1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባባሰው የደቡብ ሱዳን ግጭት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2006

የደቡብ ሱዳን ግጭት እስካሁን በሺህዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ነዋሪዎችንለሞት ዳርጓል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችም ቀዬያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አስገድዷል። ከወራት በፊት በሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት መካከል አዲስ አበባ ውስጥ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተፋላሚዎችን ደም ከመፋሰስ አልታደገም።

https://p.dw.com/p/1BqP8
ምስል AFP/Getty Images

የደቡብ ሱዳን መንግሥትና ተፋላሚዎቹ ነፍጥ አንስተው አንዱ የሌላውን ወገን ለማጥፋት የጠመንጃ ምላጭ ከመሳብ የተቆጠቡበት ጊዜ አልታየም። ኢጋድ ለድርድር ላይ ታች ይላል። የተመድ ማዕቀብ ለመጣል እያሰላሰልኩ ነው ብሏል። ደቡብ ሱዳናውያን ግን ዛሬም እየረገፉ ነው።

በደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭቱ ወደ ከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ ይመስላል። ተፋላሚ ኃይላትና ደጋፊዎቻቸው አንዱ የሌላኛውን ወገን በጅምላ መፍጀት ጀምረዋል። ነፍሰገዳይ ታጣቂዎች ግዳይ ለመጣል ከቤንቱዪ ቦር ከተማ ሲሯሯጡ እዛው ደቡብ ሱዳን ምድር ላይ ግን የዩጋንዳ ጦር መንግሥትን ለመጠበቅ ሰፍሯል። ኢጋድ ለማደራደር ላይ ታች ከማለት ባለፈ የፈየደው ነገር የለም። ዓለም ደቡብ ሱዳን የጅምላ ፍጅት እንዳይከሰትባት እሰጋለሁ ብሏል። የዓለም አቀፍ የፀጥታ ተቋም በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ ISS ከፍተኛ ተመራማሪ አንድሪውስ አታ አሳሞዋ የደቡብ ሱዳን ግጭት ከዕለት ዕለት እየከፋ መምጣቱ ሌላ ጣጣ እንዳያስከትል አሳስቧቸዋል።

አዲስ አበባ ውስጥ የደ.ደሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ተኩስ አቁም ስምምነት
አዲስ አበባ ውስጥ የደ.ደሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ተኩስ አቁም ስምምነትምስል picture-alliance/dpa

«አንዳች ነገር በፍጥነት እስካላደረጉ ድረስ ግጭቱ በእራሱ ሌላ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ አሰቃቂ ነገር ሊያስከትል ይችላል። ስለእዚህ በሌሎች ዙር አዙር ጉዳዮች ከመጠመድ ይልቅ ወደ እውነተኛው ጉዳይ ያተኩራሉ ብዬ እጠብቃለሁ።»

የነዳጅ ሀብት የታደለችው የቤንቲዩ ከተማ ውስጥ ሰሞኑን ከ200 በላይ ሰዎች በጅምላ ሲጨፈጨፉ የታደጋቸው አልነበረም። ብዙም ሳይቆይ ቦር የተባለችው ሌላኛዋ ከተማ ውስጥ የተመድ መጠለያን መድኅን አድርገው የሰፈሩ ቁጥራቸው ቢያንስ 60 የሚደርስ የኑዌር ተወላጅ ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች የጥይት እራት ሲሆኑ አሁንም ማንም አላስጣላቸውም። ደቡብ ሱዳናውያን የኑዌር ተወላጅ፣ የዲንካ ሰው በማለት እየለዩ እርስ በእርስ ተገዳድለዋል። ይህ ሁናቴ ደቡብ ሱዳንን ወደ አዲስ የፍርሃት ቃጣና እንዳይቀይራት «ሂውማን ራይትስ ዎች» የተሰኘው የሠብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አሳሳቢነቱን ጠቅሷል። አንድሪውስ አታ አሳሞዋ በበኩላቸው ነገሩ በጊዜ መላ ካልተበጀለት ከቁጥጥር ውጪ ሊወጣ ይችላል ብለዋው።

«ሁኔታዎቹ ተባብሰዋል ብሎ መናገር ይቻላል። አንዳች ጠንካራ ርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ፤ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የእርስ በእርስ ጦርነት ይከሰታል»

