1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተናጠሉ የንግድ ስምምነት እና የሰብአዊ መብት

sdestaረቡዕ፣ ሐምሌ 14 1996

ዓለም አቀፍ መልክ ያላቸው እና በተናጠል የሚደረጉ የንግድ ስምምነቶች የሰብአዊ መብቶችን እያጣሱ መሆናቸው ተገለፀ ። የአውሮጳ እና የአሜሪካ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት በተለይ አሜሪካ በምትከለው የንግድ ስምምነት መርህ ብሄራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ህጎች እየተሸረሸሩ ነው ። የሰብአዊ መብቶች ያወጡት የጋራ መግለጫ ሰነድ ከሚቀጥለው ሰኞ አንስቶ ስብሰባ ለሚቀመጠው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ንዑስ ኮሚሽን ተሰጥቷል ።

https://p.dw.com/p/E0fT

የጋራ ሰነድ አዘጋጁ የተባሉት የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በአውሮጳ የሶስተኛው ዓለም ማዕከል እና የአሜሪካ የዳኞች ማህበር የተባሉ ድርጅቶች ናቸው ። የድርጅቶቹ የጋራ ሰነድ ነጻ ንግድን በማሳደግ ስም እና የግል ምዋለ ንዋይን መብት ለመጠበቅ በሚል ሰበብ የሚደረጉ የተናጠል የንግድ ስምምነቶች ብሄራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ህጎች መጣሳቸውን ይገልጻል ። ድርጅቶቹ እነዚሁኑ የሰብአዊ መብት የሚጥሱ ናቸው የተባሉትን ስምምነቶች ጎጂነት ለማሳየት ስያሜ ሰጥተው አውዳሚ የጦር መሳሪያዎች ብለዋቸዋል ። የድርጅቶቹ መግለጫ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ዣክ ሺራክ ባለፈው ሳምንት በታይላንድ ባንኮክ ለተካሄደው የፀረ ኤይድስ አስራ አምስተኛ ዓመታዊ ጉባኤ የላኩትን የፅሁፍ መልክት ያጣቀሰ ነው ። ሺራክ በሚንስትራቸው ያስነበቡት መልክት ዩናይትድስቴትስን የሚወቅስ ነበር ። ሽራክ እንደሚሉት ዩናይትድስቴትስ ከታዳጊ ሃገራት ጋር የንግድ ስምምነት ለመፈፀም የምታስቀምጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች የሃገራቱን የማምረት ተግባር የሚፈታተን ነው ። በተለይ በመልማት ላይ ያሉት ሃገራት ከኤች አይቪ ቫይረስ ጋር ለሚኖሩ ወገኖቻቸው የሚውል የዕድሜ ማራዘሚያ መድሃኒት እንዳያመርቱ በንግድ ስምምነት ወቅት እንደ ቅድመ ሁኔታ መጥየቋ አግባብ አይደለም ብለዋል ። ሽራክ እንደሚሉት ይህ ተግባር የዶሃውን ድንጋጌ የሚጥስ ነው ።

ከሶስት ዓመት በፊት በህዳር 2001 ዓ.ም በሚንስትሮች ደረጃ በተደረገው የዓለም የንግድ ድርጅት ጉባኤ ላይ የፀደቀው የዶሃው ስምምነት ለድሃ ሃገራት የተለያዩ መድሃኒቶችን የማግኘት እና የማምረት መብትን የሰጠ ነበር ። በዓለም የንግድ ድርጅት የኤኮኖሚ ክፍል ሃላፊ እንዲሁም በፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ዘመን አማካሪ የነበሩት ጆሴፕ ሽትግሊትስ ዩናይትድስቴትስ በመልማት ላይ ባሉ ሃገራት ላይ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ጫና የምትፈጥርበትን ምክንያት አስቀምጠዋል ። እንደሳቸው አባባል ዩናይትድስቴትስ የኤኮኖሚ ኃይሏን በድሃ ሃገራቱ ላይ የምትጭነው ከፍተኛ የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ገበያ እንዳይነካ እና ተፎካካሪ እንዳይኖርባቸው ነው ። የተናጠል የንግድ ስምምነቶች የሰብአዊ መብቶችን እየጣሱ ናቸው ያሉት የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እሳካሁን የተደረጉት እና በግምት ወደ ሁለት ሺ የሚደርሱት ስምምነቶች በቀጥታ በሰብአዊ መብቶች ላይ ጫና የሚያሳርፉ ሆነው አግኝተዋቸዋል ። በሃገሮች መካከል በሚደረግ የተናጠል ስምምነት በተለይ ሙሰኛ እና ደካማ መንግስታት ለቅድመ ሁኔታዎች ተንበርካኪ እየሆኑ እንደሚታዩም ገልፀዋል ። እዚህም ላይ በግንባር ቀደምትነት የተወቀሰችው ዩናይትድስቴትስ ናት ።

