1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ስንብት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 28 2008

የቱርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አሕሜት ዳቩቶግሉ ከፓርቲ እና የመንግስት ኋላፊነታቸው እንደሚለቁ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዝዳንት ረቺፕ ጣይብ ኤርዶኻን ጋር ባለመስማማታቸው ስልጣን ይለቃሉ ቢባልም እስካሁን ልዩነታቸው በግልጽ አልታወቀም።

https://p.dw.com/p/1IjLf
Türkei Ahmet Davutoglu Premierminister
ምስል Reuters/U. Bektas

[No title]

የቱርኩ ጠቅላይ ሚንስትር አሕሜት ዳቩቶግሉ በመጪዉ ግንቦት አጋማሽ ሥልጣን እንደሚለቁ ትናንት አስታውቀዋል። ያለፉትን 20 ወራት ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ጎን ለጎን የገዢው የፍትሕ እና ልማት ፓርቲን (AKP) በሊቀ-መንበርነት የመሩት ጎምቱ ፖለቲከኛ ስልጣን የሚለቁበትን ምክንያት በይፋ አልተናገሩም። ፓርቲያቸው ግን በዚህ ወር መገባደጃ በሚያደርገው ድንገተኛ ጉባዔ አዲስ መሪ ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል። ፕሬዝዳንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት በፕሬዝዳንታዊው ቤተ-መንግስት ከመጋረጃ ጀርባ ያደረጓቸው ምክክሮች ውጤት ባለማምጣታቸው ልዩነታቸው ፈንድቶ መውጣቱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር አሕሜት ዳቩቶግሉ ግን ለፓርቲያቸው ተወካዮች የስልጣን ስንብታቸውን ባስታወቁበት ንግግር ከፕሬዝዳንት ኤርዶኻን ጋር ተፈጥሯል የተባለውን መቃቃር ወደ ጎን ትተው በጥንቃቄ የተመረጡ ቃላትን ብቻ ተጠቅመዋል።።

« እስከ መጨረሻ እስትንፋሴ ድረስ ለፕሬዝዳንቱ ያለኝን ታማኝነት እቀጥላለሁ። ማንም ሰው በፕሬዚደንታችን አንፃር ስናገር ሰምቶ አያውቅም። ወደ ፊትም አይሰማም። ይህ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። የኔ ከስልጣን መልቀቅ ለራሳቸው መጠቀሚያ እንዲያውሉት አልፈልግም። እንደ ቱርክ ፕሬዝዳንት እና እንደ አጋሬ የፕሬዝዳንቱ ክብር የእኔም ክብር ነው። የእርሱ ቤተሰቦች ክብር የእኔም ክብር ነው። የእሱ ቤተሰብ የእኔም ቤተሰብ ነው።»
ጠቅላይ ሚንስትር አሕሜት ዳቩቶግሉ ከፓርቲ ስልጣናቸው ለመልቀቅ የወሰኑት ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ከቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት መሰረት «የፓርቲውን አንድነት ለማስጠበቅ» ሲባል መሆኑን መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የቱርክ መንግስት ስልጣንን ጠቅልለው ለመያዝ ወስነዋል ከሚባሉት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን የአገሪቱን ፓርላሜንታዊ የፖለቲካ መዋቅር በመቀየር ስልጣኑን ለፕሬዝዳንቱ ጠቅልሎ የሚሰጥ ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ የማድረግ እቅድ እንዳላቸው ይነገራል። የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዳቩቶግሉን ስንብት አምረው ተቃውመዋል። ቱርካውያንም የተከፋፈለ አቋም እያንጸባረቁ ናቸው።
«ይህ አስገራሚ ክስተት ቢሆንም ያልተጠበቀ አይደለም። በመካከላቸው የፖለቲካ ቁርሾ እንደሚኖር የታወቀ ነው። ፕሬዝዳንቱ ስልጣኑን ጠቅልለው ለመያዝ እንቅፋት የሚሆንባቸውን ሁሉ እያስወገዱ ነው።»
ሑርዬት የተሰኘው የቱርክ ዕለታዊ ጋዜጣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስንብት «በፓርቲው ውስጥ አዲስ ምዕራፍ» እንደሚሆን ጠቅሶ ጽፏል። የተቃዋሚው ኩምሑርርዬት ጋዜጣ በበኩሉ «የቤተ-መንግስት መፈንቅለ መንግስት» ብሎታል። እንደ ተንታኞች ከሆነ የአሕሜት ዳቩቶግሉ ስንብት ፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን ለስላሳ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለመሾም መንገድ ይከፍትላቸዋል። ለአንዳንድ ቱርካውያን ውሳኔው ልክ ነው።
«ታላቁ መሪያችን (ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶኻን ) ይህ ያመኑበት በመሆኑ ተግባራዊ መደረግ አለበት። ይህ በጣም ጥሩ ሁኔታ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደስተኛ አልነበሩም ማለት ነው። ስለዚህ ጠንክሮ የሚሰራ ሌላ ሰው ያመጣሉ። ሁሉንም ነገር መቃወም ልክ አይደለም። ታላቁ መሪያችን የፈለገው ነገር ሁሉ ይፈጸማል። ስለዚህ ትክክለኛ ውሳኔ ነው።»
ፕሬዝዳንት ራቺፕ ጣይብ ኤርዶኻን እና ወዳጆቻቸው የተመሰረተው የፍትሕ እና ልማት ፓርቲ አወቃቀር መሰረት ሊቀ-መንበሩ አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ይመራል። ፕሬዝዳንቱ የጠቅላይ ሚንስትር አሕሜት ዳቩቶግሉ ስንብት በመንግስታዊ መዋቅሩ ውስጥ ምንም አይነት ክፍተት እንደማይፈጥር መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።

Türkei Ahmet Davutoglu und Tayyip Erdogan
ምስል Getty Images/AFP/A. Altan
Symbolbild Islam Türkei Moschee Minarett
ምስል picture-alliance/dpa/K. Kleist-Heinrich


እሸቴ በቀለ


አርያም ተክሌ