ይህ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የታየው መጨካከንና መገዳደል 6 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት አዲሲቷ ሀገር፤ ደቡብ ሱዳን በዓለም ፊት ጥላ እንዲያጠላባት አድርጓል። በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሣልቫኪርና ተቀናቃኛቸው ሬይክ ማቻር መካከል በነበረ የቆየ የሥልጣን ሽኩቻ የተቀሰቀሰው ፍጥጫ ቀስ በቀስ የጎሣ ግጭት መልክ ነው እየያዘ የመጣው።

ደቡብ ሱዳንና ጎረቤቶቿ
ደቡብ ሱዳንና ጎረቤቶቿምስል DW

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር የዲንቃ ጎሣ አባል ሲሆኑ፤ የቀድሞ ምክትላቸው የአሁኑ ተቀናቃኛቸው ሬይክ ማቻር የኑዌር ተወላጅ ናቸው። ኑዌርና ዲንቃ ከደቡብ ሱዳን አጠቃላይ ሕዝብ 60 በመቶውን ይሸፍናሉ። ሣልቫ ኪር፤ ሬይክ ማቻር ከሥልጣን መንበሬ ሊያፈናቅሉኝ ሲያሴሩ ደርሼባቸዋለሁ ካሉበት ቅፅበት አንስቶ ነው በሁለቱ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል መቆራቆሱ እየተካረረ የመጣው። ማቻር የፕሬዚዳንቱን ክስ በወቅቱ አጣጥለዋል። ፕሬዚዳንቱ በአፀፌታው የማቻር ታማኞች ያሉዋቸውን 11 ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፍርድ ቤት አቁመው ከአራቱ በስተቀር የተቀሩትን ነፃ አሰናበቱ። ምክትላቸው ማቻር ግን በወቅቱ ከመዲና ጁባ ሹልክ ብለው ነፍጥ በማንሳት «ጥራኝ ዱሩ» አሉ። አማፂያንን አደራጅተውም ሣልቫ ኪር ላይ ዘመቻ ከፈቱ።

በሥልጣን ይገባኛል ውዝግብ ተጀምሮ የተካረረው ፍጥጫ ግን የእዚያና የእዚህ ወገን እያለ ወደ መገዳደል ለመሸጋገር ብዙም አልቆየ።

«ያለፉት ሁለት ሣምንታት ክስተቶችን ብትመለከት ነገሮች እየተባባሱ ሄደዋል። በመንግሥትና በአማፂያን መካከል በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል። ከእዚያም ባሻገር እንደ ቤንትዩ ባሉ ቦታዎች ላይ የታቀዱ ግድያዎች ተፈፅመዋል።»

የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያ
የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያምስል DW/Coletta Wanjoyi

ሰሞኑን በቦር ከተማና ቤንቱዊ የተፈፀመው ወገን ለይቶ የመግደል ወንጀል መላ ዓለምን አስደንግጧል። የተመድ በበኩሉ «ሳይቃጠል በቅጠል» እንዲሉ ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን ጁባ ሰዷል። የሠብዓዊ መብቶች ጉዳይ ዋና ኃላፊ ናቪ ፒላይና በተመድ የጅምላ ጭፍጨፋ መከላከል ልዩ መልዕክተኛ አዳማ ዲንግ ዛሬ መዲናይቱ ጁባ መድረሳቸው ተዘግቧል። ባለሥልጣናቱ ጁባ ውስጥ ከፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር ጋ ይነጋገራሉ። የፀጥታው ሁናቴ አስተማማኝ ከሆነም ጅምላ ጭፍጨፋ የተፈፀመበት ቦታ ድረስ በመጓዝ ተጎጂዎችን ይጎበኛሉም ተብሏል። አማፂያንን ቢቻል እዛው ደቡብ ሱዳን ውስጥ ካልሆነም አዲስ አበባ ሄደው እንደሚያናግሯቸውም ተዘግቧል።

«ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁኔታዎችን እየተከታተለ ነው። እናም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁኔታዎች እየተከታተለ መሆኑን ተፋላሚ ኃይላቱ ካወቁ ጥንቃቄ ማድረግ ይጀምራሉ። ምክንያቱም ሁኔታዎች በኋላ ላይ ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀለኛ መዳኛ ፍርድ ቤት ሊያመራ ይችላል ብለው ይሰጋሉ።»

ደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ የሚገኙት የተመድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሁለቱም ተፋላሚ ኃይላት በኩል ተፈፀሙ የተባሉትን ጥሰቶች እንደሚመረምሩ ተገልጿል። ዩናይትድ ስቴስትስን ጨምሮ ምዕራባውያን መንግሥታት ተፋላሚ ኃይላቱ ወደ ሠላም ድርድር በአስቸኳይ ፊታቸውን እንዲያዞሩ አስጠንቅቀዋል።