የዩናይትድስቴትስ ጫና የሚያርፈው በሃገራት ላይ ብቻ አይደለም ። ለምሳሌ በአካባቢዊ የንግድ ትብብር ስም ከተቋቋሙ ማህበራት ወይም ድርጅቶች ጋር በምታደርገው የንግድ ስምምነትም የምትፈልገውን እንዲያሟሉላት ፤ ያልፈለገችውን እንዲተውሏት ታስገድዳለች ። በወጥመዷ ውስጥ የገቡ ከተባሉት ድርጅቶች መሃል የማዕከላዊ አሜሪካ ነጻ የንግድ ትብብር ተቋም ከዩናይትድስቴትስ ጋር የሚደረጉ ስምምነቶችን ለሌላኛው የአሜሪካ ሃገራት ነጻ የንግድ ቀጠና ለተባለው ድርጅት ለቋል ። ምክንያቱም የማዕከላዊ የንግድ ስምምነቱ ማናቸውም ውሎች የሚፀድቁት በየሃገራቱ ፓርላማዎች በመሆኑ ለአሜሪካ ውጣ ውረድን ይፈጥርባታልና ነው ። በምትኩ በዩናይትድስቴትስ ድጋፍ የሚመራው የአሜሪካ ሃገራት ነጻ የንግድ ቀጠና ለአሜሪካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆኗል ። በዚህ ድርጅት ውስጥ ከኩባ በስተቀር ሁሉም የአሜሪካ ሀጋራት አባል ናቸው ።

ለተባበሩት መንግስታት የሰብዊ መብት ኮሚሽን ንዑስ ኮሚሽን የቀረበው ሰነድ ያካተተው ሌላው ነጥብ በተናጠል በሚደረግ የንግድ ስምምነት የብሄራዊ የምዋለ ንዋይ ዘርፎች ከመበረታታት ይልቅ የውጭ ባለሃብቶች ገበያውን እና የሰው ኃይል ጉልበትን እየተቆጣጠሩት ነው ይላል ። በተጨማሪም በሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች የውጭ ኩባንያዎች በብሄራዊ ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሰው ቢገኙ እንኳን የሚከላከሉላቸው ስምምነቶች ተመስርተው ይገኛሉ ። ለዚህ በሰነዱ እንደምሳሌ የተጠቀሰችው ሜክሲኮ ነች ። ከስምንት ዓመት በፊት የዩናይትድስቴትስ የብረት አምራች ኩባንያ የቶክሲክ ቆሻሻዎች ማስወገጃ ሥፍራን በሜክሲኮ ለመክፈት የነደፈውን እቅድ ሜክሲኮ ከልክላ ነበር ። ክልከላዋ ግን አባል በሆነችበት የሰሜን አሜሪካ የነጻ የንግድ ቀጠና አባል ሃገራት የንግድ ስምምነት ህግ መሰረት አስራ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገደማ ካሳ እንድትከፍል አስፈርዶባታል ።

እነዚህና ሌሎች መሰል ግዴታዎች በመልማት ላይ ባሉ ሃገሮች ላይ ተፅዕኖ በማሳደራቸው በየሃገራቱ የሲቪል ፣ የኤኮኖሚ ፣ የማህበራዊ እና የባህል መብቶች መጣስ ይከተላሉ ። ድርጅቶቹ ሰነዱ እንዲመከርበት ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን ቢያቀርቡትም እንደመፍትሄ ብለው የጠቀሷቸው ነጥቦችም አሉ ። ሃገራት ያደረጉዋቸው እና የሚያደርጓቸው የተናጠል የንግድ ስምምነቶች የሚኖራቸውን አሉታዊ ተፅዕኖዎች መመርመር ፤ በስምምነቶቹ ላይ ብሄራዊ ምክር ቤቶቻቸው እና ህዝቡ እንዲመክርበት ማስደረግ አለባቸው ።