1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይናና የአፍሪቃ ግንኙነት፤ ብዝበዛ ወይስ ሽርክና?

ረቡዕ፣ ጥር 30 1999

ሕዝባዊት ቻይና ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለይ ባለፉት ሁለት አሠርተ-ዓመታት ያለማቋረጥ ስታጠናክር ነው የቆየችው። በወቅቱም ፕሬዚደንት ሁ ጂንታዎ ለዚሁ ዓላማ በአፍሪቃ አገሮች እየተዘዋወሩ የሚያደርጉትን ጉብኝት ሊያጠናቅቁ እየተቃረቡ ናቸው። የቻይና በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ላይ በዚህ መጠን ማተኮር ዓቢይ መንስዔው በተቀዳሚ የጥሬ ሐብት ፍላጎት እንደሆነ አጠቃላይ ስምምነት አለ።

https://p.dw.com/p/E0dC

የአፍሪቃ የተፈጥሮ ጸጋ ዛሬ እንደቀድሞው በምዕራቡ ዓለም ብቻ ሣይሆን በተፋጠነ ዕድገት ላይ በሚገኙ ቻይናን በመሳሰሉ አገሮች ዘንድም ይበልጥ የዓይን ማረፊያ እየሆነ ሄዷል። የቻይና የአፍሪቃ ራዕይ፤ አድጎ የማሳደግ የልማት ሽርክና ወይስ ብዝበዛ? ይህ በወቅቱ ብዙ እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው። በሌላም ለመሆኑ አፍሪቃውያን ከዚህ ሂደት ተጠቃሚ የመሆን ዕድል አላቸው ወይ፤ ከሆነስ ደግሞ እንዴት? ይህም እንዲሁ ምላሽ ይጠይቃል።

የአፍሪቃ የተፈጥሮ ጸጋ፤ ያልተሟጠጠ ጥሬ ሐብቷ የውጭ መንግሥታት ማተኮሪያ መሆን የጀመረው አሁን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አይደለም። ምዕራባውያን ቅኝ-ገዢዎች ከአንድ ምዕተ-ዓመት በፊት አፍሪቃን እንደ ቅርጫ ስጋ ከተከፋፈሉ ወዲህ አንስቶ ያለና የነበረ ጉዳይ ነው። የኮንጎ፣ የደቡብ አፍሪቃ፣ የናሚቢያና የሌሎች ብዙዎች የአፍሪቃ አገሮችም ማዕድን ለውጭ ጥቅም ሲበዘበዝ ኖሯል። ይህም አፍሪቃ ዛሬ በልማት ኋላ ቀር ለመሆኗ፣ ተፈጥሮ ሳይበድላት ሕዝቧ ድሃና ተመጽዋች ሆና ለመቀጠሉ ዋናው ምክንያት ነው።

የጥሬ ሐብት ዕጥረት እየተስፋፋ፤ የበለጸጉትና በዚያው አቅጣጫ በዕድገት ላይ የሚገኙት አገሮች የኤነርጂ ፍጆት እየጨመረ በሄደበት በአሁኑም ጊዜ ቢሆን በተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች አማካይነት ሐብቱ መሟጠጡ መልኩን ለወጥ አድርጎ እንደሆን እንጂ አላቆመም። አዲስ ነገር ቢኖር ዛሬ በምዕራቡ ዓለም ላይ ቻይናን የመሰለ ብርቱ ተፎካካሪ መፈጠሩ ነው። እርግጥ የቻይና የኤኮኖሚና የፖለቲካ ተጽዕኖ በአፍሪቃ በሰፊው መጠናከር ብዙ ጥያቄዎችን ነው ያስነሣው።
ምዕራባውያን መንግሥታት የቤይጂንግን ባለሥልጣናት ለጥሬ ሐብት ጥቅምና ምርታቸውን በአፍሪቃ በገፍ ለማራገፍ ሲሉ ሰብዓዊ መብትን ከሚረግጡ ገዢዎች ጋር ይተባበራሉ፤ በጎ አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው ጥረትም መሰናክል ሆነዋል ሲሉ ይወቅሳሉ። ቻይና በበኩሏ በሰው አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ-መግባት አልፈልግም፤ በጋራ ጥቅምና በወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ማራመድ ነው ዓላማዬ ባይ ናት። የቤይጂንግ የአፍሪቃ ጥናት ኢንስቲቲቱት ባልደረባ ዌን-ፒንግ-ሄ የምዕራቡን ዓለምና የቻይናን የአፍሪቃ ፖሊሲ ሲያነጻጽሩ እንደሚሉት፤ “የቻይናና የአፍሪቃ ግንኙነት አዲስ መልክ ባለው ስልታዊ የወዳጅነት ትብብር ላይ የተመሠረተ ነው። አፍሪቃውያን አሁን ከማን መተባበር እንደሚፈልጉ መምረጡ የራሳቸው ፈንታ ሆኗል”

