1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈጥሮ ሃብት፤ የዕድገት ጸጋ ወይስ መርገምት?

ረቡዕ፣ ግንቦት 29 1999

በዓለም ላይ ዛሬ ለልማት የሚበጅ የተፈጥሮ ሃብት ሳይጎላቸው በድህነትና በተመጽዋችነት የሚታወቁት ታዳጊ ተብዬ አገሮች ብዙዎች ናቸው። የተፈጥሮው ጸጋ ተጠቃሚዎች ሃብቱን አውጥተው የሚገለገሉበት ባዕዳንና ለነርሱው ያደሩ እፍኝ የማይሞሉ ገዢዎች እንጂ ባለቤቱ ሕዝቡ አይደለም። እንደ ቺሌ የገበያ ሁኔታ ያስገኘውን ትርፍ መጠቀሙ ሲያከራክርስ?

https://p.dw.com/p/E0cs
ምስል AP

ታዳጊ የሚባሉት አገሮች ምዕራቡ ዓለም ባሰፈነው የኤኮኖሚ ሥርዓት ሥር ለገበያ በሚያቀርቡት ምርት የሚገባውን ያህል ተጠቃሚ የሆኑበት ጊዜ ነበር ማለቱ ሲበዛ ያስቸግራል። እንግዲህ አንዱ መሪር ሃቅ፤ የችግሩ ገጽታ ይህ ሲሆን ሌላው ደግሞ በተሻለ የገበያ ሁኔታም ሃብቱ ባፈራው ገንዘብ የሕዝብን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ሲያዳግት መታየቱ ነው። የመዳብ ዋጋ ዛሬ በዓለም ገበያ ላይ ከሶሥት ዓመታት በፊት ከነበረው ከፍ ብሎ ነው የሚገኘው። ከአሥር ዓመታት በፊት በእሢያው የኤኮኖሚ ቀውስ ወቅት አንድ ፓውንድ መዳብ ከሰባ የአሜሪካ ሣንቲም በላይ አያወጣም ነበር። ዛሬ ያንኑ የሚያህለው በሶሥት ዶላር ይሸጣል። ይህ ደግሞ በዓለም ላይ ታላቋ መዳብ አምራች ለሆነችው ላቲን አሜሪካዊት አገር ለቺሌ ታላቅ አትራፊነት ነው።

ይሁንና ጉዳዩ የማስደሰቱን ያህል ትርፉን የመጠቀሙ ሁኔታ በአገሪቱ ያስከተለው ክርክር ለፕሬዚደንት ሚሼል ባቼሌት የራስ ምታት መሆኑ አልቀረም። ከመዳብ ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ ለምን ተግባር በሥራ ላይ ይዋል? በዚህ ጥያቄ በሕብረተሰቡ ውስጥ የሃሣብ ስምምነት የለም። አንዱ ወገን ገንዘቡ ይቀመጥ ወይም በቁጠባ ይያዝ፤ ሌላው ደግሞ ወጪ ይደረግ ይላል። በማዕድን አፈር የተሞሉ ግዙፍ የጭነት መኪናዎች በየዕለቱ ቹኪካማታ የተሰኘውን ማዕድን እየለቀቁ ይጓዛሉ። በዓለም ላይ ታላቁ የሆነው የመዳብ ማዕድን በሰሜን ቺሌ በአታካማ ምድረ-በዳ የሚገኝ ግዙፍ ጉድጓድ ሲሆን እ.ጎ.አ. ከ 1910 ዓ.ም. አንስቶ መዳብ ሲወጣበት ቆይቷል። የቹኪቻማታ ማዕድን አንድ ምዕተ-ዓመት ያህል እየተቆፈረ መዳብ ሲቀልብ ከቆየ በኋላ ዛሬ ጥልቀቱ 900 ሜትር መድረሱ ነው የሚነገረው።

