1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቲክሪቱ ዉጊያና ፀረ-ISIS ዘመቻ

ሰኞ፣ የካቲት 30 2007

የዓለምና የአካባቢዉ ሐያላን ላለፉት አስራ-ሁለት ዓመታት የበላይነትን ለማረጋገጥ የገጠሙት ሽኩቻ ሱኒ ኩርዶችን ከሱኒ አረቦች፤ ሱኒ አረቦችን፤ ከሺዓ-አረቦች፤ ሱኒ ኩርድ፤ ሱኒ አረቦችን ከሺዓ ፋርሶች ጋር ደም አቃብቷል።ሽኩቻዉ አሁን መናሩ ደግሞ አISIS ቢጠፋ እንኳን የጦርነቱ ዑደት ፍፃሜ አለመሆን እንዳይጠቁም ማስጋቱ ይቀርም

https://p.dw.com/p/1EnoT
ምስል Reuters/Al-Sudani

የኢራቁ ጠቅላይ ሚንስትር ሐይደር አል-አባዲ «ዓለም ከኛ ጋር ነዉ» ይላሉ።አለበሉም።የኢራቅና የሶሪያ (ላቬንት) እስላማዊ መንግሥት (ISISI፤ ISIL ወይም ዳኢሽ የተሰኘዉን አክራሪ ቡድን ለማጥፋት ከስልሳ በላይ መንግሥታት በቀጥታ፤ ሌላዉ ዓለም በተዘዋዋሪ ይዋጋል።ካለፈዉ ነሐሴ ጀምሮ ዓለም ባንድ ያበረበረበት ዉጊያ እስካሁን የድል ጭላንጭል የታየበት ቲክሪት ላይ ነዉ።የቲክሪቱ ዉጊያ ገና ለድል ሳይበቃ ግን ዩናይትድ ስቴትስን ከኢራን፤ ሳዑዲ አረቢያን ከሶሪያ ባንድ ያሳበረዉ ጦርነት ለድል ቢበቃ እንኳን ድሉ የሌላ ጦርነት መጀመሪያ የመሆኑ ሥጋት ማረበቡ ነዉ ዚቁ።የቲክሪቱ ዘመቻ መነሻ፤ ለመጠፋፋት የሚያደቡት መንግሥታት አንድነትና ሽኩቻ ማጣቀሻ፤ ድል-ሽንፈቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን ከወረረበት ከ2003 ጀምሮ(ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) አንደ ሁሉም የኢራቅ ከተሞች ሁሉ ከቦምብ-ጥይት፤ከመድፍ-ሚሳዬል ከሽብር እልቂት ሌላ-ሌላ አታዉቅም። ዛሬም ትነዳለች።ቲክሪት።

ከባቢሎኖች ዘመን ጀምሮ በከተማነት የምትታወቅ ጥንታዊ ናት።የቲግሪስን ወንዝ የተንተራሳች፤ ለም።ሥልታዊም ናት።ርዕሠ-ከተማ ባግዳድን ከሐገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ሞሱል ጋር የምታገኝ፤ የሳላዲን (ወይም ሳላሁዲን) ክፍለ-ግዛት ርዕሰ ከተማ፤ የ260 ስልሳ ሺሕዎች መኖሪያ ከተማ።ትክሪት።

Irak Tikrit Offensive gegen IS
ምስል Reuters/M. Raouf

ጥንት በዝነኛዉ የባቢሎን ንጉስ በናቦፖላሰር ወይም ናቦከደናፆር ምሽግነቷ ትታወቃለች። በመካከለኛዉ ዘመን ከኢራቅ እስከ ሶሪያ፤ ከፍልስጤም እስከ ግብፅ የሚደርሰዉን ሰፊ ግዛት በገዙት በሳላሕ አድ-ዲን ዩሱፍ ኢብን አዩብ የትዉልድ ከተማነቷ ሥም ዝናዋ በገሚስ ዓለም ናኝቷል።

በቅርቡ ዘመን ሳዳም ሁሴይን አል-ትከሪት ተወልደዉ፤ በስሟ ተሰይመዉ-አድገዉባት፤ ድፍን ኢራቅን አስገብረዉ፤ በአሜሪካኖች ከሥልጣን ተወገደዉ፤ በአሜሪካኖች ተማርከዉባታል።ቲክሪት።አሜሪካኖች የሳዳም ሁሴይንን መንግሥት ካጠፉ ወዲሕ በተቆጠረዉ አስራ-ሁለት ዓመት ደግሞ-የአሜሪካ ጦርና የአል-ቃኢዳ ታጣቂዎች፤ የሱኒዎችና የሺዓ ሚሊሺያዎች፤ የISIS እና የባግዳድ መንግሥት ጦር መፋለሚያ ሆናለች።የእስራት-ማሰቃያ፤ የግድያ ሽብር፤የእልቂት ጥፋት ማዕከል እንደሆነች አለች።ዛሬም ቀጥላለች።

