1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተራዘመው የናይጄሪያ ምርጫ እሰጥ አገባ

ሐሙስ፣ የካቲት 5 2007

የካቲት 7 ቀን 2007 በናይጄሪያ ሊካሄድ የታቀደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በስድስት ሳምንታት እንዲራዘም የሃገሪቱ ነጻ የምርጫ ኮሚሽን( Independent National Electoral Commission) ያሳለፈው ውሳኔ ከፍተኛ ትችት ገጥሞታል። የሃገሪቱ ጦር ሰራዊት በናይጄሪያ የዴሞክራሲ የስርዓት ግንባታ ጣልቃ እየገባ ነው የሚል ስጋት አይሏል።

https://p.dw.com/p/1EYdp
Nigeria Demonstration gegen Verschiebung der Wahl 7. Februar 2015
ምስል picture-alliance/AP Photo/O. Gbemiga

የፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን የጸጥታ ሹማምንት የካቲት 7 ቀን ሊካሄድ ቀነ ቀጠሮ የተቆረጠለትን የናይጄሪያ ምርጫ ደህንነት ዋስትና መስጠት አንችልም በማለታቸው የምርጫው ቀን እንዲራዘም የሃገሪቱ ነጻ የምርጫ ኮሚሽን ውሳኔ አሳልፏል። በእነዚህ ሳምንታት የናይጄሪያ ጦር ለስድስት አመታት ሞክሮ ያቃተውን የቦኮ ሃራም ሰርጎ ገብ ጥቃት የማስቆም የቤት ስራ ተጥቶታል። ውሳኔው በናይጄሪያውያንም ይሁን በምዕራቡ ሃገራት ተቀባይነት አላገኘም። በምርጫው የጉድ ላክ ጆናታን ጠንካራ ተፎካካሪ ናቸው የተባሉት የቀድሞ ሜጀር ጄኔራል ሙሃመዱ ቡሃሪ በምርጫ አስፈጻሚው ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ አላቸው።
«የናይጄሪያ ነጻ የምርጫ ኮሚሽን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። እንደ ናይጄሪያዊና እንደ ፕሬዝዳንታዊ ተወዳዳሪ በምርጫ ኮሚሽኑ ውሳኔ የተፈጠረውን መከፋት እና ተስፋ መቁረጥ እኔም እጋራለሁ። ምርጫው አንድ ሳምንት ሲቀረው የመጣው ውሳኔ ብዙ ጥያቄዎችን ያስከትላል።»
የምርጫ ኮሚሽኑ ውሳኔ ተቀባይነት ያገኘው በፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን ፓርቲ ብቻ ነው። የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ቦኮ ሃራም ደቀነ የተባለውን የጸጥታ ስጋት እንደ ቅድመ ሁኔታ በመጠቀም ናይጄሪያ የወሰነችው ውሳኔ ተገቢ አይደለም ሲሉ ተችተዋል። ዶ/ር አቡበከር ኡማር ካሪ ናይጄሪያዊ የፖለቲካ ተንታኝ ናቸው።

