1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባ መ የምግብና የእርሻ ድርጅት ዘገባ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 7 1997

የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ አሁን በዓለም ውስጥ ስላለው የረሃብተኞች ሁኔታ ያቀረበው ዘገባ ተሥፋ ተደርጎበት የነበረውን አዎንታዊ ለውጥ የሚጠቁም አይደለም። እንዲያውም፥ በዓለም ውስጥ የረሃብተኞች ቁጥር ጭራሹን እየጨመረ ነው የሚሄደው።

https://p.dw.com/p/E0f9

በጠቅላላው ፰፻፶፪ ሚሊዮን ሕዝብ ነው በየቀኑ የሚራበው፤ በያመቱ አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ ሕፃናት ናቸው በምግብ እጥረት ምክንያት የሚቀጩት። የዓለሙ ድርጅት ዘገባ እንደሚለው፥ የረሃብ ጭንቀት ሰብዓዊውን መከራ ብቻ አይደለም የሚያንፀባርቀው፤ ረሃብ ለድሆቹ ሀገራት ኤኮኖሚም ከባድ ጭነት ነው የሚሆነው።

በድሆቹ ሀገሮች ውስጥ ለውዱ ሕክምና የሚከሰከሰው ወጭ እና ሕመም የሚያስከትለው የሥራ ትጉላት በያመቱ ፭፻ ሚሊያርድ ዶላር የሚደርስ የኤኮኖሚ ጉድለት ያስከትላል። የሆነ ሆኖ፣ ዝንባሌው አሉታዊ ሆኖ ቢታይም፣ በ፪ሺ፲፭ ዓ ም(እጎአ)--በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ መሆኑ ነው፣ የረሃብተኞችን አሃዝ በግማሽ ለመቀነስ የተተለመው ግብ ሊተገበር እንደሚችል ያው የተባ መ የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ ያምንበታል። ድርጅቱ እንደሚለው ከሆነ፥ በግቡ ክንውን ረገድ ተሥፋ የሚሰጡ ብዙ ምልክቶች አሉ። ለምሳሌ፥ በፋኦ ዘገባ መሠረት፥ እንደ ጋና፣ እንደ ቪየትናም፣ እንደ ሬፑብሊክ ኮንጎ፣ ወይም እንደ ፔሩ የመሳሰሉት አዳጊ ሀገሮች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የረሃብተኞችን አሃዝ በጉልህ ለመቀነስ በቅተዋል። የረሃብተኞችን አሃዝ ለመቀነስ ያስቻለው፥ ለግብርናው ዘርፍ ልማት የተሰጠው ቀዳሚው ትኩረት ሆኖ ነው የሚታየው። ግን፣ ያው የተባ መ የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ እንደሚያስገንዝበው፣ በረሃብ አንፃር ለሚደረገው ትግል ሥምረት ዓቢይ መስፈርት የሚሆነው፣ እንደተለመደው፣ የሰላም ጽናት ነው። ጦርነት ወይም እርስበርሱ ጦርነት በሚካሄድበት ቦታ ሁሉ የረሃብ አደጋና የምግብ እጥረት የሚደቀንባቸው ችግረኞች አሃዝ እያሻቀበ ነው የሚሄደው፤ በዚህም ምክንያት ነው ለእያንዳንዱ የልማት ርምጃ ጽኑእ ሰላም ቀዳሚው ግዴታ ነው የሚባለው።

ታዛቢዎች እንደሚያስገነዝቡት፥ በአንዳንድ ጥቂት ሀገሮች ውስጥ የመሻሻል ምልክት ቢፈነጠቅም፣ ዝንባሌው በጣም አሳሳቢ ሆኖ ነው የሚታየው፤ የዓለም መንግሥታት የረሃብን ችግር ለመታገል ብቁእ እየሆኑ አልተገኙም። እንዲያውም፥ ገሃዱ ተገላቢጦሹ ሆኖ፥ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከእለት ወደ እለት በቂ ምግብ የማያገኙት ሰዎች አሃዝ ጭራሹን በ፲፰ ሚሊዮን እንደመጠቀ ነው አሁን የሚመለከተው። በተለይ የሚያስደነግጠው ደግሞ፥ በያመቱ አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ ሕፃናት በምግብ እጥረት ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የሚቀርበው ዘገባ ነው።

በዓለሙ ድርጅት ዘገባ መሠረት፥ ባሁኑ ጊዜ በዓለም ውስጥ ከ፰፻፶ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ነው በረሃብ መከራ ላይ የሚገኘው። ይኸው የረሃብተኞች አሃዝ ለምሳሌ ከጠቅላላው የጀርመን ሕዝብ አሃዝ በአሥር እጅ የላቀ ነው።