ቺለ በዓለም ላይ መዳብን ለውጭ ገበያ ከሚያቀርቡት አገሮች ቀደምቷ ስትሆን በዓለም ገበያ ላይ ከሚሸጠው መዳብ ሲሦው የሚመነጨውም ከዚህችው አገር ነው። አብዛኛው የማዕድን ውጤት ደግሞ ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓና በተለይም ወደ ቻይና ይላካል። ቻይናን ካነሣን አይቀር በተፋጠነ ዕድገት ላይ የምትገኘው እሢያዊት አገር የጥሬ ሃብት ጥም የመዳብ ዋጋ ባለፉት ሶሥት ዓመታት እየናረ እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል። ለቺሌ ቢቀር ከገበያው አንጻር የመልካም ዘመን ጎህ ቀዷል። ሆኖም የአገሪቱ ፕሬዚደንት ሚሼል ባቼሌት በመጋቢት ወር 2006 ዓ.ም. የሥልጣን ዘመናቸውን ሲጀምሩ ያደገው የመዳብ ዋጋ ዕድልም ፈተናም ነው ነበር ያሉት።

ፕሬዚደንቷ በእርግጥም የተናገሩት ምን ያህል ሃቅን ያዘለ እንደነበር ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም። ባቼሌት ከዚያን ወዲህ በተከታታይ የሠራተኛ አድማና ተቃውሞ ተወጥረው ነው የቆዩት። ቀዩ ወርቅ እየተባለ በሚጠራው መዳብ ንግድ የተገኘው የዋጋ ዕድገት በአገሪቱ አሻራውን አላሣየም ሲሉ የሚያማርሩት ጥቂቶች አይደሉም። እነዚሁ ገንዘቡ ለትምሕርት፣ ለጤና፣ ለተሻለ ደሞዝ፤ ለልማትና የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል መውጣት አለበት ባዮች ናቸው። ጉዳዩ በቺሌ መገናኛ አውታር ዘንድ ያለማቋረጥ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ሲቆይ ሕብረተሰቡን በሁለት ጎራ መክፈሉም አልቀረም።

አንደኛው የመንግሥቱን የበጀት ቁጠባ ይደግፋል፤ ሌላኛው ገንዘቡ በሥራ ላይ መዋሉን ነው የሚመርጠው። የኋለኛውን አመለካከት ከሚያንጸባርቁት ፖለቲከኞች አንዱ ቶማስ ሂርሽ ናቸው። ሂርሽ ባለፈው ምርጫ ታናሹን የግራ-አዘንባይ ፓርቲዎች ጥምረት “Juntos Podemos Mas” “በጋራ የበለጠ እናፈራለን” እንደማለት ነው፤ ወክለው የቀረቡት ዕጩ ነበሩ። ግን ስብስቡ ከመጀመሪያው የምርጫ ዙር ሊያልፍ አልቻለም፤ 6 ከመቶ ባልሞላ ድምጽ ተወስኖ ይቀራል። የሆነው ሆኖ ቶማስ ሂርሽ ሠርቶ አደሩ ሕዝብ የጥቅሙ ተጋሪ ሊሆን ይገባዋል ይላሉ።

“ሠራተኛው ድምጹን ጎላ አድርጎ የደሞዝ ጭማሪ በጠየቀ ቁጥር ለዓመታት አገሪቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው የምትገኘው፤ የሚጫል ነገር አይደለም ሲባል ነው የኖረው። ለአኔ ይህ አሣፋሪ ድርጊት ነው። ለነገሩ መንግሥት አሁን ጊዜው የተሻለ መሆኑን አረጋግጧል። ግን ሠራተኛው ከኬኩ ጥቂት እንኳ እንዲደርሰው ሲጠይቅ መንግሥት የሚለው፤ አዎን ጊዜው ተሻሽሏል፤ ሆኖም ለችግር ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ነው። በዛ፤ ይበቃል። በጎና አስቸጋሪ ጊዜያት በሚል የክርክር ዘይቤ የሕዝቡ ችግሮች ምን ጊዜም መፍትሄ ሊያገኙ አይችሉም”

