1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱኒዝ-ቤንጋዚ ትሪፖሊዎች ደስታ-ቡረቃ

ሰኞ፣ ጥቅምት 13 2004

የሶሪያም ሆነ የየመን ሕዝብ ብሶት ምሬት ግን ከሊያ ሕዝብ መክፋቱን ከሕዝቡ አኗኗር የተሻለ ምስክር የለም።የባሕሬን ሕዝብ ጥያቄ፥ የጥያቄዉ ፍትሐዊነትም ከሊቢያ ሕዝብ ቢበልጥ እንጂ ሊያንስ አይችልም።የሊቢያን አምገን በጦር ሐይል ያስወገደዉ ዓለም-የባሕሬንን ሕዝባዊ አብዮት በታንክ የጨፈለቁትን---

https://p.dw.com/p/RskH
ቱኒዝያ መራጮችምስል DW


24 10 11

ቱኒዚያ የወደፊት ሕጓን አርቃቂ መሪዎችዋን መረጠች።ቱኒዞች ተደሰቱ።
ሊቢያ የረጅም ጊዜ መሪዋን አስከሬን እንደዘረረች ነፃነት አወጀች።ቤንጋዚ-ትሪፖሊ ቦረቀች።ዕሁድ።የቱኒዝ-ቤንጋዚ ትሪፖሊዎች ደስታ-ቡረቃ መሠረት መነሻችን፣ የእስከ እሁድ ጉዟቸዉ ማጣቃሸ፣ የአረቦች ሕዝባዊ አብዮት ድል-ድክመት፣የብያኔዉ እንዴትነት መድረሻችን ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ባለፈዉ ሰኔ-ፓሪስ ፈረንሳይ የተሰበሰቡት የቡድን ሥምንት አባል ሐገራት መሪዎች ለቱኒዚያና ለግብፅ ሃያ ቢሊዮን ዶላር ለመርዳት-ማበ ደር ቃል ገብተዋል።የአዉሮጳ ሕብረት ብቻዉን ከሁለት ሺሕ አስራ-አንድ-እስከ ሁለት ሺሕ አስራ-ሰወስት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያ አቆጣጠር ነዉ) ለቱኒዚያ የሰጠና የሚሰጠዉ ድጋፍ 5.33 ቢሊዮን ዶላር ነዉ።

ከቱርክ እስከ አዉትትሬሊያ፣ ከቻይና እስከ ስዑዲ አረቢያ የሚገኙ ሐገራትም አምባገነን ገዢዎቻቸዉ በሕዝባዊ አብዮት ለተወገዱላቸዉ ለቱኒዚያና ለግብፅ ሚሊዮነ-ሚሊዮናት ዶላር ረድተዋል ወይም ለመርዳት ቃል ገብተዋል።ፖለቲካዊ ሞራላዊ ድጋፍ፣ ሰብአዊ ርዳታ ያልሰጠ ወይም ለመስጠት ቃል ያልገባ የዓለም ሐገር ድርጅትም የለም።

Libyen Jubel Feier Befreiung
ሊቢያ ፌስታምስል dapd

ቤን ዓሊና ሆስኒ ሙባረክ ከተወገዱ ማግስት ጀምሮ ዓለም ሁለቱን ሐገራት በየመስኩ ግን እንደየአቅሙ ለመርዳት የመረባረቡ ሰበብ ምክንያት ለብዙዉ፥- በየሐገራቱ፣ በአካባቢዉ፣ በዓለምም የየራስን ጥቅም ለማስከበር፣ የበላይነትን ለማስጠበቅ፣ ለተቀረዉ፥-ወገንተኝነትን ለማሳየት፣ ለሌላዉ ለዓለም አድራጊ-ፈጣሪዎች ፍላጎት ተገዢነቱን ለማረጋገጥ ከመሆን ብዙ አይዘልም።