የሆነ ሆኖ፣ ዝንባሌው በዚህ አኳኋን አሉታዊ ቢሆንም ቅሉ፣ የተባ መ የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ የዓለም ረሃብተኞች አሃዝ እጎአ እስከ ፪ሺ፲፭ ድረስ በግማሽ እንዲቀነስ የተተለመውን ግብ ከመከታተል እንደማይቆጠብ በዘገባው ውስጥ ግልጽ አድርጎታል። ረሃብን በጥንካሬ ለመታገል ይቻል ዘንድ፣ ሐብታሞቹ እንዱስትሪ-ሀገሮች እና ራሳቸው የሚደረጁትም ሀገሮች መንግሥታት የበለጠ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ፋኦ እንደሚያስገነዝበው። የዚሁ ድርጅት ምክትል-ሥራአስኪያጅ ሃርትቪኽ ደ ሄን ስለዚሁ የበለጠ ጥረት አስፈላጊነት የሚያጎሉት ማስገንዘቢያ፥ “.......በረሃብ አንፃር የሚደረገው ትግል የተለየ ጥረትን ይጠይቃል፤ በተለይም በራሳቸው ችግሩ በቀጥታ በሚመለከታቸው ሀገሮች ውስጥ የበለጠ ጥረት መንቀሳቀስ አለበት፣ በጠቅላላውም የኤኮኖሚ መርሕ ረገድ ድሆች ችላ መባል የለባቸውም፥ የልማቱ ትኩረት ሁሉ እነርሱን ነው ማማከል ያለበት። ለግብርናው ዘርፍ ልማትና ለፀረ-ረሃብ ትግል የሚውለው እያንዳንዱ ዶላር በእነዚያው ሀገሮች ውስጥ መልሶ ጥቅም እያመነጨ፣ የምርትን ተጠያቂነት፣ የግብርና ውጤቶች ለሽያጭ የሚቀርቡበትን ገበያ በይበልጥ ያነቃቃል፣ በዓለምም ውስጥ የበለጠውን የፖለቲካ እርጋታ የሚፈጥር ይሆናል። በረሃብ አንፃር ለሚደረገው ትግል የሚመደበው ውዒሎተንዋይ፥ በዓለም ውስጥ ለሰላም ጽናት እንደሚመደብ አትራፊ ውዒሎተንዋይ የሚቆጠር መሆኑ መታሰብ አለበት።”

በዚህ አንፃር ደግሞ፥ ጦርነትና እርስበርሱ ጦርነት፣ እንደሚታወቀው፣ ለከባዱ የረሃብ አደጋና ለምግብ እጥረት ተጥያቂ ከሚሆኑት ዓበይት ምክንያቶች አንዱ ነው። አፍጋኒስታን ወይም ኢራቅ፣ ወይም ደግሞ አንጎላን የመሳሰሉት የቀድሞዎቹ የእርስበርስ ጦርነት ሀገሮች የምግብ እጥረት ከተባባሰባቸው ሀገሮች መካከል ነው የሚቆጠሩት--ፋኦ እንደሚያስገነዝበው።

የዓለም ረሃብ ሁኔታ የሚያብራራው የፋኦ ዘገባ ቀጥሎ፥ ለተሥፋ ምክንያት የሚሰጡ አዎንታዊ ምሳሌዎችም አሉ ይላል። በዚህም መሠረት፣ በ፴ ሀገሮች ውስጥ ሁኔታው በጉልህ ነው እየተሻሻለ የተገኘው፤ በእነዚያው ሀገሮች ውስጥ የረሃብተኞቹ አሃዝ ቢያንስ በ፳፭ በመቶ ነው የተቀነሰው። በፋኦ ምክትል-ሥራአስኪያጅ ደ ሄን አመለካከት፥ የእነዚሁኑ ሀገሮች አዎንታዊ ሂደት በመመልከት ነው የረሃብተኞች አሃዝ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ በግማሽ የሚቀነስበት ግብ ሊተገበር ይችላል የሚያሰኘው። “.......ለመሆኑ በድህነት ቅነሳ ረገድ አርአያ የሚደረጉት ሀገሮች የትኛው የጋራ ባሕርይ ነው የሚታይባቸው?-- እነዚሁ የእመርታ ሀገሮች አንደኛ ሰላም አላቸው፣ ሌላው ቢቀር ከሌሎቹ ሀገሮች ያነሰ ውዝግብ ነው የሚደቀንባቸው። ሁለተኛ አነቃቂ የኤኮኖሚ ዕድገት ነው የሚንፀባረቅባቸው፣ ለዚሁ የኤኮኖሚ ዕድገታቸው የግብርናው ዘርፍ ነው ምሰሶ የሚሆናቸው። በዓለም ንግድ ውስጥ የተሻለ ሂደትም ነው ያላቸው።--ይኸውም ፈንጣራ ሆነው በመዳከር ፈንታ፣ ኤኮኖሚያቸውን ክፍት አድርገው ነው የሚራመዱት” ይላል የፋኦ ምክትል ሥራአስኪያጅ ማብራሪያ።