ሕዝባዊት ቻይና ዛሬ በአፍሪቃ ብዙ ገንዘብ በሥራ ላይ ታውላለች። በያካባቢው ገዢዎች ፍላጎት በመንገዶች ግንባታና በሌሎች መሰል ተግባራት በሰፊው ተሰማርታለች። ይህን ሁሉ የምታደርገው ደግሞ ለልማት ትብብሩ፤ ለምሳሌ የሰብዓዊ መብት ከበሬታን የመሳሰሉ አንዳች የፖለቲካ ቅድመ-ግዴታዎች ሳታስቀምጥ ነው። እርግጥ ቻይና በነጻ ለአፍሪቃ የምትለግሰው ነገር የለም። ለምትሰጠው ዕርዳታ ሁሉ በአንጻሩ በተለይ በክፍለ-ዓለሚቱ ጥሬ ሐብትና ገበዮች ላይ መሳተፉን ትፈልጋለች፤ አለባትም። እንግዲህ ቻይና አፍሪቃን በረጅም ጊዜ የጥሬ ሐብት ምንጯ፣ የርካሽ ሸቀጧ ማራገፊያና የሚጠቅሟትን ፋብሪካዎች የምታንጽበት ምድር ለማድረግ ቁርጠኛ ናት ማለት ነው።

የቻይናና የአፍሪቃ ንግድ ገና ከዛሬው እየደራ በመሄድ ላይ ይገኛል። ባለፈው 2006 ዓ.ም. እንኳ የሁለቱ ወገን የንግድ ልውውጥ 55 ሚሊያርድ ዶላር ደርሶ ነበር። ይህም ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር አርባ በመቶ ከፍ ያለ መሆኑ ነው። ቻይና በዚሁ ብሪታኒያን በመደረብ ሶሥተኛዋ ታላቅ የአፍሪቃ የንግድ ሸሪክ ለመሆን በቅታለች። ዕድገቱ ቀጣይ እንደሚሆንም ጨርሶ አያጠራጥርም። ቤይጂንግ ላይ በቅርቡ በቻይናና በአፍሪቃ መሪዎች መካከል ተካሂዶ የነበረው ታሪካዊ ግምት የተሰጠው የመሪዎች ጉባዔ ሽርክናው እንዲጠናከር ብርቱ መሠረት የተጣለበት ነው።

በሕዝብ ብዛቷ በዓለም ላይ ቀደምት የሆነችው ቻይና ከተፋጠነ ዕድገቷ አንጻር እየጠነከረ የመጣ የጥሬ ሐብት ጥሟን ለመወጣት ዕጣዋን ከአፍሪቃ በጥብቅ አስተሳስራለች። ይህም ከአሁኑ ጎልቶ የሚታይ ነው። በ 2005 ቻይና ውስጥ ለፍጆት ከዋለው ነዳጅ ዘይት ሶሶው የመነጨው ከአፍሪቃ፤ በተለይም ከሱዳን ነበር። በሱዳን ነዳጅ ዘይት የምታወጣው ቻይና ለወትሮው ምዕራባውያን ኩባንያዎች በቁጥጥራቸው ሥር ባቆዩት የናይጄሪያ የነዳጅ ዘይት ምንጭ ሣይቀር ሁለት ሚሊያርድ ዶላር አፍሳለች። ቤይጂንግ የአፍሪቃን ባለሥልጣናት ለማግባባት ያላንዳች ቅድመ-ግዴታ ብድር ታቀርባለች፣ የፖለቲካ ድጋፍ ትሰጣለች፤ ከመንገድ ሥራ እስከ ቤተ-መንግሥት ማነጽ ያላዳረሰችው ነገር የለም።

ታዲያ የቻይና የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ከገዢዎች አልፎ ለሕዝብ ያስከተለው ጥቅም አለ ወይ? በዚህ ረገድ ብዙዎች የተሥፋ ጭላንጭል አይታያቸውም። ከነዚሁ አንዱ የሆኑት የካርቱም ሣምንታዊ ጋዜጣ የሞኒተር አዘጋጅ አልፍሬድ ታባን እንደሚሉት፤ “በሱዳን የነዳጅ ዘይት ብዝበዛው የሚካሄደው በደቡቡ ሕዝብ ትከሻ ላይ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ መንደሮች ከምድር እንዲስተካከሉ ተደርገው ወድመዋል፤ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ነዋሪዎች ቤቶቻቸውን እየለቀቁ እንዲሄዱ ተገደዋል። ቻይናውያን ነዳጅ ዘይት ማውጣት እንዲችሉ እስከመገደል የደረሱም አሉ። ይህ ዘይት የሚበዘበዘው እንግዲህ በአካባቢው ነዋሪዎች ደምና ላብ መሆኑ ነው”

ይህን መሰሉ ትችት የሚሰማው እርግጥ ሱዳን ውስጥ ብቻ አይደለም። በሌሎች የአፍሪቃ አገሮችም የቻይና የጥሬ ሐብት ግፊት የማይዋጥላቸው ብዙዎች እንደሆኑ በሰሞኑ የፕሬዚደንት ሁ ጂንታዎ የአፍሪቃ ጉብኝት ሂደት እዚህም እዚያም መታየት፤ መሰማቱ አልቀረም። ሆኖም በአፍሪቃ መንግሥታት ዘንድ ሰፍ ድጋፍ ያለው የቻይና መስፋፋት ባለበት ይቀጥላል። ሁኔታው ይህ ከሆነ ከአፍሪቃውያን አንጻር እንዴት ከሂደቱ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል ነው ጥያቄው።