የዕርዳታ-ድጋፉ አይነት መጠን፣ የየረጂዎቹ አላማ ፍላጎት የመለያየቱ ርቀት አንዳዴም ተቃርኖ ባንድ ነገር ይጠባል-እንዲያዉም አንድ ነዉ።የረጂዎቹ ይፋዊ ሰበብ።«የቱኒዚያና የግብፅ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመሥረት የሚያደርገዉን ትግል ለመደገፍ»ይላሉ-ሁሉም።

የዓለም አድራጊ ፈጣሪዎችም በነሱ ቅኝት የሚዘምረዉ ዓለምም «እደግፈዋለሁ» የሚለዉን የሁለቱን ሐገራት ሕዝብ አብዮት ያቀጣጠለዉን ያን ወጣት ለማሰብ-መዘከር ግን ፍላጎት ጊዜዉ ትዉስታዉም የላቸዉም።የኖርዌዉ የኖቤል ሸላሚ ድርጅት የዘንድሮዉን የሰላም ኖቤል ለፍትሕና ለእኩልነት የታገሉ ላላቸዉ ሸልሟል።ያ ወጣት ግን ለገለልተኛዉ ሸላሚ ድርጅት ምንም ነዉ።

የተለያዩ ድርጅቶች፣ የመብት ተሟጋች ተቋማት፣ አሐጉራዊ ማሕበራት ሌሎችም በየዓመቱ እንደሚያደርጉት ሁሉ ዘንድሮም ለፍትሕ፣ ለነፃነት፣ ለሰብአዊ መብት ክብር የታገሉ-ያሏቸዉን ሸልመዋል።ያን ወጣት ከቁብ የቆጠረዉ ግን የለም።መሐመድ ቦዋዚዚ።እሳቸዉ ግን እንዴት ይርሱት።እናት ናቸዉ።

«ይሕ ምርጫ» አሉ ማኖዉቢያ ቦዋዚዚ ድምፅ ከመስጠታቸዉ በፊት «ሰብአዊ ክብርና ነፃነት ለማስጠበቅ ለተሰዋዉ ልጄ የድል አድራጊነቱ ምስክር ነዉ»አከሉ የሐምሳ ሰወስት አመቷ ወይዘሮ።

የአብዛኛዉን የአረብ አምባገነናዉ አገዛዝ የነቀነቀዉ ሕዝባዊ አብዮት ሰበብ-ምክንያቱ ብዙ፣ መሠረቱ ጥልቅ፥ የብዙ ዘመን ጥርቅም ብሶት ዉጤትነቱ በርግጥ አያነጋግርም።የፈላጭ-ቆራጭ ገዢዎቹ ግፍ ያንገሸገሸዉ የሃያ-ስድስት አመቱ ቱኒዚያዊ ወጣት ታሕሳስ አስራ-ሰባት ሁለት ሺሕ አስር አካሉ ላይ ያርከፈከፈዉ ቢንዚን-እራሱ ላይ የጫራት ክብሪት እሱን እንዳነደዱት-ሁሉ ብሶት ያንተከተከዉን ሕዝብ ቁጣ ማቀጠጠሉ፥ ሕይወቱን እንዳጠፉ ሁሉ፥ የአምባገኖችን ፍፃሜ ማብሰሩ ግን አያጠያይቅም።

ቱኒሶች ቦዋዚዚን በቀበሩ፣ የሃያ-ሰወስት ዘመን አምባገነን ገዢያቸዉ ባባረሩ በአስረኛ ወሩ ትናንት መረጡ።የርዕሠ-ከተማ ቱኒዝ ነዋሪ ሙራድ እንዳለዉ ድምፅ አሰጣጡ ለብዙዉ ቱኒዚያዊያዊ የወደፊት መሪዉን በነፃነት የመምረጡ ዋቢ ብቻ አይደለም-ያለፈዉ ጨቋኝ ሥርዓት የመቀበሩ ማረጋገጪያም እንጂ።

