1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተከፈላቸዉ ገራፊዎች በግብፅ

ዓርብ፣ ጥር 27 2003

የግብፅ ህዝባዊ አመፅ ወደግጭት ከተሸጋገረ ወዲህ ዉጥረት ነግሷል።

https://p.dw.com/p/QyMW
ምስል picture-alliance/dpa

ከትናንት በስተያ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ አደባባይ ለተቃዉሞ የወጣዉ ህዝብና የፕሬዝደንት ሙባረክ ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረዉን ግጭት የጫሩት በመንግስት የተቀጠሩ ጨካኞች እንደሆኑ እየተነገረ ነዉ። ከስፍራዉ የተገኙ መረጃዎች የሚያመለክቱት ብጥብጥ ያስነሱት ተጋራፊዎች እስከ ህይወት ማጥፋት ለተራመደ ተግባራቸዉ ስምንት ዩሮ ተከፍሏቸዋል። የመንግስት ባለስልጣናት ከህዝብ የወጣዉን መረጃ ተከትሎ ይቅርታ ጠይቀዋል፤ ጉዳት አድራሾችም ይቀጣሉ ሲሉ ተደምጠዋል።

ለአራት ቀናት በተከታታይ በነጻነት አደባባይ የተገኘ አንድ ግብፃዊ ወጣት በሙባረክ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል በድንጋይ፤ በስለትና ጅራፍ የተካሄደዉን ፍልሚያ ልክ በመካከለኛዉ ዘመን የነበረዉን ጦርነት ያስታወሳል ይለዋል። ግብፃዉያን ጎራ ለይተዉ ሲቀጣቀጡ በቅርብ ያስተዋሉ ዘጋቢዎች በበኩላቸዉ ድርጊቱን ጭካኔ የተመላበት ይሉታል።

Ägypten Proteste in Kairo Demonstranten Wasserwerfer Flash-Galerie
ምስል dapd

ግማሾቹ ህዝቡን መስለዉ ሌሎቹ ደግሞ እንደጀግና ጦረኛ በፈረስ ተቀምጠዉ ሰላማዊዉን ሰልፈኛ ለማጥቃት የመጡትን የፕሬዝደንቱን ደጋፊዎች ስምንት ዩሮ ለማግኘት ሰዉ ለመግደል የተሰማሩ ሲሉ ይከሳሉ። በርካታ ቱሪስቶች በሚጎርፉባት ግብፅ በአስተርጓሚነት ሥራ የተሰማራዉ የ29ዓመቱ መሐመድ ፋቲ የሙባረክ ደጋፊዎች ሰላማዊዉን የተቃዉሞ ሰልፍ ባወኩባት ረቡዕ ካይሮ ከተማ ዉስጥ የተመለከተዉን ለመግለፅ ቃላት የጣለት ይመስላል፤

«የተደራጀ ግድያ ነበር። ከቀኑ ስምንት ሰዓት አንስቶ እስከሃሙስ ማለዳ ድረስ ተከበን ነበር። የሲቪል ልብስ የለበሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጨካኝ ገራፊዎች፤ ከወህኒ የተለቀቁ እስረኞች፤ ፖሊሶችና ደህንነቶች ወታደሮች ናቸዉ ከእኛ ጋ የተፋለሙት። መካከላቸዉ የፖሊስ መኮንኖች ሁሉ ነበሩ።»

መሐመድ የሚለዉን የሚያጠናክር ማስረጃ ከበቂ በላይ ተቆጥሯል። የዴሞክራሲ ንቅናቄ አባላት የበርካቶቹን እጅ ይዘዉ ለወታደሮች አስረክበዋል። ሲፈትሸቸዉም ማንነታቸዉን የሚያረጋግጥ መታወቂያ ተገኝቷል። በርካቶቹም ለዚሁ ተግባር የተቀጠሩ መሆናቸዉን ነዉ የሚናገረዉ፤

«አንዳንዶች በፖሊስነት ተቀጥረዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ በነጋዴዎች ነዉ የተላኩት፤ እነሱ ደግሞ የበለጠ እንደሚከፍሏቸዉ ይታመናል። በተጨማሪም የምክር ቤት አባላትም ለገራፊዎቹ ከፍለዋቸዋል። ይህን ቃላቸዉንም በቪድዮ ቀርፀናል። እንደሚፈፅሙት ተግባርም አብዛኞቹ 50 አንዳንዶቹም 500 ፓዉንድ ተከፍሏቸዋል።»