ሥልታዊቷን ጥንታዊቱን ከተማ ከአክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ለማስለቀቅ የኢራቅ መንግሥት ጦር ከምድርና ከአየር፤ በሺዓ-መራሹ የኢራቅ መንግሥት የሚደገፈዉ ሐሺድ ሻዓቢ የተሰኘዉ የሺዓ ሚሊሺያ ከምድር፤ ቁዱስ የተባለዉ የኢራን ልዩ ጦር ከምድር፤ የአሜሪካ ጦር ከአየር መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተዋል።

ባለፈዉ ሳምንት በአምስት አቅጣጫ የዘመተዉ ሰላሳ ሺሕ ጦር የቲክሪት መዳራሻ አነስተኛ ከተሞችን እየተቆጣጠረ ትናት የከተማይቱን ገሚስ መያዙ ተዘግቧል።በዉጊያዉ ሥለጠፋዉ ሕይወት፤ ሐብትና ንብረት በግልፅ የተዘገበ ነገር የለም።የኢራቁ ጠቅላይ ሚንስትር ሐይደር አል-አባዲ ግን ISISን ቲክሪት ላይ ዓይደለም ሞስልም ላይ እንደሚደመስሱት እርግጠኛ ናቸዉ።ዓለም፤ በእሳቸዉ አገላለፅ ከነሱ ጋር ነዉና።

«ሞስል የሚገኙት ቅርሶች በሙሉ በሰነድ የተመዘገቡ ናቸዉ።እናገኛቸዋለን።በጥረታችን (ሁሉ) ዓለም ከጎናችን ነዉ።»

አዎ፤ ሐያል-ሐብታሙ ዓለም በርግጥ ከባግዳዶች ጎን ነዉ።ከሰሜን ጫፍ ካናዳ እስከ ደቡብ ጥግ አዉስትሬሊያ ከትልቂቱ ዩናይትድ ስቴትስ እስከ ትንሺቱ ቀጠር ISISን ለማጥፋት ኢራቅና ሶሪያ ዉስጥ ይዋጋል።ዉጊያዉ ከ1979 ጀምሮ ሲሻቸዉ በእስራኤል-ፍልስጤም ዉዝግብ፤ሲያሰኛቸዉ በሊባኖስ እስራኤል ጦርነት፤ አሁን በቅርቡ ደግሞ በኑክሌር ጦር ቦምብ ምርምር ሰበብ ለመጠፋፋት የሚዛዛቱት ዩናይትድ ስቴትስና ኢራን ባንድ ጎራ አሰልፏል።

ሶሪያ ላይ በኢራን የሚደገፈዉን የፕሬዝዳንት በሽር አል-አሰድን መንግሥት ለማስወገድ የሚፋለሙ ሐይላትን የሚደግፉት ዩናይትድ ስቴትስ፤ የአዉሮጳና የአረብ ተከታዮችዋ ልክ እንደነሱዉ ሁሉ የበሽር አል-አሰድን ጦር የሚወጋዉን ISISን በጋራ ይደበድባሉ።ለወትሮዉ የፖለቲካዉን ትብብር የሚገልጠዉ «የጠላትሕ ጠላት ወዳጅሕ ነዉ»-አይነት ብሂል ነበር።ዛሬ ግን እንዲያ አይመስልም።«የጠላትሕ ጠላት-ወዳጅሕም ጠላትሕም ነዉ» አይነት አባባል ካለ በርግጥ ይስማማል።

በቲክሪቱ ዉጊያ አክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ተሸነፈ፤ አልተሸነፈ በርግጥ ለቲክሪቶች፤ለሞሱል፤ ለባግዳዶችም ከፖለቲካ-ወታደራዊ ድል-ሽንፈትም አልፎ የመኖር-አለመኖር ጥያቄም ነዉ። የናይጄሪያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ቦኮ ሐራም የኢራቅ ብጤዉን የሚረዱ ተፋላሚዎችን ለማዝመት ቃል መግባቱ ምዕራብ አፍሪቃዉያንን በጣሙን ናይጄሪያዉያንን ማነጋገሩም አይቀርም።

ለዋሽግተን፤ ባግዳድ፤ ቴል-አቪቭ፤ ለሪያድ፤ አማን፤ ካይሮ ትላልቅ ፖለቲከኞች ግን ትልቁ ጥያቄ አክራሪዉን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ቲክሪት፤ ከዚያ በፊትና በኋላስ የሚወጋዉ እግረኛ ጦር ወይም ሚሊሻ የማና በማን የሚታዘዝ ነዉ የሚለዉ ነዉ።የቲክሪቱን ዉጊያ በቅርብ የሚከታተለዉ የሮይተሩ ጋዜጠኛ ዶመኒክ ኢቬንስ አጭር መልስ አለዉ።

