1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተማሪዎች ተቃውሞ በአዲስ አበባ

ማክሰኞ፣ የካቲት 29 2008

የአዲስ አበባ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የፖሊስ የኃይል ርምጃ እንዲያበቃ በመጠየቅ ዛሬ በከተማይቱ ተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን ዜና ምንጭ ሮይተርስ ዘገበ።

https://p.dw.com/p/1I9Sy
Blick aus meinem Fenster Addis Abeba Äthiopien
ምስል Solomon Mengist

[No title]

አደባባይ የወጡት ተማሪዎች የተቀናጀውን የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ የከተማ ማስፋፊያ እቅድን በመቃወም ከጥቂት ወራት ወዲህ የተካሄዱትን ሰልፎች ተከትሎ ፖሊስ አስፋፍቶታል ያሉትን የኃይል ርምጃ ነው የተቃወሙት። መንግሥት እቅዱን ባለፈው ታህሳስ ቢሰርዘውም፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዛሬ፣ «እኛ ሽብርተኞች አይደለንም፣ የኦሮሞ ሕዝብን መግደል አቁሙ» የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ በሁለት አቅጣጫዎች ፣ ለኢትዮጵያ ዋና ርዳታ አቅራቢ ወደሆነችው ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ማምራታቸውን ዜና ምንጩ አክሎ አስረድቶዋል። ስለተቃውሞ ሰልፉ የመንግሥት ቃል አቀባይ አስተያየት እንዲሰጡ ዜና ምንጩ ላቀረበው ጥያቄ መልስ እንዳላገኘ ገልጾዋል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኦሮሚያ ክልል ለተነሳው ቅሬታ መንግሥታቸው መፍትሔ እንደሚፈልግለት ቀደም ሲል ቃል መግባታቸው እና ዓማፅያን ቡድኖች ለሁከቱ ተጠያቂዎች ናቸው ሲሉ መውቀሳቸው የሚታወስ ነው። ዜና ምንጩ የመብት ተሟጋች ቡድኖችን እና በዩኤስ አሜሪካ ያሉ ተቃዋሚዎችን በመጥቀስ እንዳመለከተው፣ የመንግሥቱ እቅድ በቀሰቀሰው ከፍተኛ ተቃውሞ እስከ 200 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል። የመንግሥት ባለስልጣናት የሞተው ሰው ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ቢያስታውቁም፣ ትክክለኛውን ቁጥር አልገለጹም።

ስለ ሁኔታዉ ነጋሽ መሐመድ የአዲስ አበባዉን ወኪላችን ዮሐንስ ገ/እግዚአብሄርን በስልክ ጠይቆት ነበር።

አርያም ተክሌ

ዮሐንስ ገ/እግዚአብሄር

ነጋሽ መሐመድ