማይቱ ነዋሪዎቹ በአምስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛሉ። በአባ ጎኒ ማሳ አቅራቢያ ከሚኖረው ህዝብ የተውጣጣ፣ ግን፣ በሚገባ ያልታጠቀ  ቡድንም ለነዋሪዎቹ ጥበቃ ያደርጋል።
« በዚህ አካባቢ ሌት ከቀን ጥበቃ እናደርጋለን። የቦኮ ሀራም አባላት ካጋጠሙን እንዋጋቸዋለን፣ እንገድላቸዋለን ወይም ይገድሉናል። አንፈራም፣ ሌሊት የሆነ ቦታ መብራት ካየን ወደዚያ  በመሄድ እናጣራለን። »
ሰብል ካልተሰበሰበ መዘዙ ምን ሊሆን እንደሚችል በራን ከተማ በግልጽ ይታያል። ብዙ ሰዎች በረሀብ እና ባልተመጣጠነ አመጋገብ እየተሰቃዩ ነው። ሌሎች ደግሞ በቀላሉ ሊፈወሱ በሚችሉ በበሽታዎች እየሞቱ ነው። ከዚህ ሌላ ደግሞ ፣ በናይጀሪያ የተመድ የሰብዓዊ ርዳታ አስተባባሪ መስሪያ ቤት፣ በምህጻሩ የኦቻ ምክትል ኃላፊ ፒተር ሉንድበርግ እንደሚሉት፣ ባካባቢው የመኪና መንገዶች ስለሌሉ የርዳታ ድርጅቶች በነዚህ የዝናብ ወራት እንደልብ መንቀሳቀስ አለመቻላቸው ችግሩን አባብሶታል። 
« ይህ የፀጥታ ቀውስ አሁን የምግብ እጥረት ቀውስ አስከትሏል። ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ነው። በዓመቱ በጣም አዳጋች የተባለ ወቅት ላይ ነው የምንገኘው። ለገበሬዎች በሰኔ ወር በርዳታ የቀረበው ዘር፣ የማረሻ ቁሳቁስ እና ማዳበሪያ ጥሩ ሰብል መሰብሰብ  እንደሚያስችላቸው እና የአካባቢውን ሁኔታ እንደሚያሻሻል ተስፋ አድርገን እየጠበቅን ነው። »
ይሁንና፣ ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ብሩህ ተሳፋ የላቸውም። ናይጀሪያዊው የግብርና ባለሙያ አባ ጋምቦ የሀገሪቱ መንግሥት በቂ ርምጃ አልወሰደም ሲሉ ወቅሰው፣ ለገበሬዎቹ ተጨማሪ ርዳታ እና ምግብ እንዲቀርብ  ጠይቀዋል።
« ሰዎችን ምግብ ሳታቀርብላቸው ዘር ብቻ  ከሰጠሀቸው፣ ዘሩን እንደምግብ እንደሚጠቀሙበት የሚጠበቅ ነው። አንድ የተራበን እና በቤቱ እንደሱ የተራቡ ሁለት ሚስቶች እና ሰባት ልጆች ያሉትን ሰው የሚዘራው አስር ኪሎ ማሽላ ብትሰጠው፣ ማሳውን ረስቶ ማሽላው ተገንፍቶ ለተራቡት ልጆቹ  እንዲሰጥ ነው የሚያደርገው። »
ሰላም እስከሌለ ድረስ ረሀብ እንደማይጠፋ ገበሬው ጎኒ አባ እርግጠኛ ናቸው። ብዙዎቹ ጎረቤቶቻቸው በወቅቱ  የዝናብ ወራት ማሳቸውን ሊያርሱ አይችሉም። በዚህም ለተጨማሪ አንድ ዓመት በምግብ ርዳታ ላይ ጥገኛ ናቸው። በነዚህ ገበሬዎች አንጻር፣ ቢያንስ ለማዳበሪያ መግዣ ትንሽ ገንዘብ ያጠራቀሙት ጎኒ አባ  እንደገና  ቤተሰባቸውን ራሳቸው ለመመገብ ቆርጠው ተነስተዋል።

Der Hunger in Rann ist überall sichtbar
ምስል DW/A.Kriesch
Ein von Boko Haram zerstörtes Dorf in der Nähe von Rann
ምስል DW/A.Kriesch
Bauer Goni Issa Abba besprüht in Rann sein kleines Feld mit Pflanzenschutzmittel
ጎኒ አባምስል DW/A.Kriesch

 አድሪያን ኪርሽ/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