1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ የደቡብ ሱዳን ሰላም ተልዕኮ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 23 2006

የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት በሳምንቱ መጀመሪያ እንዳስታወቀው፣ በዚህ በተያዘው የግንቦት ወር ብቻ ከ66,000 የሚበልጡ ደቡብ ሱዳናውያን ከመንደሮቻቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል 22,000 ወደ ጎረቤት ኢትዮጵያ ተሰደዋል።

https://p.dw.com/p/1C9uY
Ban Ki-moon mit Flüchtlinge in Südsudan 06.05.2014
ምስል Reuters


በደቡብ ሱዳን ካለፈው ታህሳስ ወር ወዲህ የሚካሄደውን ውጊያ ለማብቃት ካንዴም ሁለቴ የተደረሱትት ስምምነቶች በመጣሳቸው ብዙ ሕዝብ ሀገሪቱን መሸሽ ተገዶአል። የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባል ሀገራት በምሕፃሩ «ኡንሚስ» በደቡብ ሱዳን የጀመረውን ተልዕኮ እንዳዲስ ለማዋቀር በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በአንድ ድምፅ ውሳኔ አሳልፎአል። በዚሁ ውሳኔ መሠረት፣ ደቡብ ሱዳን እአአ ሐምሌ 2011 ዓም ከሱዳን ተገንጥላ ነፃ መንግሥት ባቋቋመችበት ጊዜ በሀገሪቱ የሰላሙን እና የፖለቲካ ሽግግሩን ሂደት እንዲያግዝ የተጀመረው የተመድ ተልዕኮ አሁን ትኩረቱን ሲቭሉን ሕዝብ ፣ በተለይ ሴቶችን እና ሕፃናትን ለመከላከል፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር፣ የሰብዓዊ ርዳታ ለማቅረብ እና የተኩስ አቁሙን ስምምነት ተግባራዊ በማስደረጉ ላይ ያሳርፋል። ምክር ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በሀገሪቱ መንግሥት ጦር ኃይል እና በአንፃሩ በሚዋጉ ዓማፅያን መካከል ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ በቀጠለው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተገደሉ እና ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡም ከተፈናቀሉ በኋላ ነው። የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ የ«ኡንሚስ »ን የስራ ዘመን እአአ እስከ ህዳር 30፣ 2014 ያራዘመ ሲሆን፣ ተቀናቃኞቹ ወገኖች በሀገሪቱ ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ የተጀመረውን ጥረት ማሰናከላቸውን ከቀጠሉ ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችልም አስጠንቅቋል።

Südsudan Flüchtlingslager in Bor
ምስል Reuters


የደቡብ ሱዳን ጊዚያዊ ሁኔታ አሳሳቢ እና ተለዋዋጭ በሆነበት ባሁኑ ጊዜ የተመድ በዚያ ያሠማራቸው 12,500 ውታደሮች እና 13,000 ፖሊሶች ሲቭሉን ሕዝብ ለመከላከል ባላቸው አቅም ሁሉ እንዲጠቀሙ ፈቃድ ሰጥቶዋል። በዓለሙ መንግሥታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተጠሪ ፍራንሲስ ማዲንግዴንግ ውሳኔ ትክክለኛ ቢሆንም ብዙ ሊደረግ የሚገባ ነገር እንዳለ አስታውቀዋል።
« የደቡብ ሱዳን መንግሥት በሀገሩ የቀጠለው ቀውስ አሳሳቢነት ሲታይ ሲቭሉን ሕዝብ ለመከላከሉ ተግባር አሁን ትልቅ ትኩረት የተሰጠበትን ድርጊት በደስታ በመቀበል አሞግሶዋል። ይሁን እንጂ፣ ተቀናቃኞቹ ወገኖች መረጋጋት እና ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ጥረት በያዙበት ባሁኑ ጊዜ አሳዛኝ ቀውስ እንደማይፈጠር ተስፋ እናደርጋለን ፤ ተግባራቸውን ለማከናወን ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋለጡት የ»ኡንሚስ» ወታደሮች አሁን እንዳዲስ የተዋቀረውን ተልዕኮ እና እስካሁን ካገኙት ተሞክሮ የቀሰሙትን ትምህርት መሠረት በማድረግ ወደፊት ሲቭሉን ሕዝብ፣ ራሳቸውን እና ሠፈራቸውን ለመከላከል የሚያስችላቸው ዝግጁነት እና አቅም እንደሚኖራቸውም ተስፋችን ነው። »