Irak Haider al-Abadi IS Tikrit PK
ምስል picture-alliance/EPA

«አብዛኞቹ የሺዓ ሚሊሺያዎች በኢራን የሚደገፉና ኢራን ያስታጠቀቻቸዉ ናቸዉ።በምሥራቁ ግንባር የሚዋጉትን ሐይላት በበላይነት የሚያዙት የኢራኑ ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒ ናቸዉ።እሳቸዉ አብይ ተሳትፎ እያደረጉ ነዉ።ሥለዚሕ ኢራኖች ሚሊሺያዎቹን በአዛዥና መመሪያ ሰጪነት፤ምዕራባዉያን ደግሞ በአስታጣቂነት ይሳተፋሉ።»

ብርጌድየር ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒ ቁድስ የተሰኘዉ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ልዩ ኮምንዶ ጦር አዛዥ ናቸዉ።ኢራን ከዉጪ መንግሥታት ወይም ቡድናት ጋር የምታደርገዉ ወታደራዊ ዘመቻዎችን የሚወስኑት እሳቸዉ ናቸዉ።በወታደራዊ ማዕረግ የሚበልጧቸዉ የጦር መኮንኖች ብዙ ናቸዉ።የሳቸዉ አዛዥ ግን አንድ ሰዉ ነዉ።የኢራን ላዕላይ መሪ አያቶላሕ አሊ ሁሲይን ኻሚኒ።አሜሪካዊዉ ጡረተኛ ጄኔራል ጃክ ኪን ያክሉበታል።

«የቁድስ ሐይልን ማዘዝ ከጀመሩ ከሃያ-ዓመት በልጧቸዋል።አንድ አለቃ ነዉ ያላቸዉ።እሱም ላዕላይ መሪ ኻማኒ ናቸዉ።ከመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆነ ከሳቸዉ የሚበልጥ ማዕረግ ላላቸዉ የጦር አዛዦች አይታዘዙም።በየአካባቢዉ የሆነ ነገር ከተፈጠረ-እሳቸዉ እስፍራዉ ይገኛሉ።የኢራን ሥርዓት የዉጪ መርሕን ለማሥፈፀም ቁጥር አንድ መሳሪያ ናቸዉ።»

ኢራን ለሐማስ፤ ለሒዝቡላሕ፤ለኢራቅ ሺዓ ሚሊሺያዎች፤ ለሶሪያ መንግሥት፤ አሁን ደግሞ ለየመን ሁቲ ሚሊሻዎች ወታደራዊ ድጋፍ ከሰጠች-ፈቃጁ ጄኔራል ሱሌይማኒ ናቸዉ። ለወዳጆቻቸዉ ጀግና ምርጥ አዋጊ፤ ድንቅ ሥልት ነዳፊ፤ ለጠላቶቻቸዉ ጭካኝ፤ አሸባሪና አዋኪናቸዉ።

በተለይ የዩናይትድ ስቴትስ፤ የእስራኤል፤የሳዑዲ አረቢያ፤የግብፅና የዮርዳኖስ፤ ፖለቲከኞችና የጦር አዛዦች የሱሌይማኒ ሥም ሲነሳ ደማቸዉ ይፈላል።ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪነት ወንጅላቸዋለች።ዩናይትድ ስቴትስ፤የአዉሮጳ ሕብረት፤የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ ማዕቀብ ጥለዉባቸዋል።

በመሠረቱ ዩናይትድ ስቴትስ የሳዳም ሁሴይንን መንግሥት አስወግዳ የባግዳድ ቤተ-መንግሥትን በኢራን ለሚደገፉት የሺዓ ፖለቲከኞች ስታስረክብ ኢራቅን ለቴሕራን ማስረከቧ መሆኑን ለማወቅ ነብይነትን አይጠይቅም ነበር ።የዛሬዉን አሸባሪ ድርጅት ISISIን ያጠናከሩት ሐይላት በኢራን በሚደገፈዉ የባግዳድ የሺአዎች መንግሥት በሱኒዎች ላይ የሚፈፅመዉ በደል ያንገፈገፋቸዉ ወገኖች መሆናቸዉን ለመገንዘብ አስተንታኝ ባላስፈለገ ነበር።

