1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይናና የደቡብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ግንኙነት

ረቡዕ፣ ኅዳር 8 2003

ቻይና በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የኤኮኖሚ ተጽዕኖዋን ለማስፋፋት በምታደርገው ጥረት በተለይም በማዕድን ሃብት የታደለችውንና በአካባቢዋ በፊናንስ አገልግሎት ረገድ ቀደምት የሆነችውን ደቡብ አፍሪቃን ዋና ማተኮሪያዋ ታደርጋለች።

https://p.dw.com/p/QBPb
ምስል AP

በመሆኑም ምክትል ፕሬዚደንት ሺ ጂንፒንግ እየተፋጠነ የሚሄደው የአገራቸው ዕድገት የሚጠይቀውን የጥሬ ዕቃ ፍላጎት ለማረጋገጥ ከትናንት ወዲህ ደቡብ አፍሪቃን በመጎብኘት ላይ ናቸው። የሁለቱ አገሮች የንግድና የኤኮኖሚ ትብብር በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ከወቅቱ ጉብኝት ምንድነው የሚጠበቀው፤ ደቡብ አፍሪቃ ለመሆኑ ተጠቃሚ እየሆነች ነው ወይ?

ደቡብ አፍሪቃ በያመቱ ለቻይና የ 5,5 ቢሊዮን ዶላር የማዕድን ሃብት የምትሸጥ ሲሆን ከቻይና የሚገባው ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይም ያለማቋረጥ እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኝ ነው። የሁ-ጂንታዎ ተተኪ እንደሚሆኑ የሚነገርላቸው ምክትል ፕሬዚደንት ሺ የሁለቱ አገሮች የኤኮኖሚ ትብብር መስኮች እየሰፉ መሄዳቸውን እንደሚቀጥሉ ነው ትናንት በጉብኝታቸው መጀመሪያ የገለጹት።
የቻይናው ልዑካን ቡድን ከብዙ በጥቂቱ በማዕድንና በኤነርጂና መስኮች በሚደረግ የሁለት ወገን ትብብር ላይ ዛሬ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር የስምምነት ውሎችን እንደሚፈራረም እየተጠበቀ ነው። በአዳጊ ገበዮች ላይ የገበያ ተፎካካሪነት ብቃትን ለማራመድ የሚጥረው ጆሃንስበር ላይ ተቀማጭ የሆነ ድርጅት የፍሮንቲየር አድቫይዘሪይ ከፍተኛ ተጠሪ ሃና ኤዲንገር እንዳስረዱት ከጉብኝቱ የሚጠበቀው ውጤት ከዚህ ቀደም የተደረገ የስልታዊ ሽርክና ስምምነትን የሚመረኮዝ ነው የሚሆነው።

“ጉብኝቱን ከአጠቃላዩ ግንኙነት ጋር አጣምሮ መመልከቱ ጠቃሚ ይመስለኛል። ባለፈው ነሐሴ ወር፤ በትክክል በነሐሴ መጨረሻ ፕሬዚደንታችን ጆኮብ ዙማ 350 የንግድ ልዑካንንና በርካታ የካቢኔ ዓባላትን አስከትለው ቤይጂንግና ሻንግሃይን ጎብኝተው ነበር። እና በዚሁ አጋጣሚም ብዙ ውሎች መፈረማቸው አይዘነጋም። አንዱ ውል ደግሞ የቻይናንና የደቡብ አፍሪቃን አጠቃላይ ስልታዊ ሽርክና መፈጠር የሚመለከት ነበር”

ቻይና ከአውሮፓና ከሰሜን አሜሪካ ገሸሽ በማለት ንግድና መዋዕለ-ነዋይዋን በተፋጠነ ዕድገት ላይ ወደሚገኙት አገሮች ለማሸጋሸግ ትፈልጋለች። በዚህ ሂደቷ እንግዲህ ደቡብ አፍሪቃም አንዷ ማተኮሪያዋ ሆናለች። በሃና ኤዲንገር አመለካከት ታዲያ የወቅቱም ጉብኝት ይህን ያገናዘበና ትብብሩን በማስፋፋቱ ላይ ያለመ ነው።

“በቻይና የአፍሪቃ ፖሊሲ የመጠናከር ሂደት ደቡብ አፍሪቃ በአፍሪቃ ስልታዊዋ የቤይጂንግ ሸሪክ ሆና ነው የምትታየው። እርግጥ የንግድ ግንኙነቱ በወቅቱ የሚገኝበትን ደረጃ ከተመለከትን በተለይም በንግድና በመዋዕለ-ነዋይ በኩል ገና መሟጠጥ የሚኖርበት ብዙ ዕድል አለ። አሁን እየተካሄደ ያለው ጉብኝት ሁለት ዓላማ ነው ያለው። የመጀመሪያው ይህን የንግድ ዘርፍ በተለይም የማዕድን ሃብትን ማስፋፋትና መጠቀም መቻል ነው። በሌላ በኩል በኤነርጂና ኤሌክትሪክ ዘርፎች ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብዙ የሃይል ስርጭት መቋረጥና እጥረት ልምዶችን መቅሰማችን አልቀረም። ለነገሩ ማዕድኖች ብዙ ኤነርጂንና የኤሌክትሪክ ሃይልን ይጠይቃሉ። በሁለቱ መካከል ብዙ ትስስር ነው ያለው። እናም በዚህ በኩል መስፋፋት እንደሚኖር ይጠበቃል”