«የመምረጥ እድል ይኖረኛል ብዬ ብዙ አስቤ አላዉቅም ነበር።ሥመርጥ በይሕወቴ የመጀመሪዬ ነዉ።ፍላጎቴን ማንም ጠይቆኝ አያዉቅም።ፍላጎቴን ለመግለፅ ሥሞክርም የሚቀበለኝ አልነበረም።የድምፅ መስጪያ ኮረጆዎቹ ለኔ-የድምፅ መስጪያ ኮሮጆዎች ብቻ አይደሉም።ያለፈዉ ሥርዓት የመቀበሩ ምልክቶች ጭምር እንጂ።»

ሁለት መቶ አስራ-ሰባት መቀመጫዎች ላሉት ምክር ቤት የሰማንያ ፓርቲዎች ተወካዮችና በግል የተመዘገቡ አስራ-አንድ ሺሕ እጩዎች ተወዳድረዋል።ምክር ቤቱ የሐገሪቱን ሕገ-መንግሥት ያረቅቃል።ሕገ-መንግሥቱ ፀድቆ የሚመረጥ መንግሥት እስኪመሠረት ድረስ ሐገሪቱን የሚያስተዳድሩ ጊዚያዊ መሪዎችንም ይሰይማል።

ድምፁን ለመስጠት ከተመዘገበዉ 7.2 ሚሊዮን ሕዝብ እስከ ሰማንያ በመቶ የሚገመተዉ መርጧል።ምርጫዉ በቱኒቲዚያ ታሪክ የመጀመሪያዉ ነፃ ምርጫ ነዉ።ከምረጡኝ ዘመቻ-እስከ ድምፅ አሰጣቱ የነበረዉ ሒደትም በአዉሮጳ ሕብረት የታዛቢዎች ቡድን የበላይ በሚሻኤል ጋሕለር አገላለፅ አስደናቂ ነበር።

«በአፃራዊ መመዘኛ የምረጡኝ ዘመቻዉ ሰላማዊ ነበር።ሒደቱ ሥርዓት ጠብቆ መከናወኑ እኔን በግሌ በጣም ነዉ ያስደነቀኝ።የተወዳዳሪዎቹ ማስታወቂያ በየተፈቀደዉ ሥፍራ ደንብ ሳያዛቡ ነበር-የተለጠፉት።መንግሥት በሚቆጣጠራቸዉ ቴሌቪዢን ጣቢያዎች ለያንዳዱ ተወዳዳሪ ፓርቲ የተሰጠዉ የሰወስት ደቂቃ ጊዜም ገንዘብ ያላቸዉ ትላልቅ ፓርቲዎች ተፅኦኖ ሳያደርጉበት ሁሉም ፓርቲዎች በእኩልነት፥ በተገቢዉ ሁኔታና ያለምንም እንቅፋት ነበር የተጠቀሙበት።»

Befreiungsfeier in Libyen
ዓብዱጀሊልምስል dapd

የቱኒዚያ ሕዝባዊ አብዮት ከአደጋ ነፃነዉ ማለት ያሳስታል።በምርጫ፥ በርዳታ ወይም በሌላ ሰበብ የዉጪም የዉስጥም ብልጣብጦች፥ የሐይማኖት አክራሪዎች ጠልፈዉ ሊጥሉት ወይም ለየራሳቸዉ መጠቀሚያ ሊያዉሉት ይችላሉ።ለእስከ ዛሬዉ ድል-ስምረት ዋና መሠረቱ ግን የቱኒዚያ ሕዝብ ቦዋዚዚን የመሳሰሉ ወጣቶቹን ሕይወት የሰዋበትን ሕዝባዊ አብዮት-በራሱ ፍላጎት፥ ያለ ብዙ ጣልቃ ገብነት ልዩነቱን አቻችሎ፥ በጋራ ግን ብቻዉን በመታገሉ ነዉ።

«በደስታ ብዛት እንቅልፍ ባይኔ ሳይዞር ነዉ-ያደርሁት» አሉ የስልሳ ሁለቱ አዛዉንት።ድምፅ ሰጡ።

ተደሰቱም።ደስታዉ እሷን አስነባት።«ሲበዛ አስደሳች፥ አስገራሚም ነዉ።ይሕን ዕለት ለረጅም ጊዜ ስንጠብቀዉ ነበር።ተስፋችን ተመናምኖም ነበር።አሁን ግን የምለዉ የለኝም።አይኖቼ ያነባሉ።»

