1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተ.መ.ድ ጸጥታ ምክር ቤት በሊቢያ ላይ ዉሳኔ አሳለፈ

እሑድ፣ የካቲት 20 2003

የተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ም/ቤት የሞአማር ጋዳፊ አገዛዝ የሊቢያን ህዝብ እንቅስቃሴ ለመቅጨት በሲቪሉ ህዝብ ላይ ያደረሰዉን ጥቃት በማስመልከት በሞአመር ጋዳፊ እና ተከታዮቻቸዉ ላይ ዉሳኔዉን አጸደቀ።

https://p.dw.com/p/R4cc
በተባበሩት መንግሥታት መቀመጫ በኒውዮርክ የሊቢያ አምባሣደር ሞሐመድ ሻልጋምምስል AP

የጸጥታዉ ምክር ቤት ትናንት ምሽት በጠራዉ ዝግ ስብሰባ በጋዳፊ መንግስት ላይ የጦር መሳርያ ማዕቀብ፣ ጋዳፊና ተከታዮቻቸዉ ወደ ሌላ አገራት እንዳይሻገሩ ማገድ እና በሌሎች አገሮች ያላቸዉን ማንኛዉንም አይነት ሃብት በቁጥጥር ማዋል ነዉ። እንደ ተባበሩት መንግስታት ጸጥታዉ ምክር ቤት፣ የጋዳፊ መንግስት በሲቪል ሰልፈኞች ላይ የፈጸመዉ ኢሰብአዊ እርምጃ ለዴንሃግ የጦር ፍርድ ቤት ክስ ሳይበቃዉ አይቀርም። በሌላ በኩል የጋዳፊን አገዛዝ የከዱትና በተባበሩት መንግሥታት መቀመጫ በኒውዮርክ የአገሪቱ አምባሣደር የሆኑት ሞሐመድ ሻልጋም የጸጥታው ም/ቤት አስከፊውን አገዛዝ ለማስወገድ ፈጣን ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ባን-ኪ-ሙንም በጉዳዩ የሚደረግ መዘግየት የሟቹን ቁጥር የሚያሳድግ እንደሚሆን እያስገነዘቡ ነው። እንደ ተባበሩት መንግስታት ገለጻ በሊቢያ በደረሰዉ ቀዉስ እስካሁን ከአንድ ሽህ በላይ ህዝብ ህይወቱን አጥቶአል፣ በሳምንቱ የሊቢያ ቀዉስ ብቻ ሶስት መቶ ሽህ የሊቢያ ዜጎች ወደ ቱኒዚያ እና ግብጽ ፈልሰዋል።

በሌላ በኩል በሊቢያ ትልቁ የነዳጅ ዘይት ማምረቻ የሚገኝበትና ከሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፑሊ ሃምሳ ኪሎ ሜትር ላይ ርቆ የሚገኘዉ አል-ዛዊያ ቁልፍ ከተማ በታጠቁ ጸረ ሞአመር ጋዳፊ መንግስት ንቅናቄ ሃይላት በቁጥጥር ስር መግባቱ ዛሪ ተገልጾአል።


AT/MM/DW