ፋኦ እንደሚለው ከሆነ፣ ይኸው አዎንታዊ ምሳሌ የሚያሳየው፥ ስኬታማው የፖለቲካ መርሕ በረሃብ አንፃር ለሚደረገው ትግል ምኑን ያህል ድጋፍ እንደሚሆን ነው። የምግብ አቅርቦት ችግራቸውን ለመቅረፍ የሚታገሉት ሀገሮች ሁሉ ተመሳሳይ ርምጃዎችን እንደሚከተሉ የጠቀሱት ሃርትቪኽ ደ ሄን በዘገባው ውስጥ እንደሚያስረዱት፥ “.........ከጠቅላላው ድሆች መካከል ሁለት-ሦሥተኛው በሚኖሩባቸው በገጠር አካባቢዎች ለሚመደበው ውዒሎተንዋይ እጅግ የበለጠውን ትኩረት መስጠት ግዴታ ነው። ይህም በሚደረግበት ጊዜ የማኅበራዊ ኑሮው ጥያቄ አብሮ መታሰብ ነው ያለበት። በፍፁሙ የረሃብ አደጋ ላይ የሚገኙትን ሰዎች በቀጥታ ለመርዳት መንግሥታት ከምንጊዜውም የበለጠ ጥረት ነው ማንቀሳቀስ ያለባቸው። እንደሚታወቀው፣ ረሃብ ብዙውን ጊዜ ከድህነት የሚመነጭ ነው፤ የሥራ ቦታ የሌለው ለድህነት ይጋለጣል፤ በድህነት የተያዘ የሚመገበው ያጣል፤ በት/ቤት ውስጥ ዕውቀት መቅሰምም ይሳነዋል፣--ነገሩ ያዙሪት ቀለበት ነው፤ ይኸው ያዙሪት ቀለበት ነው መበጠስ ያለበት።”

ያው የተባ መ የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ እንደሚያስገነዝበው፥ ረሃብ ሰብዓዊውን መከራ ብቻ አይደለም የሚደቅነው፥ ለሚደረጁት ሀገሮች ኤኮኖሚም ከባድ ጭነት ነው የሚሆነው። በድሆቹ አዳጊ ሀገሮች ውስጥ በምግብ እጥረት የተጎዱ እናቶችን እና የኮሰመኑ ሕፃናትን በሕክምና ለመጠገን መንግሥታቱ በያመቱ የሚከሰክሱት ወጭ በ፴ ሚሊያርድ ዶላር ነው የሚገመተው። ስለዚህ፥ ደጋግመን የጠቀስናቸው የፋኦ ምክትል ሥራ-አስኪያጅ ሃርትቪኽ ደ ሄይን እንደሚሉት፣ በረሃብ አንፃር የሚደረገው ትግል በሥነምግባር/በሞራል ብቻ ሳይሆን፥ በኤኮኖሚ ጠቀሜታም አኳያ ነው መታየት ያለበት።

ነገሩን ለመድገም፥ ረሃብ ከሰብዓዊው መከራ ጎን በብሔራዊ ደረጃ የኤኮኖሚንም ጉዳት ነው የሚያስከትለው። ገና በጨቅላው ዕድሜያቸው የምግብ እጥረት የሚደርስባቸው ወጣቶች በኋለኛውም ዘመን ሙሉ ያምራችነት አቅም የማያገኙበት ሁኔታ በጠቅላላው በ፭፻ ሚሊያርድ ዶላር የሚገመት የኤኮኖሚ ጉድለት የሚያስክትል እንደሚሆን ነው የተባ መ የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ ያቀረበው ዘገባ አጥብቆ የሚያስገነዝበው። ረሃብ በሚያስከትለው በዚሁ ግዙፍ ክስረት አንፃር ሲታይ፥ ያንኑ የረሃብ አደጋ ለማስወገድ የሚዘረጋው ፍቱኑ መርሐግብር ብዙ ወጭ የሚጠይቅ አይደለም ይላል ያው የዓለሙ ድርጅት ዓመታዊ ዘገባ።