የሕዝባዊ አብዮት ሁለተኛ ታላቅ ድል።

ከደቡብ-ምሥራቅ ድንበር ማዶም ፌስታ ቡረቃ ነበር።ሊቢያ። ፎኒሲያኖች ወይም ቤርበሮች ነባሮቹን የኒዮሊትክ ነገዶችን ወረዉ ካርቴዥን ሲመሰርቱ ፈንድቀዉባት ነበር።ግሪኮች ፎኒሲዎችን፥ ፋርሶች ግሪኮችን፥ ሮሞች ፋርሶችን፥ አረቦች ሮሞችን፥ ቱርኮች አረቦችን፥ ጣሊያኖች ቱርኮችን ሲያስገብሩባትም በየዘመናቸዉ ፈንጥዘዉባታል።

የነዑመር ሙክታር የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ፍልሚያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ በ1951 ለነፃነት ሲያበቃት-ንጉስ ኢድሪስ ነፃነት አዉጀዉባት፥ ሕዝብ አስፈንድቀዉባት ነበር።በ1969 ሻለቃ ሙዓመር ቃዛፊ የመሯቸዉ የጦር መኮንኖች የንጉስ ኢድሪስን ዙፋናዊ አገዛዝ አስወግደዉ ሥልጣን ሲይዙ የሊቢያ ሕዝብ ነፃ ወጣ አሰኝተዉ፥ ድፍን ሊቢያን ጮቤ-አስረግጠዉት ነበር።

ትናንት ተራዉ የነሙስጠፋ አብዱል ጀሊል ነዉ።እነ አብዱ ጀሊል እንደ ታማኝ አገልጋይ፥ እንደ ጥሩ ተመሪ የታዘዙ፥ ያገለገሏቸዉን የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን አስከሬን ሚሲራታ ላይ ዘርረዉ ፎኒሲያዎች፥ ግሪኮች፥ፋርሶች፥ ሮሞች፥ አረቦች፥ ትሮኮች፥ ኢጣሊያኖች ፥ንጉስ ኢድሪስ፥ ኮሎኔል ቃዛፊ በየዘመናቸዉ እንዳስደረጉት ቤንጊዚ፥ ትሪፖሊን አስቦረቁ።

ከስልሳ ዓመት ከኢጣሊያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣችዉን ሐገር ዳግም ነፃ አወጣን አሉ።በቃዛፊ መገደል የተደሰተ እንጂ በይፋ ያዘነ-የዓለም መሪ የለም።የቀድሞዎቹ አማፂያን ትሪፖሊን ከተቆጣጠሩበት፥ ቃዛፊ እስከተገደሉበት፥ ቃዛፊ ከተገደሉበት እስከ ትናንት ያላባራዉ ፍንደቃ-ቡረቃ ግን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ዉጊያ፥የፓሪስ-ለንደን፥ የኒዮርክ-ብራስልስ፥ የቀጠር-ሪያድ ከሁሉም በላይ የሁሉም የበላይ የዋሽግተን ሁለንተናዊ ርብርብ ዉጤት እንጂ የእነ አብዱጀሊል በሳል አመራር ድል ብቻ ነዉ ሊባል ጨርሶ አይቻልም።ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማም ሌላ አላሉም።

«በዚሕ ሳምንት አሜሪካ ለዓለም የምትሰጠዉን አመራር ማደሳችንን የሚያሳዩ ሁለት ጠንካራ ማስታወሻዎች አይተናል።ኢራቅ የሚገኘዉ ቀሪ ጦራችን ከዚሕ ቀደም በገባነዉ ቃል መሠረት በዚሕ ዓመት ማብቂያ ወደ ሐገሩ እንደሚገባ ሳስታዉቅ በኩራት ነዉ።ሊቢያ ዉስጥ ደግሞ የሙዓመር ቃዛፊ ሞት የሊቢያን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከልና ጨቋኙን አገዛዝ ሰብረዉ ነፃ እንዲወጡ ያደረግንላቸዉ ርዳታ ተገቢ መሆኑን ያረጋግጣል።»