Südsudan Politik Soldaten
ምስል SAUL LOEB/AFP/Getty Images


የተመድ እስካሁን በመዲናይቱ ጁባ ከሚገኘው የደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋ ያን ያህል ጥሩ የሚባል ግንኙነት አልነበረውም። የጁባ መንግሥት የተመድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ከጋና ወደ ደቡብ ሱዳን የገባ የጦር መሳሪያ ጭነትን የግንባታ ቁሳቁስ ነው ሲል ለማሳለፍ መሞከሩ ከተጋለጠ በኋላ «ኡንሚስ» ዓማፅያኑን የጦር መሳሪያ አስታጥቆዋል በሚል መውቀሱ የሚታወስ ነው። እና አሁን የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ የኡንሚስ ተልዕኮ እንዳዲስ መዋቀሩ በፍራንሲስ ማዲንግዴንግ ብለውታል።


« ምንም እንኳን መንግሥታችን አሁን ተሻሽሎ በቀረበው ውሳኔ ላይ በተጠቀሱት አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ቁጥብነትቢኖረውም ፣ ጉዳዩ ሁላችንንም የሚያሳስብ እንደመሆኑ መጠን መረጃ በተሻለ መንገድ በመለዋወጥ ትብብራችንን ማጠናከር እንደምንችል እናምናለን። የደቡብ ሱዳን መንግሥት ዜጎቹን በመከላከሉ ረገድ ግዴታውን እና ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ ለመወጣት በሚያደርገው ጥረቱ ላይ ያለበትን ገደብ በሚገባ ያውቀዋል። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የታየው ጦርነት ትቶት ያለፈው ሥር የሰደደ ቁስል እስኪሽር ብዙ ጊዜ ይወስዳል። »


ማዲንግዴንግ የሚሉት ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ በመንግሥቱ ጦር እና የቀድሞ ምክትል ፕሬዚደንት ሪየክ ማቸርን በሚደግፉ ዓማፅያን መካከል በቀጠለው ውጊያ ይበልጡን ተባብሶዋል። በተመድ ግምት መሠረት፣ በውጊያው ሰበብ እስከ አውሮጳዊው ዓመት 2014 መጨረሻ ድረስ ወደ 1,3 ሚልዮን የሚጠጋ የሀገሪቱ ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ሊፈናቀል ይችላል። የተመድ እና በርካታ የርዳታ ድርጅቶች ተፈናቃዮች በየማሳዎቻቸው መስራት ባለመቻላቸው ሀገሪቱ የረሀብ ስጋት ሊደቀንባት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
በደቡብ ሱዳን የተመ የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ አስተባባሪ መሥሪያ ቤት ተጠሪ ቶቢ ላንዘር እንዳሉት፣ በሚቀጥለው ወር የሚጀምረው የዝናቡ ወራት ተፈናቃዩን ሕዝብ ለመርዳት የተጀመረውን ጥረት አዳጋች የሚያደርግበት ሁኔታ የተመድ እጅግ አሳስቦታል። የደቡብ ሱዳን መንግሥት በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኘው ሲቭል ሕዝብ ርዳታ በማቅረብ እንዲተባበር ላንዘር ጥሪ አስተላልፈዋል።


« ጥሩ እና ቀላሉ ርምጃ ፣ ባለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ ውጊያው ሲነሳ ለቀውት ወደ ወጡበት አካባቢ ለመመለስ ፈቃደኝነት ያሳየቱን ሰዎች መርዳት ነው። እነዚህን ሰዎች ተጨባጭ በሆነ መንገድ፣ ለምሳሌ፣ የግንባታ ቁሳቁስ፣ ፍራሾች፣ ለጤና ጥበቃ የሚያስፈልግ ያቅርብላቸው። ባጠቃላይ፣ ኑሯቸውን እንዳዲስ መገንባታ የሚያስችላቸውን ርዳታ ይስጣቸው። »

