የትራምፕ ቃለ-ምልልስ እና አውሮጳ
ሰኞ፣ ጥር 8 2009ማስታወቂያ
በቃለ ምልልሱ ላይ ትራምፕ የኔቶን አስፈላጊነት አጠያይቀዋል፣ ብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት ለመውጣት የወሰደችውን ውሳኔ በማድነቅ ሌሎችም የርሷን አርአያ ይከተላሉ ብለው እንደሚጠብቁም በቃለ ምልልሳቸው ጠቅሰዋል። ይህ አነጋገራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅሬታን ፈጥሮዋል። ቃለምልልሱን ተከትሎ በርካታ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ኅብረቱ አንድነቱን እና ዓለም አቀፍ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል። ትራምፕ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የተከተሉትን የስደተኞች አቀባበል ፖሊሲን በጥብቅ ነቅፈዋል።
«ታላቅ ፣ ታላቅ መሪ ነበሩ። ግን፣ በጣም ብዙ ጥፋት ያስከተለ አንድ ከባድ ስህተት የፈፀሙ ይመስለኛል። ይኸውም፣ ከየትም የመጡትን እነዚያን ሁሉ ሕገ ወጥ ስደተኞች ሀገራቸው ማስገባታቸው ነው። በርግጥም፣ ከየት እንደመጡ ማንም የሚያውቅ የለም።»
ከሥዩሙ አሜሪካዊ ፕሬዚደንት ትራምፕ ቃለምልልስ በኋላ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አውሮጳውያን ዕጣ ፈንታቸው በእጃቸው መሆኑን በማመልከት፣ 27ቱ የህብረቱ አባል ሃገራት ኤኮኖሚያቸውን ማጠናከር እና ወደፊት የሚጠብቁዋቸውን ፀረ ሽብሩን ትግል የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ማሸነፍ እንዲችሉ ጠንክረው እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
አርያም ተክሌ
አዜብ ታደሰ