1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ዳርፉር፧

ሰኞ፣ ነሐሴ 28 1999

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ ባን ኪ ሙን፧ የሱዳን መንግሥትና የዳርፉር አማጽያን፧ ውዝግቡ ይወገድ ዘንድ እንዲወያዩ ለመገፋፋትና ጠንከር ያለ ሰላም አስከባሪ ኃይል የሚሠማራበትን መንገድ ለመጥረግ ዛሬ፧

https://p.dw.com/p/E0aR
የዳርፉር፧ ስደተኞች
የዳርፉር፧ ስደተኞችምስል picture-alliance/ dpa/dpaweb
ካርቱም ሳይገቡ አይቀሩም። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳን የሀገር አስተዳደር ሚንስቴር የፍትኅና የእኩልነት ንቅናቄ፧ እንዲሁም የሱዳን ነጻ አውጭ ጦር የአንድነት አንጃ፧ የተሰኘው፧ ሁለቱም አማጽያን ኃይሎች፧ ዋድ ባንዳ፧ ኮርዶፋን ውስጥ ባለፈው ሳምንት 41 ፖሊሶችን መግደላቸውን የገለጠ ሲሆን፧ ከአማጽያኑ አመራር አባላት መካከል የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪው፧ ሱሌይማን ጃሙስ ድርጊቱን አውግዘዋል። ስለዳርፉርና የባን ኪ ሙን ጉብኝት የቀረበው ዘገባ ቀጥሎ ይሰማል።
የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ፧ በዳርፉር ጠንካራ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሠማራ ግፊት የሚያደርጉት፧ በሱዳን ላይ ማዕቀብ ሊጣል ይችላል እየተባለ በሚነገርበት ሰዓት ነው። ባለፈው ዓርብ የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ጎርደን ብራውንና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ፧ እገዳ እንዲደረግ ረቂቅ ውሳኔውን እናንቀሳቅሳለን በማለት ቢዝቱም፧ የቻይናው አምባሳደር፧ ሊ ቸንግዌን፧ ትናንት በሰጡት መግለጫ ላይ፧ ሰላምን ለማሥፈንና ለማረጋጋት፧ ዛቻ አንዳች ፋይዳ አይገኝም ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ዛሬ ካርቱም ከገቡ በኋላ ወደ ዳርፉር የሚያመሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ ባን ኪ ሙን፧ በዚያ አንድ ቀን በማሳለፍ፧ የህዝቡን ሥቃይ በዓይናቸው ብሌን የማየት ዕድል ያገኛሉ ነው የተባለው። እ ጎ አ ከየካቲት 2003 ዓ ም አንስቶ፧ የሱዳን መንግሥት ጦር ሠራዊትና የዳርፉር አማጽያን፧ የጭካኔ ውጊያ ከማካሄድ የቦዘኑበት ጊዜ የለም። የኃይሉ እርምጃ እስካሁን ሊገታ አለመቻሉ፧ ባን ኪ ሙንን አላሳዘነም አይባልም።
«በቅርቡ፧ ዳርፉር ውስጥ የኃይል እርምጃ ይበልጥ ማገርሸቱና ባለፈው ሳምንት ብቻ በመቶ የሚቆጠሩ መገደላቸው በጥልቅ አሳስቦኛል።«
በዳርፉር የጅምላ ጭፍጨፋው ከተጀመረ ከ አራት ዓመት ወዲህ ባን ኪ ሙን፧ ውዝግቡ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሁሉ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ያቆሙ ዘንድ ጠይቀዋል።
«ከዚህም በተጨማሪ፧ የሱዳን መንግሥት፧ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዑክ፧ የሰብአዊ እርዳታ ጉዳይ ተጠሪ አገር ለቀው እንዲወጡ ማዘዙ አሳስቦኛል።«
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሱዳን፧ ዋና ጽህፈት ቤቱ በዩ ኤስ አሜሪካ የሚገኘውን የእርዳታ ድርጅት CARE ፧ በሱዳን የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን Paul Barker ን ከስድስት ቀን በፊት፧ በሰባ ሁለት ሰዓት ውስጥ፧ አገር ለቀው እንዲወጡለት ካዘዘ ወዲህ፧ አሁን ተመልሰው ሥራቸውን ማካሄድ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንደገና በመነጋገር ላይ መሆኑ ታውቋል። ሆኖም ባን ኪ ሙን አሁን ሱዳንን በመጎብኘት ላይ በመሆናቸው፧ ውይይቱ ሊጓተት እንደሚችል ነው ባርከር የጠቆሙት። የካርቱም መንግሥት አገር ለቀው እንዲወጡ የወሰነው፧ በተሳሳተ ግምት ተመርኩዞ መሆኑን ነው የተናገሩት። CARE እ ጎ አ በ 1979 ዓ ም በሱዳን መሠማራት ከጀመረ ወዲህ ቢያንስ 184 ሚልዮን ዶላር ለእርዳታ ማዋሉን ከ 60 ሚልዮን ዶላር በላይ የሚሆነውን ወጪ ያደረገውም በይበልጥ ዳርፉር ውስጥ ባለፉት 3 ዓመት መሆኑን ባርከር አስረድተዋል።
የሱዳን መንግሥት፧ ሌሎች የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶችንና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ቡድኖችን «የምዕራቡን አጀንዳ« ያለውን፧ እንደሚያራምዱ በመግለጽ፧ ጥረታቸው፧ የካርቱም መንግሥት በዳርፉር የሚያደርገውን ሁሉ ዋጋ ማሣጣት ነው ሲል ይከሣል። ባለፉት አራት ዓመታት ከመንፈቅ፧ በዳርፉር ሲካሄድ የቆየው የኃይል እርምጃ 2.5 ሚልዮን ህዝብ ከቀየው ማፈናቀሉ ይነገራል። ዓለም አቀፍ ጠበብት እንደሚገምቱት፧ በአመዛኙ የዓረብ ባህል ተከታዮች ያልሆኑ አማጽያን ብረት አንስተው መታገል ከጀመሩ ወዲህ፧ 200,000 ያህል ሰዎች ናቸው፧ ህይወታቸውን ያጡት።