Südsudan - Abkommen
ምስል Reuters


ይኸው የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ሰሞኑን ያስተላለፈው አዲስ ውሳኔ «ኡንሚስ»ን በአሁኑ ጊዜ በሠፈሩ ያሉትን ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉትንም ለመከላከል እንደሚያስችል በጁባ የሚገኙት የኡንሚስ ቃል አቀባይ አርየን ክዌንቴ ገልጸዋል።


«አሁን ትኩረታችንን ሲቭሉን ሕዝብ በመከላከሉ ተግባር ላይ ማሰረፍ ይሆናል፣ «ኡንሚስ» ሠፈር ከለላ ያገኙትን ከ90,000 የሚበልጡትን ተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች አካባቢዎች ለውጊያው አደጋ የተጋለጡትን በ10,000ዎች የሚቆጠሩትንም ደህንነት ለመጠበቅ እና ያኃይሉን ተግባር ከነሱ ለማራቅ ነው የምንሰራው። »


የ«ኡንሚስ» ወታደሮች እና ፖሊሶች ሲቭሉን ሕዝብ ለመከላከል ባላቸው አቅም ሁሉ እንዲጠቀሙ ፈቃድ የሰጠው ውሳኔ ግን «ኡንሚስ» ተቀናቃኞቹ ወገኖች በሚያካሂዱት ውጊያ በቀጥታ ጣልቃ ሊገቡ ያደርጋል በሚል አንዳንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች ያሰሙትን ስጋት ወይዘሮ አርየን ክዌንቴ አይሆንም ሲሉ ስጋቱን አርግበዋል።


« ሀሳቡ ሰላም አስከባሪው ጓድ ከየትኛውም ተፋላሚ ቡድን ጋ በቀጥታ ውጊያ ውስጥ መግባት እንደሌለበት ያሳስባል፣ በዚህ ፈንታ ሦስት ባታልዮን ያለው ጓድ የሰላሙን ሂደት እንዲደግፍ፣ ተፋላሚዎቹ ወገኖች በመጀመሪያ እአአ ባለፈው ጥር 23፣ 2014 ዓም ፣ ከስድስት ወራት በፊት የፈነዳውን ውጊያ ለማቆም የፈረሙትን እና ወዲያው የተጣሰውን ፣ በኋላም ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ሪየክ ማቸር እአአ ባለፈው ግንቦት ዘጠኝ የደረሱትን የተኩስ አቁም ስምምነት ማስከበር እና መቆጣጠር፣ እንዲሁም፣ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን፣ በምሕፃሩ፣ የ«ኢጋድ» ቴክኒካዊ ኮሚቴ ተግባር እንዲያስተባብር ነው የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የወሰነው። »

Symbolbild - Soldaten Südsudan
ምስል Getty Images


ከጥቂት ጊዜ በፊት የተመድ ዋና ፀሐፊ ፓን ኪ ሙን ደቡብ ሱዳንን የጎበኙበት እና አዲሱ ውሳኔ በ«ኡንሚስ» እና በደቡብ ሱዳን መንግሥት መካከል ሻክሮ የቆየውን ግንኙነት እንዳሻሻለው ታዛቢዎች ቢገልጹም፣ ውሳኔው ኡንሚስ እስካሁን ያካሄደው የሀገር ግንባታ መክሸፉን ያሳየ አድርገው ተመልክተውታል። የኡንሚስ ቃል አቀባይ ይህንን ሀሳብ በፍፅም አይጋሩትም።


« የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ተልዕኮው ከሽፎዋል ብሎ አያስብም። ምክር ቤቱ ካለፈው ታህሳስ ወዲህ የተፈጠረው ውዝግብ ያስከተለውን መዘዝ ለመቀነስ እንዲችል ለማድረግ ነው ተልዕኮውን ያሻሻለው። እናም ምክር ቤቱ ከአዲሱ ሁኔታ ጋ የሚስማማ ርምጃ መውሰዱ ኃላፊነት የተመላው አሰራር ነው፣ ሀገሪቱ በወቅቱ የሀገር ግንባታ አይደለም የሚያስፈልጋት። ሀገሪቱ የምትገኝበትን የቀውስ ሁኔታ ተገንዝበን በዚህ አንፃር ተገቢውን መልስ መስጠት ነው የሚጠበቅብን። »

አርያም ተክሌ
ማንተጋፍቶት ስለሺ