ለመግደል ከስምንት እስከ ሰማንያ ዩሮ ማግኘት ማለት ነዉ። እስከትናንት ጠዋት ድረስም ይህ ቡድን በአዉቶቡስ ተጭኖ ወደተሰበሰበዉ ህዝብ የሚወረዉረዉን ጓዳ ሰራሽ ፈንጂ እያከታተለ በመጣል አደባባዩን ከቦ ታይቷል። መሃመድ ፋቲ ጠንካራ ተኩስም እንደነበር ነዉ የሚገልፀዉ፤

«እስካሁን ቢያንስ ስድስትተገድለዋል፤ 1,500 ሰዎች ቆስለዋል። ከተጎጂዎቹ መካከል የሃይማኖት መሪዎች፤ ተማሪዎች፤ ሠራተኞች፤ ሙስሊም ወንድማማች፤ ቀኞችና ለዘብተኞች፤ እንዲሁም ፖለቲከኛ ያልሆኑ አሉባቸዉ። አንድ ዶክተር ትናንት በድንጋይ ተደብድቦ ህይወቱን አጥቷል። ደሙ ፈሶ ነዉ የሞተዉ። ከግብፅ ቤተመዘክር አጠገብ ከተካሄደዉ አስከፊ ዉጊያ ዉስጥ ነበር። እሱ እዚያ የተገኘዉ ሰዎችን ለመርዳት ነዉ። ሙባረክ ትናንት በወንጀለኛ ስርዓቱ ወንጀለኛ ተደባዳቢዎች የአንድን ዶክተር ህይወት ለህልፈት ዳርገዋል። በነጻነት አደባባይ ለሰላማዊ ተቃዉሞ መዉጣት ዋጋዉ እልቂት ሆነ።»

Mideast_US_Egypt_LLP105_271141102022011.jpg
ምስል AP

የግብፅን ህዝባዊ አመፅ ለመዘገብ በስፍራዉ የተገኙ የዉጭ ጋዜጠኞችም ሳይቀሩ ከትናንት በስተያ ከሰዓት በኋላ አንስቶ ዱላም እስርም ደርሶባቸዋል። የግብፅ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ግን በዋናነት ይዘዉ የቀረቡት «ግብፅ ከገጠማት ዉዝግብ ይልቅ ጠንካራ ናት»፤ ወይም፤ «የማረጋገጫ ሰነድ፤ ይህ ግብፅ ላይ የተሰነዘረ አደገኛ የዉጭ ጥቃት ነዉ።» የሚሉ ርዕሶችን ነዉ። በዘገባዎቹ የዴሞክራሲ ንቅናቄዉ ቡድን አደገኛ ወንበዴ እንደሆነ ተደርጎ ቀርቧል። ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋ ለመነጋገር ዝግጁ እንደሆኑ ሲያስታዉቁ የነበሩት የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝደንት፤ ንግግሩ የሚካሄደዉ ተቃዉሞዉ ከቆመ ብቻ ነዉ የሚል ቅድመ ሁኔታ አቅርበዋል። የጣህሪር አደባባይን ያስጨነቀዉ የዴሞክራሲ ንቅናቄ በበኩሉ እዚያዉ ለመሞት እንደቆረጠ ምላሽ ሰጥቷል። ከረቡዕ ምሽት አንስቶም ቃላቸዉ ቃል መሆኑን በርግጥም አሳዩ። ዛሬም በግብፅ የተጠናከረዉ ህዝባዊ ተቃዉሞ ቀጥሏል። ፕሬዝደንት ሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን እንዲለቁ በህዝብ የተሰጣቸዉ የጊዜ ገደብ ዛሬ በማለቁ በርካታ ሰዎች ወደአደባባይ እየወጡ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ዩናይትድ ስቴትስ ሙባረክ ስልጣናቸዉን ለምክትላቸዉ በመስጠት በአገሪቱ የሽግግር መንግስት እንዲመሠረት ጥሪ ማቅረቧ ቢዘገብም ዋሽንግተን ይህን አስተባብላለች። ፕሬዝደንት ሙባረክ ግን ስልጣን ስለመልቀቅ ሲጠየቁ እሳቸዉ አሁን ከመንበራቸዉ ቢነሱ አገሪቱ ቀዉስ ዉስጥ ትገባለች ይላሉ። በሌላ በኩል የእሳቸዉ ለህዝቡ ጥሪና ተቃዉሞ ጆሮ አለመስጠት ግብፅን ወዳልተገመተ ዉጥንቅጥ እንደከተታት የሚናገሩ አሉ።

ኤስተር ሳዉብ

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