1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ የልማትና ፋይናንስ ጉባኤ ተጠናቀቀ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 9 2007

ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና ልማት ጉባኤው ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ተጠናቀቀ። ምንም እንኳን በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጉባኤው የመጨረሻ ውጤት ስኬታማነት ጥርጣሬያቸውን ገልጠው የነበረ ቢሆንም፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) እጅግ ስኬታማ ብሎታል።

https://p.dw.com/p/1G0Ht
Äthiopien Addis Abeba UNO-Konferenz zur Finanzierung nachhaltiger Entwicklung
ምስል DW/G. Tedla HG

[No title]

ጉባኤውን በተመለከተ ቀደም ሲል በደሃ ሃገራት እና በበለፀጉ ሃገራት መካከል ስምምነት ላይኖር ይችላል የሚል ጥርጣሬም አሳድሮ ነበር። የአዲስ አበባ የድርጊት አጀንዳ በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (AAAA) የሚል ስያሜ የተሰጠውን ስምምነት አስመልክቶ የተመድ «ፈር ቀዳጅ ስምነት» ሲል አወድሶታል። ስብሰባዉ ሲጠናቀቅ ንግግር ያደረጉት አንድ የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣንም አዲስ አበባ ላይ የተደረሰዉ የድርጊት አጀንዳ የአምዓቱን የልማት መርሃግብር ከዳር ለማድረስ ለታሰበዉ ዓላማ ጠንካራ መሠረት መጣሉን አመልክተዋል። በተመድ የኤኮኖሚ እና ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ክፍል ባለሥልጣን ዉ ሆንግቦ በበኩላቸው ብለዋል።

«የአዲስ አበባው የድርጊት አጀንዳ ዘላቂ የልማት ግቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ መስከረም ወር ውስጥ በኒውዮርክ ለሚጸድቀው ስምምነት ጠንካራ መሠረት ለማበጀት ፈር ይቀዳል።»

በአዲስ አበባ ስምምነት የተደረገበት የድርጊት አጀንዳ በታዳጊ ሃገራት መዋዕለ-ንዋይ ፍሰት እንዲጠናከር አጋዥ ይኾናል ተብሏል። ስምምነቱ ለታዳጊ ሃገራት የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍም ያስገኛ ተብሏል።

«የድርጊት አጀንዳው ዘላቂ ልማትን በገንዘብ እና ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ለመደገፍ ዓለም አቀፍ የሥራ መሠረት እንዲኖር ያመቻል። ዘላቂ ፋይናንስ እንዲጠናከርም ይረዳል። ይኽ አዲስ የሥራ መመሪያ መሠረት ማናቸውንም የገንዘብ ነክ ፍሰቶችን እና የኤኮኖሚ፣ ማኅበረሰባዊ እንዲሁም የከባቢ ዓየር ጥበቃን የሚያስቀድሙ መርኆችን ያግዛል።»

የአዲስ አበባው የድርጊት አጀንዳ የተሰኘውን ስምምነት የዓለም መሪዎች የፊታችን መስከረም ወር ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያጸድቁታል ተብሎ ይጠበቃል። አዲስ አበባ ላይ ለአራት ቀናት የተካሄደዉ ጉባኤ የመጨረሻ ዕለት ላይም በመክፈቻዉ ተኝተዉ የነበሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ከዋና ጽሕፈት ቤታቸዉ ከኒዉዮርክ መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል።


ጌታቸው ተድላ ኃ/ጊዮርጊስ

Äthiopien Addis Abeba UNO-Konferenz zur Finanzierung nachhaltiger Entwicklung
ምስል DW/G. Tedla HG

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