Propagandabild IS-Kämpfer ARCHIV
ምስል picture-alliance/abaca/Yaghobzadeh Rafael

ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራና የምታስተባብራቸዉ መንግሥታት ISISን የሚወጋ የአየር ጦር ከማዝመታቸዉ በፊት ጄኔራል ሱሌማኒ የሚመሩት የሺዓ ሚሊሺያ ኢራቅ ዉስጥ ከአሸባሪዉ ቡድን ሐይላት ጋር ሲፋለም እንደነበር የተደበቀ አልነበረም።ጄኔራል ሱሌማኒ የቲክሪቱን ዘመቻ መምራት ማስተባባራቸዉ ሲነሳ ሰሞኑን ግን ወትሮም የሚታወቀዉ አዉነት ዋሽግተንና ተባባሪዎችዋን እንዳዲስ ማንገብገቡ ነዉ ግራዉ።

«በ2006 ሒዝቡላሕ እስራኤሎችን ከሊባኖስ ሲያስወጣ-እዚያ ነበሩ።ከ2004 ጀምሮ የኢራቅ ሺዓ ሚሊሺያዎችን ኢራን ዉስጥ ሁለት ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ሲያሰልጥኑና የተሻሻለ ፍንጂ ሲያስታጥቁ ነበር። ኢራቅ ዉስጥ ከተገደሉት 4400 የአሜሪካ ወታደሮች ሁለት ሺሕ ያሕሉ እሳቸዉ ባሰለጠኗቸዉ ሐይላት እንደተገደሉ ፔንታጎን ይገምታል።የሶሪያ አማፂያን አሰድን ለመጣል ተቃርበዉ በነበረበት ወቅት አማፂያኑን መትተዉ አሰድ እንዲጠናከሩ ያደረጉት እሳቸዉ ናቸዉ።አሁን በቅርቡ የየመን ሁቲዎች በአሜሪካ የሚደገፈዉን መንግሥት ያስወገዱት እሳቸዉ እዚያዉ ድረስ ሔደዉ በሰጧቸዉ ድጋፍ ነዉ።»

ዩናይትድ ስቴትስ የጄኔራል ሱሌማኒን ተፅዕኖ ለመቋቋም ይመስል ዋና የጦር ጄኔራሏን ዛሬ ወደ ባግዳድ ልካለች።የጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች ጥምረት ሊቀመንበር ጄኔራል ማርቲን ዴምፕሲ ለባግዳድ ሹማምንት የሚያስተላልፉት መልዕክት ምናልባት ጄኔራል ሱሌይማኒን ከቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ራቅ ከማድረግ ያለፈ ተቀባይነት ማግኘቱን ግን ብዙዎች ይጠራጠሩታል።

Irak Tikrit Schiitische Freiwillige Kampf gegen IS
ምስል Getty Images/AFP/Al-Rubaye

በመሠረቱ ድፍን ኢራቅን እስከ ዛሬ፤ ዛሬና ምናልባት ወደፊትም የሚያተራምሰዉ ጦርነት የ2003ቶቹ የዋሽግተን-ለንደን መሪዎች ለሠላም፤ ዴሞክራሲ፤ ለፍትሕ-ብልፅግና ፅናት ያለመ ባሉት ወረራ-የተከፈተዉ የእልቂት-ሥደት-ጥፋት እቶን ዉጤትነቱ በርግጥ ሊያነጋግር አይገባም።

ከሳዳም ዉድቀት በኋላ ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ ባዓዚስት፤ሱኒይ፤ አል-ቃኢዳ፤ ወዘተ እያሉ፤ ሺዎችን ያስገደለ፤ መቶ ሺዎችን ያቆሰለ፤ ሚሊዮኖችን ያስደደዉ ጦርነት ሌላ ጦርነት ወለደ እንጂ ለሠላም የተከረዉ ነገር የለም።በጠላትነት የሚፈላለጉት መንግሥታት የጋራ ጠላታቸዉን ለማጥፋት ሳይስማሙ-የተስማሙበት ይሕ ያሁኑ የጋራ ጦርነትም ገና ለግሚስ ድል እንኳ ሳይደርስ ሽሚያ፤ ሽኩቻቸዉ ንሯል።

የዓለምና የአካባቢዉ ሐያላን ላለፉት አስራ-ሁለት ዓመታት የበላይነትን ለማረጋገጥ የገጠሙት ሽኩቻ ሱኒ ኩርዶችን ከሱኒ አረቦች፤ ሱኒ አረቦችን፤ ከሺዓ-አረቦች፤ ሱኒ ኩርድ፤ ሱኒ አረቦችን ከሺዓ ፋርሶች ጋር ደም አቃብቷል።ሽኩቻዉ አሁን መናሩ ደግሞ አISIS ቢጠፋ እንኳን የጦርነቱ ዑደት ፍፃሜ አለመሆን እንዳይጠቁም ማስጋቱ ይቀርም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