1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቶጎና የፖለቲካው ቀውስ ሰለባዎች

ዓርብ፣ ጥቅምት 3 2010

በቶጎ ሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ እና የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፎር ግናስንግቤም ስልጣን እንዲለቁ በመጠየቅ ከጥቂት ወራት በፊት የተጀመረው ተቃውሞ  አሁንም እንደቀጠለ ነው።

https://p.dw.com/p/2lni6
Togo Protest #Faure Must Go
ምስል Getty Images/AFP/P. U. Ekpei

ቶጎ

በተቃውሞ ወቅት የፀጥታ ኃይላት በሰልፈኞች ላይ የፈጸሙት የኃይል ተግባር  የተነሳ ብዙዎችን ወደ ጎረቤት ሀገር እንዲሰደዱ ማድረጉ ተሰምቷል።

የቶጎ መንግሥት በስራ ቀኖች የፖለቲካ ተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ ቢከለክልም፣ 14 የቶጎ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተጠቃለሉበት ቡድን አነሳሺነት ደጋፊዎቻቸው በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ እና የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፎር ግናስንግቤም ስልጣን እንዲለቁ በመጠየቅ በዚህ ሳምንት ያካሄዱት ተቃውሞ በሚቀጥለው ሳምንትም እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል። ያይን እማኞች እንደገለጹት፣ በዚሁ ጊዜ ከፀጥታ ኃይላት ጋር ግጭት ተፈጥሮ፣ በተለይ በሰሜናዊ የሀገሪቱ ከፊል የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ብዙዎችም ቆስለዋል። የጦር ኃይሉን የኃይል ተግባር በመሸሽ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ወደ ጎረቤት ጋና ተሰደዋል። ፀረ መንግሥት ተቃውሞን ተከትሎ የተፈጠረውን ክትትል በመሸሽ ጋና የገቡት የቶጎ ዜጎች ሁሉ ከለላ ያገኙት በሰሜናዊ ጋና በምትገኘው የቼርፖኒ ከተማ ነው።  ወደጋና ከተሰደዱት መካከል የ50 ዓመቱ ያዎባ ኦስማን አንዱ ናቸው።
«  እስከዛሬ ሰዎችን ማሰር እንደቀጠሉ ነው። ንብረታችንን ሁሉ አቃጥለውብናል፣ ከለበስኩት በስተቀር ምንም የተረፈ የለኝም።  ጥያቄአችን ሕገ መንግሥቱ  በ1992 ዓም ወደነበረበት እንዲመለስ ነው። እና ልክ እንደ ጋና  በነፃ መኖር ነው የምንፈልገው።  ፎር ግናስንግቤ እና አባታቸው ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱን መርተዋል። ይህ ጥሩ ነውን? »
የቼርፖኒ መጠለያ ጣቢያ ባለስልጣናት በይፋ እንዳስታወቁት፣ በዚያ የቶጎ ስደተኞች ቁጥር አሁን ወደ 494 ከፍ ብሏል፣ ይኸው ቁጥር ከፍ ማለቱ አይቀርም።  
ይሁንና፣ ከስደተኞቹ ጋር ወንጀለኞችም ተቀላቅለው ሊገቡ እንደሚችሉ መስጋታቸውን በቼርፖኒ የብሔራዊ አደጋ መከላከያ መስሪያ ቤት ኃላፊ አማዱ ሱሌይማን ገልጸዋል።
« ስጋታችን አሁን ወደ ቼርፖኒ እየመጡ ባሉት በእውነት ከለላ ከሚሹት ስደተኞች መካከል እኩዮችም ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ነው። ይህን ለይቶ ማወቁ ለኛ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖብናል። ጋና ትልቅ ስጋት ተደቅኖባታል። ስለዚህ፣ ትክክለኛ ምክንያት ያላቸውን ከሀሰተኞቹ አጣርተው እንዲለዩልን የሀገራችንን ብሔራዊ ምርመራ ጽህፈት ቤትን እና የፍልሰት ጉዳይ መስሪያ ቤትን ጠይቀናል። »
በወቅቱ ከለላ ያገኝት ያዎባ ኦስማንን የመሳሰሉት ስደተኞች ግን ቶጎ ወደ 1992 ሕገመንግሥታዊ አሰራር የምትመለስበትን እና በጋና የሚታየው ዓይነት ስርዓተ ዴሞክራሲ የሚተከልበትን ዕለት እና ወደ ትውልድ ሀገራቸው ለመመለስ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
« የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ቶጎ ውስጥ ዴሞክራሲ እንደሚመጣ እናውቃለን። ሕገ መንግሥቱም እንደምንፈልገው እንደሚሆን እናውቃለን። እርግጥ፣ አሁን በኛ ላይ የኃይል ተግባር ይፈጽሙብናል። ይሁንና፣  ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል የሚፈልገው ሰው ቁጥር ከማይፈልገው በእጅጉ እንደሚበልጥ በሚገባ እናውቃለን። »

Faure Gnassingbe
ምስል AP

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