1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት መንግሥታት ዓመታዊ የልማት ዘገባ

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 5 2000

የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ በአሕጽሮት ዩንክታድ ሰሞኑን ዓመታዊ የልማት ዘገባውን አውጥቷል። ጥናቱ እንዳመለከተው በያዝናውና በሚቀጥለው ዓመት የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ማቆልቆሉ የማይቀር ጉዳይ ነው።

https://p.dw.com/p/FFUV
ሃይነር ፍላስቤክ
ሃይነር ፍላስቤክምስል AP

የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ UNCTAD የዓለም ሕብረተሰብ ድርጅት ጠቅላይ ጉባዔ ቁዋሚ አካል ሆኖ የተመሠረተው እ.ጎ.አ. በ 1964፤ ማለትም ከ 44 ዓመታት በፊት ነበር። ጽሕፈት ቤቱ ጄኔቫ ላይ የሆነው ተቁዋም 193 ዓባል ሃገራት ሲኖሩት ከ 2005 ዓ.ም. ወዲህ የሚመራውም በታይላንዱ ተወላጅ በሱፓቻይ ፓኒችፓክዲ ነው። ዩንክታድ ቀደም ባሉት ዓመታት ለታዳጊ አገሮች የንግድ ሁኔታዎችን ለማቃለልና ዕዳ ቅነሣን ለማስፈን የረዱ ጠቃሚ ጥረቶችን አንቀሳቅሷል። ምንም እንኳ አሣሪ ውሣኔዎች ባይከተሉም።

የቀድሞው የዩንክታድ ጠቅላይ ጸሐፊ ሩበንስ ሪኩፔሮ ድርጅቱን በ 2000 ዓ.ም. የባንግኮግ አሥረኛ መደበኛ ጉባዔው በዓለም አጽናፋዊነት ጉዳይ የዓለም ፓርላማ ነው ሲሉ ነበር የተናገሩት። እርግጥ አሣሪ ሕጋዊ ውሎች ከሚሰፍኑበት በ 1995 ዓ.ም. ከተመሠረተው ከዓለም ንግድ ድርጅት ሲነጻጸር ዩንክታድ ክብደት እያጣ መምጣቱም አልቀረም። ሆኖም ድርጅቱ ሰሞኑን ያወጣው ዓመታዊ የልማት ዘገባ ሁሉም ነገሩ አዲስ ባይሆንም ክብደት የሚሰጠው ነው። የጉባዔው ጠቅላይ ጸሐፊ ሱፓቻይ ፓኒችፓክዲ የዓለም ኤኮኖሚ ከዕርጋታ የራቀና የወደፊት ሂደቱም ያልተረጋገጠ ሆኖ እንደሚገኝ ነው ያስገነዘቡት።

በዕውነትም በድርጅቱ ዘገባ የቀረቡት መረጃዎች ይህንኑ ሃቅ ነው የሚያንጸባርቁት። በዚህ በያዝነው 2008 ዓ.ም. ሂደት የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ከ 2,9 ከመቶ ይበልጣል ተብሎ አይጠበቅም። በበለጸጉት መንግሥታት ዘንድ እንዲያውም ዕርምጃው የመነመነ ነው። ለምሳሌ በጀርመን ዘገባው እንደጠቆመው ዕድገቱ በ 1,8 ከመቶ የተወሰነ ነው የሚሆነው። በአንጻሩ ራመድ ያሉት አዳጊ ሃገራት ዕድገት በ 7 ከመቶ ተገምቷል። በሌላ በኩል የዩንክታድ ዘገባ አጠናቃሪዎች የተከታዩን 2009 ዓ.ም. ሂደት በተመለከተ ጭብጥ ትንበያ ማድረጉን ብዙም አልደፈሩትም። ግን እንደ ድርጅቱ የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ እንደ ሃይነር ፍላስቤክ ከሆነ አድማሱ በጭጋግ የተሸፈነ ነው የሚመስለው።

“በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት ሃገራት ውስጥ ግልጽ የሆነ ማቆልቆል እንደሚኖር እንጠብቃለን። ይህ ሚስጥር አይደለም። በየቦታው የሚታየው የኤኮኖሚ ቀውስ አዝማሚያ ነው። እና በአጠቃላይ ቢበዛ የአንድ ከመቶ ዕድገት ማድረግ ይቻል ይሆናል”

ፍላስቤክ እንደሚሉት በወቅቱ በተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኙት ታዳጊዎቹ አገሮች ናቸው። ቢቀር በዚህ በያዝነው 2008 ዓ.ም. ከስድሥት እስከ ሰባት በመቶ ዕድገት ሊያደርጉ ይችላሉ። ሆኖም ግን ሂደቱ ከዓመቱ ባሻገር ቀጣይነት አይታይበትም።

“በ 2009 ዕድገቱ ጥቂትም ቢሆን ደከም ማለቱ የማይቀር ነው። ሆኖም ታላላቆቹ አዳጊ አገሮች ቀውስ መሰል ማቆልቆል ላይ እንደማይወድቁ ገና ተሥፋ እናደርጋለን። እርግጥ ይህ ከትክክለኛ ግምት ይበልጥ ተሥፋ ነው”

