1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተልዕኮ ቅሌት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 7 2007

በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ከቀረበበት የወሲብ ጥቃት ክስ በተጨማሪ በርካታ ውስብስብ ችግሮች አሉበት ተባለ። በተ.መ.ድ. ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን ግፊት የተልዕኮው ዋና አዛዥ ስራቸውን መልቀቃቸው ለችግሮቹ መፍትሄ እንደማይሆን በዓለም አቀፉ ቀውስ ተመልካች ቡድን ተመራማሪው ቴሪ ቪርኮሎን ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/1GFGB
Symbolbild UN Mission Soldat
ምስል imago/blickwinkel

[No title]

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ግዳጅ ላይ ሲሰማሩ ቀዳሚ አላማቸው በርስ በርስ ጦርነት ኑሯቸው የተቃወሰ ዜጎችን የመጠበቅ ነበር። ወታደሮቹ በእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች ልዩነት በተበጠበጠችው አገር ቆይታቸው ዓለም የጣለባቸውን አደራ ረስተው በሰላማዊ ዜጎች ላይ ወሲባዊ ጥቃት መፈጸማቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ዘገባ አትቷል።

የልዑኩ የበላይ አዛዥ የ64 አመቱ ሴኔጋላዊ ባባካር ጋዬ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን በደረሳቸው ትዕዛዝ የስራ መልቀቂያቸውን አስገብተዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪዎች በዘመቱባቸው አካባቢዎች በወሲብ ጥቃት ሲከሰሱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በዓለም አቀፉ ቀውስ ተመልካች ቡድን የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተመራማሪው ቴሪ ቪርኮሎን የባንኪ ሙን ውሳኔ ግብረ-ኃይሉ በቀረበበት የወሲብ ጥቃት ክስ ላይ ብቻ መሰረት ያደረገ አለመሆኑን ይናገራሉ።

Französische Soldaten in der Zentralafrikanischen Republik
ምስል AFP/Getty Images/M.Medina

«እንደሚመስለኝ ይህ ከቀረበው የወሲባዊ ጥቃት ክስ ከፍ ያለ ነው። ከወሲባዊ ጥቃት ክሱ በተጨማሪ በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሚገኙ የሰላም አስከባሪዎች አሳሳቢ የባህሪ ችግሮች እንዳሉባቸው ሪፖርቶች ቀርበዋል። አንደኛው ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአንድ ታጣቂ ቡድን መሪን ለመያዝ የተደረገው የተሰናከለ ተልዕኮ ነው። ይህ ያልተሳካ ተልዕኮ በምሽት የተካሄደ ሲሆን የታጣቂ መሪውን ለመያዝ በተደረገው ሙከራ በርካት ንጹሃን ሰዎች ተገድለዋል። በሰላም አስከባሪዎቹ መካከልም በርካታ ግድያዎች ተፈጽመዋል።»

ቴሪ ቪርኮሎን በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ከሚገኙ የሰላም አስከባሪዎች መካከል ባልደረቦቹን የገደለውን የብሩንዲ ወታደር አስታውሰዋል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንኳ የሩዋንዳ ሰላም አስከባሪ ወታደር አራት ባልደረቦቹን ገደሎ ፤ሌሎችስምንትደግሞማቁሰሉ አይዘነጋም።ቴሪ ቪርኮሎን ባንኪ ሙን በባባካር ጋዬ ላይ የወሰዱት እርምጃ ውስብስብ ችግሮች ያሉበትን የመካከለኛው አፍሪቃ ሰላም አስከባሪ አያስተካክለውም ይላሉ።

«በእርግጥ የተልዕኮው አዛዥ ተጠያቂ ናቸው። ይሁንና ሌሎች ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች በተለይ በወታደራዊ የእዝ ሰንሰለቱ ውስጥ ስለመኖራቸው ምንም የተባለነገር የለም። ከኒው ዮርክ የተወሰነው ውሳኔ አዛዡ ስራቸውን እንዲለቁ በማስገደድ የሚያበቃ ብቻ ከሆነ የተልዕኮውን ውስጣዊ ችግሮች አይፈቱም። በመካከለኛው አፍሪቃ የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ምን እንደተፈጠረ ሊፈተሽ ይገባል።»

Zentralafrikanische Republik UN-Sicherheitstruppen in Bangui
ምስል picture-alliance/AA/Stringer

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮውን የተቀበለው ከአፍሪቃ ህብረት ወታደሮች ነው። ቴሪ ቪርኮሎን ከአፍሪቃ ህብረት ወደ አሁኑ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ሽግግሩ ሲካሄድ ወታደሮቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የስነ-ምግባርና ወታደራዊ ስልጠና መስፈርቶች ስለማሟላታቸው ፍተሻ ይደረጋል ተብሎ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከሰላም አስከባሪዎቹ መካከል የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መስፈርቶች የማያሟሉ ሊኖሩ ስለሚችሉ አሁን በርካታ ችግሮች የገጠሙት የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተልዕኮ መፈተሽ ይገባዋል ብለዋል።በጥፋተኝነት ወደየአገሮቻቸው የሚላኩ ወታደሮች በህግ የሚጠየቁበት አግባብ አለመኖሩ ተጨማሪ ክፍተት እንደሆነም ቴሪ ቪርኮሎን ይተቻሉ።

«ወታደሮች ጥፋት አጥፍተው አሊያም ወንጀል ፈጽመው ወደ አገሮቻቸው ሲላኩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ወታደር የሚልኩ አገሮች ባላቸው ስምምነት መሰረት ወታደር የሚልከው አገር በህግ የመጠየቅ ሃላፊነት አለበት። እነዚህ ወታደሮች ወደ አገራቸው ሲመለሱ ግን የታሰሩ አሊያም በህግ የተጠየቁ አይመስለኝም። ወታደሮቹ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ ላይ በነበሩበት ወቅት በባለስልጣኖቻቸው ለጥፋታቸው አለመጠየቃቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ካሉበት ችግሮች አንዱ ነው። ምክንያቱም ሰላም አስከባሪዎችን ያለመከሰስ መብት ያላቸው ያስመስላል።»

እሸቴ በቀለ

ገበያው ንጉሴ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