ለነገሩ ቺሌ በዕድገት፣ ዝቅተኛ የውጭ ዕዳና የተረጋጋ የምንዛሪ ይዞታ ለላቲን አሜሪካ አርአያ ተብላ ነው የምትታየው። ይህም ሆኖ ግን አገሪቱ ሃብቷን በተጣጣመ ሁኔታ ለሕብረተሰብ ማከፋፈል ባለመቻል ችግር ተወጥራ ነው የምትገኘው። በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት ቺሌ ከብራዚል ቀጥላ ብሄራዊ ሃብት ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የሚከፋፈልባት የላቲን አሜሪካ አገር ናት። 16 ሚሊዮን ከሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ 3,2 በመቶው የሚኖረው በድሀነት ነው። ከማንኛውም የኤኮኖሚ ችግር ተላቆ የሚኖረው ሕዝብ ከአሥር በመቶ አይበልጥም።

ከዚህ ሌላ መካከለኛው የሕብረተሰሰብ ክፍል ወይም መደብ በብድር ዕዳ የተወጠረ ሲሆን የኑሮው ውድነትም በላቲን አሜሪካ ተወዳዳሪ የሌለው ነው። ቺሌያውያን ዜጎች እንደሚሉት ለሁሉ ነገር መክፈል አለባቸው። ደህናዎቹ ትምሕርት ቤቶችና ሆስፒታሎች በግል የሚተዳደሩ ናቸው። የመንግሥት ትምሕርት ቤቶች በአንጻሩ አስፈላጊው ብቃት ይጎላቸዋል። አንድ አስተማሪ ለሃምሣ ተማሪዎች ቢደርስ ነው፤ አስፈላጊው የትምሕርት መሣሪያም በሚገባ የተሟላ አይደለም። የጤና ጥበቃው ዘርፍም ቢሆም ሲበዛ ደካማ ነው። ዋና ከተማይቱ ሣንቲያጎ ውስጥ አንድ ሆስፒታል ብቻ ነው አንድ ሚሊዮን ተኩል የሚሆን ሕዝብን መንከባከብ ግድ ሆኖበት የሚገኘው።

ከዚሁ ሌላ በብዙሃኑ ድሆችና በጥቂቶቹ ሃምታሞች መካከል ያለው ልዩነት በአንድ ቦታ የጸና ነው። ለተራው ዜጋ ከፍተኛ ወደሆነ የሕብረተሰብ ክፍል ወይም የኑሮ ደረጃ መሸጋገሩ ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ቺሌ ውስጥ ማን የት አካባቢ መኖሩ፣ የሚማርበትና የመነጨበት ቦታ ለዕድሉ ወሣኝ ነው። ብሎንድ ማለት ቢጫማ ጸጉርና ነጭ የቆዳ ቀለም ለያንዳንዱ ዕርምጃ በር ከፋች መሆኑም አልቀረም። በመንግሥት ትምሕርት ቤት ለተማረ ዜጋ ግን ለተሻለ ኑሮ የተገኘውን መንገድ ሁሉ የሚዘጋ ነው። ለምሳሌ ያህል የሣንቲያጎ-ዴ-ቺሌ ነዋሪ ሆነው የከተማይቱን ማዕከል ያልረገጡ ብዙዎች አሉ። እነዚህ ዳር ዳሩን የሚኖሩት ቺሌያውያን ከድሃም ድሃ የአገሪቱ ዜጎች መሆናቸው ነው። ልጆቻቸው አድገው አንድ ቀን ለዩኒቨርሲቲ ትምሕርት መብቃታቸውን ሊያምኑ ቀርቶ አያልሙትም። ከነዚሁ አንዷ ጌማ ካቢዬሬስ እንደምትለው ልጆቹ የአንደኛ ደረጃ ትምሕርት ካጠናቀቁ እንኳ ደስተኞች ናቸው።
ዛሬ በየቦታው ከፍተኛ የትምሕርት ደረጃ ነው የሚጠየቀው። ሌላው ቀርቶ በቤት ሠራተኝነት ለመቀጠር እንኳ ትምሕርት አጠናቀሃል-አጠናቀሻል ተብሎ መጠየቅ አለ። ጌማን የመሳሰሉ ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ወደ ግል ትምሕርት ቤት ለመላክ የገንዘብ አቅም የላቸውም። አንድ የግል ትምሕርት ቤት በየወሩ በነፍስ-ወከፍ በእያንዳንዱ ሕጻን እንደ ደረጃው መጠን ከ 35 እስከ 100 ኤውሮ ወጪን ይጠይቃል። የቤተሰቡ የወር ገቢ ደግሞ ከመቶ ኤውሮ አይበልጥም። ብዙሃኑ ቼሌያውያን ይህ የትምሕርት ሥርዓቱ ችግር ካልተፈታ አገሪቱ ወደፊት ለመራመድ ባለመቻሏ በሃሣብ ይስማማሉ። የሚመረጠው የሕብረተሰብ መደብ ሳይለይ ሁሉንም እኩል የሚያስተናግድ የትምሕርት ሥርዓት ነው።