የዩንክታድ ዘገባ ደራሲያን ለዚህ ለደበዘዘው የዓለም ኤኮኖሚ ሁኔታ ቀደምት ምክንያቶች አድርገው ያስቀመጡት የአሜሪካን የቤት ዕዳ ቀውስ፣ የጥሬ ሃብቶችን መወደድና በፊናንሱ ገበዮች ላይ ያለውን ከፍተኛ ውጣ ውረድ ነው። በዩንክታድ የኤኮኖሚ ባለሙያ በሃይነር ፍላስቤክ ዕምነት ከዚህ እየተባባሰ ከሄደው አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የለየለት የኤኮኖሚ ቀውስ ሊጠበቅ የሚችል ነገር ነው። አይደርስም ሊባል አይቻልም።

“ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ከዚህ ቀደም የደረሰ ጉዳይ ነው። በ 1929/30! የዛሬውንም ሁኔታ ብዙ ሰዎች ከዚያ ጊዜ ያመሳስሉታል። ለምን? አሜሪካ ውስጥ አስደንጋጭ ወይም አስደንጋጭ ሊባል የሚችል ሂደት በመከሰቱ! ይህም እየተጠናከረ እንዳይሄድ በጣሙን የሚያሰጋ ነው። አሜሪካ ውስጥ በወቅቱ የቤቶች ዋጋ እየተወደደ ሄዷል። ይህ ደግሞ የማቆልቆል ሂደትን ማስከተሉ አልቀረም። በዕዳ የተወጠሩት ሰዎች ሁኔታ በየዕለቱ እየባሰ ነው። በመሆኑም መንግሥት በጉዳዩ በሰፊው ጣልቃ እንዲገባ ለማድረግ ይታሰባል። የቤቶች ዋጋ ውድቀት እንዲገታ የሰው ችግር እንዲቃለል ለማድረግ”

ዩንክታድ በዘገባው የነዳጅና የሌሎች ጥሬ ዕቃዎችን ዋጋ ወደ ላይ በሚገፉት ትርፍ አጋባሾች ላይም ጠንካራ ትችት ሰንዝሯል። በገበዮችና ምርቶች ላይ ግልጽ አሠራር አለመኖሩም ተነስቷል። እርግጥ ይህ ወይም ያ ተብሎ ስም አልተጠቀሰም። ሆኖም ጥብቅ ደምብና ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ ነው ዩንክታድ ያስገነዘበው። ትግሉ እንዴት ሊካሄድ ይችላል? አሁንም ሃይነር ፍላስቤክ!

“ቀላሉ መንገድ ሁልጊዜም መንግሥታት ችግሩን መጋተራቸው ነው። እንበል የራሳቸውን የጥሬ ሃብት ክምችት ማድረግ። እና መንግሥታትና ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ችግሩን መቁዋቁዋም አስፈላጊ ሲመስላቸው ይህንኑ ማድረግ አለባቸው። ይህ በአጠቃላይ ሲታይ ቀረብ ያለው ዕርምጃ ይሆናል። ከዚህ ባሻገር በተለይ በምግብ ምርቶች አኳያ የትርፍ ማጋበስ ድርጊትን ማገድ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ለነዚህ ድርጊቶች መንገድ የሚከፍቱትን ሕጋዊ ቀዳዶች መድፈኑ በፍጥነት እንዲወገዱ የሚያደርግ ነው”

የዩንክታድ ዘገባ የዋጋ መናር ተጋኖ እንዳይታይ የሚያስጠነቅቅም ነው። የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ወለዱን በማሳደግ እንዳይቀጥልም ያስገነዝባል። በድርጅቱ ዕምነት ይህን መሰሉ ዕርምጃ በዓለምአቀፉ ዕድገት ላይ የቀውስ አደጋን የሚያባብስ ነው የሚሆነው።

የጀርመን መዋዕለ-ነዋይ በአፍሪቃ

የብዙዎቹ የአፍሪቃ አገሮች ኤኮኖሚ ከዚህ ቀደም ባልታየ ጥንካሬ በማደግ ላይ ነው የሚገኘው። ታዲያ በዚሁ መጠን የውጭ መዋዕለ-ነዋይ በለቤቶችን ትኩረት መሳቡም አልቀረም። ይሁንና የጀርመን ኩባንያዎች ተሳትፎ በዚህ ረገድ ባለበት ዝቅተኛ ሆኖ ነው የቀጠለው። በተለይ ቀጥተኛ የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት አፍሪቃ ድሃ ክፍለ-ዓለም ሆና በመታየቷ ጨርሶ የለም ለማለት ይቻላል። ይህ እርግጥ ትልቅ ስህተት ነው።

በዚህ በጀርመን በተለይ መለስተኛ ኩባንያዎችን የሚያማክሩት የምጣኔ-ሐብት ማራመጃና የውጭ ኤኮኖሚ ፌደራል ማሕበር ተጠሪ ሽቴፋን ሽሚትስ የጀርመን ኩባንያዎች አፍሪቃ ውስጥ ስላለው የንግድ ዕድል በቂ መረጃ የላቸውም ይላሉ።

