1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦኮ ሃራም እና የአይ.ኤስ. ግንኙነት የደቀነው ስጋት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 1 2007

የናይጄሪያው እስልምና አክራሪ ቡድን ቦኮ ሃራም በኢራቅና ሶሪያ እስላማዊ መንግሥት መሰረትኩ ላለው አይ.ኤስ. (IS) ታጣቂ ቡድን ታማኝነቱን መግለጹ የፖለቲካ ተንታኞችን ትኩረት ስቧል።

https://p.dw.com/p/1EoKQ
Abubakar Shekau
ምስል picture alliance/AP Photo

የቡድኑ መሪ አቡባካር ሼካው በድምጽ ያስተላለፈው መልዕክት ለዛሬ ለቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ብቻ ቢውልም በሂደት ግን በናይጄሪያ ብቻ የተወሰነውን ግጭት ዓለም አቀፍ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት እየተደመጠ ነው።

ላለፉት ስምንት ወራት በአፍጋኒስታን፤ አልጄሪያ፤ግብጽ፤ሊባኖስ፤ሊቢያ፤ፓኪስታንና የመንን በመሳሰሉ ሃገሮች አጋሮች ያገኘው እና በአቡበከር አል-ባግዳዲ የሚመራው አይ.ኤስ. (IS) አክራሪ ቡድን ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ከምዕራብ አፍሪቃ የቦኮ ሃራምን ታማኝነት አግኝቷል። በቻድ እና ኒዠር ወታደሮች መጠነ ሰፊ ዘመቻ የተከፈተበት የቦኮ ሃራም እስላማዊ ታጣቂ ቡድን መሪ አቡባከር ሼካው ድምጽ የተላለፈው እና በትዊተር ማህበራዊ ድረ-ገጽ የተለቀቀው መልዕክት የዓለምን ትኩረት ስቧል። ሬድ24 (Red24) በተሰኘው የቀውስ ጥናት ተቋም የፖለቲካ እና የደህንነት ስጋት ተንታኝ የሆኑት ሪያን ካሚንግስ የቦኮ ሃራም እና አይ.ኤስ. (IS) ታጣቂ ቡድኖች ግንኙነት ለጊዜው ተምሳሌታዊ ብቻ መሆኑን ይናገራሉ።

«ቦኮ ሃራም ለአይ.ኤስ ያለውን ታማኝነት መግለጹ ለጊዜው ተምሳሌታዊ ነው። አሁን ባለበት ደረጃ ግን ሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች የጋራ ተልዕኮ ይኖራቸዋል ወይም የተልዕኮ ትብብር ያደርጋሉ ማለት አይደለም።»
እንደ ሪያን ካሚንግስ ያሉ የፖለቲካ እና ደህንነት ተንታኞች የአቡበከር ሼካው የድምጽ መልዕክት ትክክለኛ ነው አይደለም ከሚለው ክርክር ይልቅ የታማኝነቱ ዋነኛ ዓላማ ላይ ትኩረት አድርገዋል።ቦኮ ሃራም ከአይ.ኤስ ጋር ጥምረት ለመፍጠር መሞከሩም እምብዛም የሚገርም አይደለም ይላሉ። የናይጄሪያው ቦኮ ሃራም በኢራቅ እና ሶርያ እስላማዊ መንግስት መስርቻለሁ ከሚለው አይ.ኤስ ጋር የሚፈጥረው ግንኙነት ተቀባይነት ለማግኘት፤በጎ ፈቃደኛ ታጣቂዎችን ለመመልመል እና የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማሰባሰብ ሊያግዘው ይችላል ተብሏል። ቡድኑ በተበታተነ መንገድ የሚያስተላልፋቸውን የማህበራዊ ድረ-ገጽ መልክቶቹን መልክ ለማስያዝ ከአይ.ኤስ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እርዳታ ሊያገኝ እንደሚችልም ተንታኞቹ ያምናሉ። ቦኮ ሃራም ከአይ.ኤስ መሪ አቡበከር አልባግዳዲ በጎ ምላሽ ካገኘ ዓለም አቀፉን የእስላማዊ ጦርነት አሊያም ጂሃድ ለመቀላቀል ያግዘዋል። ሪያን ካሚንግስ ቦኮ ሃራም በኢራቅና ሶርያ ተመሰረተ ለተባለው እስላማዊ መንግስት ታማኝነቱን ሲገልጥ በሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ካሉት የታጣቂ ቡድኑ ወኪሎች ጋር አጋርነት እየመሰረተ መሆኑን ያስረዳሉ።

«ቦኮ ሃራም ለእስላማዊው መንግስት ታማኝነቱን ሲገልጽ የመጀመሪያው ታጣቂ ቡድን አይደለም።አይ.ኤስ በአልጄሪያ፤ሊቢያ እና ግብጽ ካሉ ቡድኖች ተመሳሳይ ታማኝነትን ተቀብሏል። እነዚህ ትንንሽ ቡድኖች የሚንቀሳቀሱት በተናጠል ቢሆንም ሁሉም በእስላማዊ መንግስት ሰንደቅ ስር ነው። በዚህ ወቅት እንደ እስላማዊ መንግስት ወኪል በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት ቡድኖች ታጣቂዎችን እና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን የሚለዋወጡበት የጋራ ጥምረት በሂደት ሊፈጥሩ ይችላሉ።»
የቻድ እና ኒጀር ወታደሮች በቦኮ ሃራም ላይ በወሰዱት እርምጃ ሁለት ከተሞችን ማስለቀቃቸው ተሰምቷል።በቦኮ ሃራም ላይ በተከፈተው ጥቃት ማላም ፋቱሪ እና ዳማሳክ የተሰኙ ከተሞች ከታጣቂው ነጻ መውጣታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ሪያን ካሚንግስ የናይጄሪያ ጦር የቦኮ ሃራምን ጥቃት ለመመከትም ይሁን ቡድኑን ለማጥፋት ቸልተኝነት ቢታይበትም የቡድኑ መስፋፋት በራሱ አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራሉ።

«የቦኮ ሃራም ጉዳይ የናይጄሪያ የውስጥ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል። ይሁንና ትልቁ ጉዳይ ቡድኑ የናይጄሪያን ድንበር በመሻገር በካሜሩን፤ኒዠር እና ቻድን በመሳሰሉ ሃገሮች በመስፋፋት ላይ ይገኛል።ይህ ደግሞ የናይጄሪያ መንግስት የቦኮ ሃራምን ጥቃት ለመመከት ባሳየው ቸልተኝነት ላይ ተጨማሪ ፈተና ነው። የናይጄሪያ መንግስት ጥቃት ሲከፍት በጎረቤት ሃገራት የሚገኘው የቡድኑ መሰረት ሳይነካ እየቀረ ፈተና ሆኖበታል።»
የቦኮ ሃራም ታማኝነት ከአይ.ኤስ ምን አይነት ምላሽ እንደሚያገኝ እስከሁለት ሳምንት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። ሪያን ካሚንግስ ግን በናይጄሪያ እና የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ተወስኖ የቆየው የቡድኑ ተፅዕኖ በቀጠናው ብሎም በመላው ዓለም ሊስፋፋ እንደሚችል ስጋታቸውን ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Boko Haram Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo
Afrika Nigeria Niger & Tschad Offensive gegen Boko Haram
ምስል Reuters/E. Braun