ለዚህ እርግጥ የመንግሥቱ ሥርዓተ-ትምሕርት ጥራት የሰመረበት ሊሆን ይገባዋል። እስካሁን ከዝቅተኛው የሕብረተሰብ መደብ የኋላ ኋላ ለዩኒቨርሲቲ ትምሕርት የሚበቁት አሥር በመቶው ሕጻናት ብቻ ናቸው። ችግሩ እርግጥ ለቺሌ አዲስ ነገር ሆኖ አይደለም። ግን አሁን የመፍትሄው ጥሪ ማየሉ አገሪቱ በመዳብ ሃብቷ የምታገኘው ገቢ በመጨመሩና ገንዘቡ በመኖሩ ነው። ሶሻሊስቷ ሚሼል ባቼሌት በ 1990 ዓ.ም. በተመራጭ ፕሬዚደንትነት ቤተ-መንግሥት ሲገቡ የተሻለ ዘመን ተሥፋ ያቀነቀኑት ጥቂቶች አልነበሩም።

እርሳቸውም በተለይ በማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ ቃል በመግባት ነበር ሥራቸውን የጀመሩት። የአገሪቱ የጤና ጥበቃና የትምሕርት በጀት ከፍ እንዲል መደረጉም አልቀረም። ይህም ሆኖ ግን የተሻለ ነገር የጠበቁት ብዙዎቹ ዛሬ ቅር የተሰኙና ይበልጥ ሊደረግ በተቻለ ነበር ባዮች ናቸው። በሌላ በኩል ይህን የብዙሃኑን አመለካከት የቀድሞው የቺሌ መንግሥት የበጀት ዕቅድ ተቋም ባልደረባ የነበሩት የኤኮኖሚ ባለሙያ ካረን ቬልትስል አይቀበሉትም። አስተያየታቸውን ሲገልጹ፤
“እንበል ወጪውን እንጨምር! የሃኪሞችን ደሞዝ ማሳደግ ወይም በሺህ የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችን ማነጽ፤ ማለት የቺሌን የቤት ችግር መፍታት ይቻላል። ግን ቺሌን በአስቸኳይ የሚያስፈልጓት መኖሪያ ቤቶች ሣይሆኑ ትምሕርት ነው። ደህና፤ ለመምሕራን ደሞዝ እንጨምር! ይህ ለደሞዝ የሚወጣው ተጨማሪ ወጪ ግን በዘላቂነት መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው። የመዳብ ዋጋ ነገ እንደገና ሊወድቅ ስለሚችል በዚህ በጊዜ በተገደበ ሁኔታ ዘላቂ በጀት ማስፈን አይቻልም። እንግዲህ ሃላፊነት የሚሰማን ከሆነ ከዛሬው ሁሉንም ገንዘብ ማውጣት የለብንም”