“እርግጥ ፌደራሉን የውጭ ኤኮኖሚ ኤጀንሢይ የመሳሰሉ ተቁዋማት በአፍሪቃ ላይ መረጃዎችን ያቀርባሉ። ግን ስለ ቻይና ወይም ስለ ሩሢያ ከሚቀርበው ሲነጻጸር በጣም ትንሽ ነው። እና አፍሪቃንም በተመለከተ የበለጠ የመረጃ አገልግሎት ሊሰጥ ይገባል ባይ ነኝ። እዚያ የጀርመን የኤኮኖሚ ዘርፍ ሊመለከተው ያልቻለ ጠቃሚ የንግድ ዕድል ነው ያለው”

ሆኖም ሽሚትስ እንደሚሉት በአፍሪቃ የሚታየው ያለፉት ዓመታት ዕድገት ልብ አልተባለም። በዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቁዋማት ግምት መሠረት በርከት ባሉ የአፍሪቃ አገሮች ኤኮኖሚው በዓመት ከአምሥት በመቶ በላይ እያደገ ነው። ከነዚሁ ነዳጅ ዘይት ያላቸው ሃገራት ደግሞ በዋጋው መጨመር ተጠቃሚ በመሆናቸው ዕድገታቸው ከስምንት በመቶ ይበልጣል። ሌሎች ኮኮንና ቡናን የመሳሰሉ የእርሻ ምርቶች የሚያቀርቡ አገሮችም እንዲሁ ከፍተኛ ዕድገት በማድረግ ላይ ናቸው። ዕድገቱ የኢንዱስትሪና የፍጆት ምርቶችን ፍላጎትም ከፍ እያደረገ ነው።

ሆኖም በጀርመን የንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቤት የአፍሪቃ ልማት ጉዳይ ሃላፊ የሆኑት ሃይኮ ሽቪደሮቭስኪ እንደሚሉት የአፍሪቃና የጀርመን የንግድ ልውውጥ ከቀድሞው ምንም ያህል አልተለወጠም።

“አዘውትረን የምንታዘበው ከታዳጊ አገሮች ጋር የሚደረገው ንግድ አሁንም በቀድሞ መልኩ እንደቀጠለ መሆኑን ነው። ይህም ጀርመን ጥሬ ዕቃዎች ገዝታ ታስገባለች፤ በአንጻሩ የምርት መኪናዎችን፣ መሣሪያዎችንና የንጥረ-ነገር ኢንዱስትሪ ምርቶችን ትልካለች ማለት ነው”

ምንም እንኳ የሚላከው ምርት መጠን ቢጨምርም የጀርመን ኩባንያዎች መዋዕለ-ነዋይ ወደ አፍሪቃ በማሻገሩ ረገድ የሚሰጡት ትኩረት በጣም አነስተኛ ሆኖ ይገኛል። ከጀርመን ወደ አፍሪቃ የተሻገረው ቀጥተኛ ካፒታል በወቅቱ 36 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ከሚደርሰው ከጠቅላላው የውጭ ኩባንያዎች ድርሻ አንድ-ስድሥተኛው ገደማ ቢጠጋ ነው። እርግጥ አብዛኛው የሚመነጨው ከቻይና መሆኑም መዘንጋት የለበትም።

ሕዝባዊት ቻይናን ካነሣን የቻይና የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ በአፍሪቃ መስፋፋት በምዕራቡ ዓለም፤ በዚህ በጀርመንም ብዙዎች ኩባንያዎችን ከተኙበት መቀስቀሱ አልቀረም። ሁኔታው ጀርመንና አውሮፓ በአፍሪቃ ላይ ጠንከር አድርገው እንዲያተኩሩና የንግድ ዕድላቸውን እንዲያጤኑ እያደረገም መሄድ ይዟል። ሽቪደሮቭስሊ መዋዕለ-ነዋዩ ቢስፋፋ የአፍሪቃን የልማትና የድህነት ችግሮች ለመፍታትም ይበጃል ባይ ናቸው።

“የሥራ መስኮችን መፍጠር፣ በቦታው ለሕዝቡ ትምሕርትና ከፍተኛ ሥልጠና መስጠት ታላቅ ጠቀሜታ አለው። ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማረጋገጥ ከዚህ የተሻለ መንገድ ሊታሰብ አይችልም”

በዚህ በኩል በግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ በኩባንያዎች መካከል የሚደረገው ትብብር እጅግ ጠቃሚ ነው፤ ሽቪዶቭስኪ እንዳስረዱት! እርግጥ በአፍሪቃ አለ የሚባለው የኤኮኖሚ ዕድገት፤ የውጩ መዋዕለ-ነዋይም መጠናከር ለሕዝብ ለሚጠቅም ማሕበራዊ ልማት አመቺ ሆኖ ሊራመድ ከቻለ! እስካሁን ይህ ሆኗል ለማለት ሲበዛ ያዳግታል።