«በቅዳሜው የምርጫ ኮሚሽን ውሳኔ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን ወደ ኋላ ተመልሷል የሚለውን አስተያየት እጋራለሁ። እንደ ናይጄሪያ ላለ በቀላሉ ሊንኮታኮት ለሚችል ዴሞክራሲ ውሳኔው አሳሳቢ ነው። የጦር ሰራዊቱ ፖለቲካዊ ስልጣንን ነው የነጠቀው። ከፍተኛውን ስልጣን በመንጠቅ በሂደት አንገብጋቢ ጉዳዮችን የመወሰን ስልጣን እየተቆናጠጡ ነው። የጦር ሰራዊቱ በገለልተኝነት ሊቆም ሲገባው ተቃራኒውን እያደረገ ነው። ይህ ደግሞ ለፖለቲካ በጣም አደገኛ ነው።»
የምርጫ ኮሚሽኑ ውሳኔ ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን ከሙሃመዱ ቡሃሪ የገጠማቸውን ፉክክር ለማኮላሸት የተደረገ መሆኑን የሚናገሩ ተንታኞች ጥቂት አይደሉም። የናይጄሪያ ጸጥታ አማካሪ ሳምቦ ዳሱኪ ግን የምርጫው ቀን የተራዘመው በፖለቲካዊ ምክንያት አለመሆኑን ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤ.ኤፍ.ፒ. ተናግረዋል። እንደ ሳምቦ ዳሱኪ ከሆነ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በየካቲት 28 የሚካሄደው ምርጫ በድጋሚ የሚራዘምበት ምክንያት አይኖርም።
ለናይጄሪያውያን ለምርጫ ጸጥታ የጦር ሰራዊቱ በምክንያትነት መቅረቡ አልተዋጠላቸውም። የምርጫ ደህንነት ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው የሃገሪቱን ፖሊስ እና ማህበራዊ የደህንነት ተቋማትን በመሆኑ አሁን የቀረበው ምክንያት ተገቢ አይደለም። በናይጄሪያ ዴሞክራሲና ልማት ማዕከት ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ጂቦ ኢብራሂም ኮሚሽኑ ምርጫ የማስፈጸም ግዴታውን የቦኮ ሃራምን ሰርጎ ገብ ጥቃት ከመዋጋት ጋር ለማገናኘት መሞከሩ እጅጉን አደገኛ መሆኑን ይናገራሉ።
«የቦኮሃራምን ጥቃት ለማስቆም የሚደረገው ትግል ስድስት አመታት አስቆጥሯል። አሁን በስድስት ሳምንታት ውስጥ የቡድኑን ጥቃት እናስቆማለን የሚለው ነገር ፍጹም ተዓማኒነት የሌለው ነገር ነው። ከስድስት ሳምንታት በኋላ የቦኮ ሃራም ጥቃት ካልቆመ እንደ ገና ምርጫውን ሊያራዝሙ ነው። ይህ ደግሞ ህገ-መምግስታዊ ቀውስ ይፈጥራል። ምክንያቱም በህገ-መንግስቱ ከሰኔ 29 በፊት ምርጫው መደረግ አለበት። እነሱ ደግሞ ህገ-መንግስታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ በመፍጠር የዴሞክራሲያዊ መንግስትን ለማብቃት በመጣር ላይ ናቸው። ለዴሞክራሲ ብዙ መንገድ ተጉዘናል።ብዙ ታግለናል። ማንም የዚህን ሃገር ዴሞክራሲ እንዲቀለብስ አንፈቅድም።»
የናይጄሪያ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ተወዳዳሪ ሙሃመዱ ቡሃሪ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ማጠናቀቅና አለማጠናቀቃቸው በፍርድ ቤት እየተጣራ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቅ በፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር አንዱ ቅድመ ሁኔታ ነው። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2011 በተካሄደው የናይጄሪያ ምርጫ ማግስት ለተከሰተውና 800 ሰዎች ለሞቱበት ብጥብጥ ቡሃሪ እጃቸው አለበት የሚል ክስም ቀርቦባቸዋል። ቡሃሪ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን በብጥብጡም እጃቸው እንደሌለበት ተናግረዋል። ቢመረጡ ግን የአሁኑን ፕሬዝዳንት ጉድ ላክ ጆናታንን ጨምሮ የናይጄሪያን ሙሰኞች ዘብጥያ አወርዳለሁ ያሉት ነገር ጠላት ሳያበዛባቸው አልቀረም።
እሸቴ በቀለ
ተክሌ የኋላ

Wahlkampf in Nigeria 2015 Goodluck Jonathan
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Alamba
Wahlkampf in Nigeria 2015 Muhammadu Buhari
ምስል AFP/Getty Images/P. Utomi Ekpei
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