ይህ ግፊት ጫና የፈጠረበት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ባለፈው አርብ የአማፂያን ከፍተኛ አመራር አራት እስረኞችን ከእስር በነፃ አሰናብቷል። ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር የእስረኞቹን ከእስር መፈታት «ለሠላም የተከፈለ ዋጋ» ነው ብለዋል። አያይዘውም «ስቅላት ብንፈርድባቸው እንኳን ለሟቾቹ ካሣ ሊሆን አይችልም» ማለታቸውም ተደምጧል።

የተባባሰው የደቡብ ሱዳን ግጭት
የተባባሰው የደቡብ ሱዳን ግጭትምስል DW/J.-P.Scholz/A.Kriesch

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃልአቀባዪት ጄን ፕሳኪ ሀገራቸው በአንዳንድ የደቡብ ሱዳን ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ለመጣል እያሰላሰለች መሆኗን ጠቅሰዋል። የእስረኞቹን መፈታት በተመለከተም «የምንደግፈው ርምጃ ነው፤ ሆኖም ገና ድሮ ተግባራዊ መሆን ነበረበት» ሲሉ ተችተዋል።

በሌላ በኩል የአካባቢው ሃገራት ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚያንፀባርቁት የግል ፍላጎት ለሠላም ሂደቱ እክል እንዳይሆን ማስጋቱን የISS ከፍተኛ ተመራማሪ አንድሪውስ አታ አሳሞዋ ገልፀዋል። የዩጋንዳ ጦር ደቡብ ሱዳን ውስጥ መገኘቱን እንዲሁም ግብፅ ወደ ደቡብ ሱዳን ጦር ለመላክ የመፈለጓ ነገር ሁኔታውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊመራው ይችላልም ብለዋል።

«ነገሮች በምን ይተረጎሙ እንደሆን በጥንቃቄ መመልከት ያሻል። ለምሳሌ፦ግብፅ ጦሯን ለማስፈር የመፈለጓ ነገር በአባይ ወንዝ ዙሪያ ካለው ታላቅ ጥያቄ አንፃር ሊታይ ይችል ይሆናል። እናም ሃገራት ጥቅማቸውን በማስከበሩ ዙሪያ የሚያነሱት ጥያቄ ሊኖር ይችላል። ያ ነገሮችን የበለጠ ያወሳስባል። የደቡብ ሱዳን ግጭት የተፈጥሮ ሀብትን መሠረት ያደረገ ፍትጊያ የሚስተናገድበት አውድ ሊሆን ይችል ይሆናል። ይኽ ደግሞ ነገሩን የበለጠ ያወሳስበዋል።»

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪርና የዩጋንዳው አቻቸው ሙሴቬኒ
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪርና የዩጋንዳው አቻቸው ሙሴቬኒምስል Tony Karumba/AFP/Getty Images

የደቡብ ሱዳን መንግሥትን ከአማፂያን ለመጠበቅ በሚል ደቡብ ሱዳን ውስጥ ጦር ኃይል ያሠማራችው ዩጋንዳ፤ የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት የልማት በይነ-መንግሥታት በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ «ኢጋድ» ሠላም አስከባሪ ኃይል ሲልክ ሀገሪቱን ለቅቄ እወጣለሁ ማለቱ ተደምጧል። የአካባቢው ሃገራት በበኩላቸው «አማራጮችን ለማጤን» ውይይት እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል።

አራት ወራት የፈጀው የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት አክትሞ ሠላም እንዲሰፍን ለማስቻል የደቡብ ሱዳን መንግሥትና አማፂያን አዲስ አበባ ውስጥ ዛሬ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል። አደራዳሪዎች እንዳስታወቁት የሠላም ንግግሩ በሀገሪቱ ብሔራዊ እርቀ-ሠላምና መግባባት ለማስፈን የፖለቲካ ውይይት ላይ እንደሚያተኩርም ጠቅሰዋል። እናስ ይህ ሁሉ ምክክር፣ የማዕቀብ ዛቻና ማስፈራሪያ ታክሎበት እንደ ሀገር ከቆመች ገና ሦስት ዓመት ያልሞላት ደቡብ ሱዳን ለግጭቷ ዕልባት ይገኝለት ይሆን? ተፋላሚ ኃይላቱስ አዲስ አበባ ላይ የፈረሙትን የተኩስ አቁም ስምምነት አክብረው ለሠላም ይገዙ ይሆን?

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