ካረን አያይዘው እንደሚሉት የቺሌ መንግሥት ጥብቅ የበጀት ቁጠባ መርህ ማስፈኑ ትክክለኛ ዕርምጃ ነው። የዕዳውን መጠን የሚገድብ ጣራ መበጀቱንም ይደግፉታል። የአገሪቱ የኤኮኖሚ ሁኔታ ጥሩም ሆነ መጥፎ ቁጠባው ጊዜ ሳይመርጥ መቀጠል ይገባዋል ባይ ናቸው። በሌላ በኩል ግን ዛሬ የመዳብ ዋጋ መናር በፈጠረው ጥሩ አጋጣሚ የሚገኘውን ትርፍ ለአገሪቱ ዕርምጃ መልሶ በሥራ ላይ መዋሉ ጠቃሚ እንደሆነ የብዙሃኑ ዕምነት ነው። ለማንኛውም ቺሌ ውስጥ የመዳቡን ሃብት አስመልክቶ የሚካሄደው ክርክር በማሕበራዊው ዘርፍ ይዞታ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ቹኪካማታ የብሄራዊው የመዳብ ተቋም የ CODELCO ንብረት የሆነ መንግሥታዊ ማዕድን ነው። ይሁንና በቺሌ መዳብ የሚነግደው ብቸኛው ኩባንያ አይደለም። የግል ኩባያዎችም ይህን የአገሪቱ ጸጋ የሆነውን ማዕድን በሰፊው ያወጣሉ። በ 2005 ዓ.ም. ከወጣው ከአምሥት ሚሊዮን ቶን በላይ የሚመዝን ማዕድን የኮዴልኮ ድርሻ 1,7 ሚሊዮን ብቻ ነበር። ቀሪው፤ ማለት ሁለት ሶሥተኛው ለገበያ የቀረበው እንግዲህ በግል ኩባንያዎች መሆኑ ነው።

መንግሥታዊው ተቋም ከግል ኩባንያዎቹ ጋር የመፎካከር ከባድ ችግር ነው ያለበት። እንደሌሎቹ የቺሌ መንግሥታዊ ኩባንያዎች ሁሉ ከግሎቹ የበለጠ አርባ በመቶ ግብር መክፈል ይኖርበታል። ኮዴልኮ ከዚህ በገንዘብ ሚኒስትሩ መሥሪያ ቤት ፊት ካለበት ግዴታ ባሻገር አሥር በመቶ ገቢውን ለአገሪቱ ጦር ሃይል እንዲገብር ሕጋዊ መርህ የተጣለበትም ተቋም ነው። ይህ ገንዘብ የት እንደሚደርስ ደግሞ ከፕሬዚደንቷ፣ ምናልባትም ከጥቂት ሚኒስትሮችና ከራሱ ከጦር ሃይሉ በስተቀር የሚያውቅ ማንም የለም። ሕጉ እንደሚለው ከሆነ ገንዘቡ ለጦር መሣሪያና ለሠራዊቱ ይዞታዎች ተሃድሶ መውጣት ስላለበት በያዝነው 2007 ዓ.ም. ለጦር መሣሪያ ግዢ አንድ ሚሊያርድ ዶላር መፍሰስ ሊኖርበት ነው። የተቀረው የኩባንያው ገንዘብም የሚፈሰው ወደ መንግሥት ካዝና ነው። ይህ ነው እንግዲህ ዛሬ አገሪቱ በመዳብ ገበያው መድራት ሳቢያ ያገኘችውን ትርፍ ለማሕበራዊና ለቴክኖሎጂ በሥራ ላይ ማዋሉን አዳጋች ያደረገው። በአጠቃላይ የቺሌም ሆነ የሌሎች በተፈጥሮ ጸጋ የታደሉ አገሮች፤ አፍሪቃን ጨምሮ ለሕዝብ እንዲጠቅም ከውጭ ኩባንያዎች ዕጅ ቀስ በቀስ መውጣቱ፤ ከገዢዎች የሥልጣን ተጽዕኖና ምዝበራም መላቀቁ ግድ ነው የሚሆነው። አለበለዚያ የተፈጥሮ ጸጋ ጸጋ መሆኑ ቀርቶ መርገምትነቱ ይቀጥላል።