የቃዛፊ መገደል፥ የገዳይ-አስገዳዮች ድል የምሥራች የዓለም መገናኛ ዘዴዎችን ባጨናነቀበት ባለፈዉ ሐሙስ የብሪታንያዉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በድብቅ ከሆልም-ሶሪያ አጩልጎ ብልጭ ያደረጋት መፈክር «የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ርዳታ እንደልጋለን» ትላለች።ቦምብ-ሚሳዬልን እንደ ጥሩ መፍትሔ የሚያምነዉ ዓለም የሳዳምን፥ ወይም የቃዛፊን እጣ ለአሰድ ለማከፈል-ማቀድ አለማቀዱ አሁን አይታወቅም።

የሶሪያም ሆነ የየመን ሕዝብ ብሶት ምሬት ግን ከሊያ ሕዝብ መክፋቱን ከሕዝቡ አኗኗር የተሻለ ምስክር የለም።የባሕሬን ሕዝብ ጥያቄ፥ የጥያቄዉ ፍትሐዊነትም ከሊቢያ ሕዝብ ቢበልጥ እንጂ ሊያንስ አይችልም።የሊቢያን አምገን በጦር ሐይል ያስወገደዉ ዓለም-የባሕሬንን ሕዝባዊ አብዮት በታንክ የጨፈለቁትን ሐይላት እሹሩሩ የማለቱ ሐቅ ነዉ-የእዉነቱ ተቃርቶ-ሕቅታ።

የሊቢያ የብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ፕሬዝዳት መስጠፋ አብዱል ጀሊሊ በትናንቱ ንግግራቸዉ የየመን እና የሶሪያ ሕዝብ ትግል ለድል እንዲበቃ ተመኝተዋል።የባሕሬንን ስም ቢያነሱ-ግን ከወንበራቸዉ የሚነሱበትን ቀን ከመቁረጥ እንደማይተናነስ አላጡትም።

የንንግራቸዉ አብዛኛ ክፍል ከድልአድራጊነት ይልቅ ብዙዎቹን የድል-ተካፋዮች በመዘርዘር ማመስገን መሙላትም ግድ ነበረባቸዉ።እና በጎሳ የተከፋፈለዉን፥ እሳቸዉና ብጤዎቻቸዉ የቀድሞዉ ሥርዓት አገልጋይ በመሆናቸዉ ቅር የተሰኘዉን ሕዝብ መማፀን።«አብዮቱ ግቡን እንዲመታ እና ለሊቢያ መፃኤ-እድል መቻቻል፥ይቅር ባይነትና እርቀ-ሠላም አስፈላጊዎች ናቸዉ።»

እንደ ቱኒዚያ ብጤዎቹ ሁሉ ብዙ መሐመድ ቦዋዚዚዎችን ሰዉቶ፥ በጋራ ግን ብቻዉን ታግሎ ገዢዉን ያስወገደዉ የግብፅ ሕዝብ፥ ብዙዎች እንደሚያምኑት የሐይማኖት ቁርቁስ፥ የአክራሪ-ለዘብተኞች ሽኩቻ፥ የጣልቃ ገቦች ሻጥር ትብትብ-ድርን በዘዴ ከበጣጠሰ ከተመኘዉ መድረስ አይገደዉም።በሰብአዊ ልማት ከአፍሪቃ የመጀመሪያዉን ደረጃ የሚያይዘዉ ሊቢያዊ፥ ሐገሩን ዳግም ለመገንባት፥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመስረት እዉቀት ሐብቱ እንደልቡ ነዉ።ሁሉንም ለማድረግ የሁሉንም አድራጊዎች ፊት-ፍላጎት ማየት ትዕግስቱ እስከየትነት፥ የሰለለች የአንድነት ገመዱን-ማደንደን የመቻሉ ብልጠት ማጠያየቁ ነዉ ፈተናዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰመን።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ



ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