1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ ውሳኔና ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 23 2005

የሶሪያ መንግሥት በዜጎቹ ላይ ፈፅሟል የተባለው የኬሚካል ጦር መሣሪያ ጥቃት በተባበሩት መንግስታት ፈታሾች በመጣራት ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ምዕራባውያን መንግሥታት በሶሪያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር የተዘጋጁ ይመስላል ከህግ አንፃር ሲታይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ዓለም ዓቀፉን ህግ የሚጥስ እርምጃ ነው ።

https://p.dw.com/p/19Ykc
ምስል Getty Images

ወታደራዊ እርምጃን ህጋዊ ሊያደርግ የሚችለው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውሳኔ ሲያሳልፍ ብቻ ነው ። ይሁንና የፀጥታ ምክር ቤት ቋሚ አባላት ሩስያና ቻይና ምናልባትም ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቀውን ውሳኔ ሊያግዱ ይችላሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው ። ድምፅን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ሁለቱ ሃገራት ወታደራዊ እርምጃን ከጥያቄ ውስጥ አያስገቡም ።
በሶሪያ ላይ ይወሰዳል ተብሎ የሚሰጋው እርምጃ የመጀመሪያው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አይደለም ። የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆርጅ W ቡሽ እጎአ ለ2003 ዓ. ምህረቱ የዩናይትድ ስቴትስ የኢራቅ ወረራ ድጋፍ ለመስጠት የተባበሩትን ሃገራት «የፈቃደኞች ጥምረት » በማለት ነበር የሚጠሩት ።
በዩናይትድ ስቴትስና በብሪታኒያ የሚመራው የዚህ ተልዕኮ ዓላማም ኢራቅን ከሰዳም ሁሴን ነፃ ማውጣት ነበር ። ከዘመቻው በፊት ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅ ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎች እንዳሏት ለማረገጋጥ ሞክራ ነበር ። የዚያን ጊዜው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮልን ፓውል ማስረጃ ነው ያሉትን በወቅቱ ለተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አቀረቡ ።

Syrien UN-Kontrolleure überprüfen Vorwürfe zu Giftgasangriff
የተመድ የኬሚካል ጦር መሣሪያ ፈታሽ በሶሪያምስል Reuters/Mohammad Abdullah

ሆኖም ጀርመን ፈረንሳይ እና ሩስያ የማስረጃውን እውነትነት በእጅጉ ተጠራጠጥረውት ነበር ። የያኔው የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሽካ ፊሸር ያኔ ማስረጃው አላሰመነኝም ነበር ያሉት ። ጥርጣሬያቸው ወደ ኋላ መለስ ተብሎ ሲጤን ትክክለኛ ነበር ። በመካከሉ ያኔ የቀረበው መረጃ የተጭበረበረ ሰነድ እንደነበረ ግልፅ ሆኗል ። ኮልን ፓውልም የፈፀሙት ስህተት አጋልጧቸው ከፖለቲካው ራሳቸውን አግለዋል ። የቀድሞው የጀርመን ጦር ኃይሎች ሜጀር ጀነራል ማንፍሬድ አይዝለ የኢራቅ ወረራና የሶሪያው ሁኔታ ለንፅፅር የሚቀርብ አይደለም ይላሉ ። ሆኖም በርሳቸው አስተያየት የሶሪያ ሁኔታ በ1999 በኮሶቮ ከተፈፀመው ጋር ይመሳሰላል ። ዝርያቸው አልባንያ የሆነ አማፅያን ኮሶቮን ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ነፃ ለማውጣት በጀመሩት ውጊያ የዩጎዝላቪያ ጦር ኃይል ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችና ጭፍጨፋዎች መፈፀሙን የተመለከቱ ዘገባዎች ወጥተው ነበር ። ሩስያ ግን በወቅቱ ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የቀረበውን የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ተቃውማለች ። የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት NATO ም ካለ ፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ውሳኔ የአየር ጥቃት ለማካሄድ ወሰነ ። ውሳኔው ግንሜጀር ጀነራል ማንፍሬድ አይስለ እንደሚሉት መዘዙን ከግምት ውስጥ ያስገባ አልነበረም ።


« የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት እዚያ የተካሄደውን የዘር ማጥፋት በጣም ተጨባጭ አድርጎ አሳይቷል ። የጎደለ ነገር ቢኖር ሞስኮ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ስትጠቀም ያስከተላቸው መዘዞች ነበሩ ። »
የአግስቡርግ ዩኒቨርስቲ ባልደረባና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አንድሪያስ ቡክ በአይዝለ አስተያየት ይስማማሉ ።
« ኮስቮ ውስጥ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳምን ግልፅ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነበር ።» ምንም እንኳን የ NATO ጣልቃ ገብነት በመሠረቱ ዓለም ዓቀፉን ህግ የተፃረረ ቢሆንም በወቅቱ እርምጃውን ለመውሰድ የሚያስገደድ የሞራል ሃላፊነት እንደነበረ ቦክ ያምናሉ ። ከዚያም ቀደም ሲል ያለ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ እጎአ በ1990 የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ አባል ሃገራት ወታደሮች በላይቤሪያው የርስ በርስ ጦርነት ሰብዓዊነት መሠረት ያደረገ ተመሳሳይ ጣልቃ ገብነት ተፈፅሟል ። ይህ ግን ያን ያህል አላነጋገረም እንደ አይዝለ ።

Galerie Leben und Alltag der syrischen Zivilbevölkerung im Bürgerkrieg
የሶሪያ አይር ኃይል ጥቃት በደማስቆ አቅራቢያምስል Reuters/Goran Tomasevic


« ጉዳዩ አንገብጋቢ ሆኖ በዚያን ጊዜ የዓለምን ትኩረት አልሳበም ። ምክንያቱም አፍሪቃ ውስጥ በሚገኝ አንድ አገር የሆነ ነበርና ።»
ያለ ፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችለው አማራጭ እጎአ በ2001 በካናዳ ሃሳብ አቅራቢነት ሥራ ላይ የዋለው «ጥበቃ የማድረግ ሃላፊነት» የተሰኘው ደንብ ብቻ ነው ። ደንቡ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ በአንድ ሃገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ያስችላል ። እ.ጎ.አ በ2011 የተመድ በሊቢያ ላያ ባሰለፈው ውሳኔ ይህ ደንብ ተጠቅሶ ነበር ። በሶሪያ ጉዳይም ላይ ቢሆን የተመድ እስካሁን ያሳለፈው ውሳኔ ባይኖርም ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታኒያ በሶሪያው ጦርነት ጣልቃ ለመግባት እንደ አንድ ህጋዊ መነሻ መጠቀማቸው አይቀርም ። በረዥም ጊዜም ደንቡ ዓለም ዓቀፋዊና ጣልቃ ለመግባትና ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ህጋዊ መሰረት ሊሆን ይችላል ።
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ

UN Inspektoren in Syrien 26.08.2013
የተመድ ፈታሾችምስል Reuters
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