1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ዘገባ

ሐሙስ፣ ግንቦት 29 2005

ኪተሩስ በዘገባቸው ኤርትራውያን ድንበር አቋርጠው ሲሸሹ ለሞት አደጋ ያጋልጣቸዋል ያሉትን ተኩሶ የመግደል ፖሊሲን ክፉኛ አውግዘዋል ። ኤርትራ ውስጥ የሚታሰሩ ሰዎች እዚያም የሚገኙ እስር ቤቶች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንም ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/18lLs

የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ይዞታ አሳሳቢ መሆኑን አንድ የተባበሩት መንግሥታት አጥኚ አስታወቁ ። በኤርትራ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ ያተኮረ ዘገባ ትናንት ጄኔቭ ውስጥ ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያቀረቡት የድርጅቱ ልዩ ዘጋቢ ሼልያ ኪተሩስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን መንግሥታቸው በሚፈፅመው የዘፈቀደ ግድያና ቁም ስቅል ምክንያት ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው እንደሚሰደዱ አስታውቀዋል ። ኬታሩስ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ በኤርትራ የሰብዓዊ መብት እንዲሻሻል ዓለምዓቀፉ ማህበረሰብ ጥብቅ ክትትል እንዲያደርግ አሳስበዋል ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፣ የኤርትራን የሰብዓዊ መብት ይዞታ እንዲያጠኑ እጎአ ህዳር 2012 ያሏቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዘርዝረዋል።

Flüchtlinge Eritrea
ስደተኞች በኢትዮጵያምስል AP

ሃላፊነቱን የሰጣቸው ሼልያ ኪተሩስ ትናንት ለድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሰጡት ገለፃ ኤርትራ ውስጥ በተለያየ መልኩ በሚደርስ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት በርካቶች ለአስከፊ ስደት እንደተዳረጉ አስታውቀዋል ። ኪተሩስ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ በኤርትራ እጅግ አሳሳቢ ያሏቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዘርዝረዋል።

«በዘገባው ካለ ፍርድ ሂደት የሚፈፀሙ ግድያዎች ፣ በሁኔታዎች አስገዳጅነት የሚከሰት የሰዎች መሰወር ፣ ሰዎች ከማንም ጋር እንዳይገናኙ አድርጎ ማሰር ፣ በዘፈቀደ መያዝ ና ቁም ስቅል ማሳየት እንዲሁም ሰብዓዊነት የሚጎድላቸው እስር ቤቶችን ጉዳይ አጉልቼ አውጥቻለሁ። ማለቂያው የማይታወቅ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ የመሰብሰብና የመደራጀት መብት እንዲሁም የእምነት ነፃነት አለመኖር በጣም ያሳስቡኛል »

ኪተሩስ በዘገባቸው ኤርትራውያን ድንበር አቋርጠው ሲሸሹ ለሞት አደጋ ያጋልጣቸዋል ያሉትን ተኩሶ የመግደል ፖሊሲን ክፉኛ አውግዘዋል ። ኤርትራ ውስጥ የሚታሰሩ ሰዎች እዚያም የሚገኙ እስር ቤቶች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንም ተናግረዋል ።   

« ብዙ ጊዜ ካሰባሰብናቸው የምስክሮች ቃሎችና ባለው መረጃ ሰዎች ከማንም ጋር እንዳይገናኙ ተደርገው የሚያዙት ለረዥም ጊዜ ነው ። ይህ የተለመደ የሆነ ይመስላል ። ሰዎቹን ለመቅጣት ወይንም ደግሞ ከሰዎቹ መረጃ ለማግኘት የሚጠቀሙበት ዘዴም ሊሆን ይችላል በተጨማሪም እስር ቤቶች እጅግ በከፋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ፣ በሰዎች የተጣበቡ መሆናቸውንና የምግብ የመድሐኒትና የመሳሰሉት እጥረት እንዳለም ሰምቻለሁ ። ሰዎች አንዴ እስር ቤት ከገቡ አይወጡም »

Israel Flüchtlinge aus Eritrea und Sudan
ኤርትራውያን ስደተኞች በእስራኤልምስል DW/U. Schleicher

ኪተሩስ እነዚህን መረጃዎች ያሰባሰቡት ወደ ጅቡቲና ኢትዮጲያ ከተሰደዱ ኤርትራውያን ነው ። ኤርትራ ሄደው መረጃዎቹን በቀጥታ ራሳቸው ለመሰብሰብ ቢፈልጉም ፈቃድ ስላላገኙ አልተሳካላቸውም ።

« ሃላፊነቱን በህዳር ወር እንደወሰድኩ የመጀመሪያው ሥራዮ ያደረግኩት አንድ ዲፕሎማትን ጨምሮ የኤርትራ ባለሥልጣናትን ማግኘት ነበር ። ከዚያ ሆኜም ወደ ኤርትራ መሄድ እንደምፈልግ አሳወቅኩ ነገር ግን እንደተሰጠኝ ሃላፊነት መልስ አልተሰጠኝም ። ከዚያ በኋላ ግን ለፕሬዝዳንንቱ በቀጥታ ደብዳቤ ፃፍኩ መልስ አላገኘሁም እስካሁን እየጠበቅኩ ነው ። »

ያም ሆኖ በዘገባቸው የጠቀሱዋቸው የኤርትራ መንግሥት ይፈፅማል የተባለው ሰዎችን እንዳሻው መግደል ፣ ማሰር ፣ ቁም ስቅል ማሳየትና የመሳሰሉትን በሃገሪቱ ውስጥ ተገኝተው ማረጋገጥ ባልቻሉበት ሁኔታ ፣ ዘገባቸው ምን ያህል የተሟላና ተዓማኒ ሊሆን እንደሚችል ተጠይቀው ሲመልሱ

  

Dawit Isaak
በ2001 የታሰረው ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ

«ብዙ ሰዎችን ነው ያነጋገርኩት ። በምንም ዓይነት መንገድ የማይዛመዱ የተለያዩ ሰዎች አነጋግረሽ ስዎች እንደሚጠፉና በዘፈቀደም እንደሚገደሉ ና እንደሚያዙ ቁም ስቅልም እንደሚደርስባቸው ተመሳሳይ ታሪኮች ሲነግሩሽ በዚህ መንገድ የሚደጋገፍ መረጃ ታገኛለሽ ። ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ የተለያዩ ሰዎች ተመሳሳይ ታሪኮች ነግረውናል ። እዚያ ስለተፈፀመው መረጃ ስንሰበስብ የተባለውን የሚያሳይ ስእል ነው የምናገኘው ።»

ኪተሩስ በኤርትራ የሰብዓዊ መብት ይዞታ እንዲሻሻል ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብና ከኤርትራም የሚጠበቀውን ተናግረዋል ።

« በመጀመሪያ ሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዟን ለማሻሻል ተጨባጭ እርምጃዎች መስውሰዷን በአይነቁራኛ መከታተል ያስፈልጋል ። ኤርትራም ድንበር ላይ ተኩሶ የመግደል ፖሊሲዋን በአስቸኳይ ማቆም አለባት ። »

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ይዞታ አጥኚ ስለሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ስላቀረቡት ዘገባ የኤርትራን መንግሥት አስተያየት ለማግኘት ሞክረን አልተሳካም ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