ደቡብ አፍሪቃ ብራዚልን፣ ሩሢያን፣ ሕንድንና ቻይናን የመሳሰሉት ብሪክ በሚል አሕጽሮት የሚጠሩ በተፋጠነ ዕድገት ላይ ያሉ የተራመዱ ሃገራትን ቡድን ለመቀላቀል ባላት ፍላጎት ሕዝባዊት ቻይናን እንደ ሞዴል አድርጋ ነው የምትመለከተው። ሆኖም ይህ ደቡብ አፍሪቃ በወቅቱ ካላት ሶሥት በመቶ ገደማ የሚጠጋ ዓመታዊ ዕድገት አንጻር ቢቀር በቅርቡ መሳካቱ ማጠያየቁ አይቀርም። ሃና ኤዲንገር እንደሚያስታውሱት ከሆነ ለነገሩ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ዕድሜም ያን ያህል ብዙ አይደለም።

“የቻይናና የደቡብ አፍሪቃ ግንኙነት ገና አምሥት ዓመት ዕድሜ ብቻ ያለው ነው። ማለት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ትስስር። ግንኙነቱ የሚካሄደውም በምክትል ፕሬዚደንቶች መሪነት ደረጃ ነው። በወቅቱ ግንኙነቱን ለማስፋፋት የተቋቋመውን የጋራ ብሄራዊ ኮሚሢዮን የሚመሩት እንግዲህ የደቡብ አፍሪቃው ምክትል ፕሬዚደንት ሞትላኬና የፕሬዚደንት ሁ ጂንታዎ ተተኪ እንደሚሆኑ የሚነገርላቸው ሺ ጂንፒንግ ናቸው። ይህ ኮሚሢዮን ደግሞ ግንኙነቱን ለማስፋፋት እጅግ ጠቃሚ የሆነ አካል ነው”

Wen Jiabao China EU GIpfel Brüssel
የቻይና ጠ/ሚ ዌን ዢባኦምስል AP

ያም ሆነ ይህ ቢቀር በወቅቱ በሁለቱ አገሮች የኤኮኖሚ ግንኙነት ተጠቃሚነቱ ለቻይና ያጋድላል። ደቡብ አፍሪቃ የንግድ ኪሣራዋን ለማለዘብ ብዙ ዕርምጃ ማድረግ ይጠበቅባታል ማለት ነው። ምናልባት በተወሰኑ ዘርፎች፤ እንበል በአርሻው መስክ ምርቶች በቻይና ገበዮች ላይ የመስፋፋት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ነው የሚታሰበው።

“የበለጠ ልንጠቀምበት የምንችለው ነገር አለ ብዬ አስባለሁ። እርግጥ ነው ቻይና በማዕድኑ መስክ ብቻ ሣይሆን የእርሻ ኢንዱስትሪን ጨምሮ በጠቅላላው ገበያ ላይ የበለጠ ድርሻ አላት። በዚህ በደቡብ አፍሪቃ አንድ የኢንዱስትሪ ዘርፍን ለመጥቀስ ያህል ለምሳሌ የአርሻ ምርት አውጪው ኢንዱስትሪ የተራመደ ነው። እናም በቻይና ገበዮች የፍጆት ፍላጎት መለወጥ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ቻይና ውስጥ ዛሬ ሰዎች ብዙ ስጋ፣ ፋራፍሬና መሰል ነገሮች ይበላሉ። ታዲያ ለደቡብ አፍሪቃ ነጋዴዎች ይህ ገበያ እያደገ የሚሄድ ነው። ቪኖን፣ ፍራፍሬንና አትክልትን ለመሸጥ ገበያው ግ’ዙፍ እየሆነ እንደሚሄድ አንድና ሁለት የለውም”

ይህ ሁሉ ከስልታዊው ሽርክና በሂደት የሚጠበቅ ሲሆን ደቡብ አፍሪቃ በወቅቱ የምትጠቀመው በአጠቃላዩ የኤኮኖሚ ግንኙነት ባህርይ ነው።

“እርግጥ ደቡብ አፍሪቃ በወቅቱ የምትጠቀመው በኤኮኖሚ ግንኙነት ደረጃ ነው። መረጃዎችን ከተመለከትን ባለፉት ዓመታት ከቻይና ያስገባናቸው ዕቃዎች ወይም ምርቶች ቢቀር በአንዳንድ ዘርፎች በዋጋ ብዙም የከፉ አልነበሩም። እናም ምንም እንኳ በምርትና በተለይም በጨርቃጨርቅ ንግድ ረገድ ፍጆታችን ግዙፍ ቢሆንም ቅሉ ጠቅመውናል ማለት ነው። በሌላ በኩል የደቡበ አፍሪቃ ታላላቅ ኩባንያዎች፤ የብረታብረትና የማዕድን፤ እንዲሁም ባንኮችና መድሕን ኩባንያዎቻችን ራሳቸው ወደ ቻይና ገበዮች መዝለቁ ተሳክቶላቸዋል። የሁለት ወገን ጥቅምን በማራመዱ በኩል ከቻይናም ፍላጎት መኖሩ የሚታይ ነው። እናም ይህን ማጠናከሩ ደቡብ አፍሪቃ ውስጠ አንዱ ትልቅ ተግባር ሆኖ ይቀጥላል”

የቻይናው ምክትል ፕሬዚደንት የደቡብ አፍሪቃ ጉብኝታቸውን እንዳበቁ በነዳጅ ዘይት ሃብት ወደታደለችው ወደ አንጎላና ከዚያም ወደ ቦትሱዋና ይዘልቃሉ። ይህ በዚህ እንዳለ የቻይና በአፍሪቃ የተፈጥሮ ሃብት ላይ አጥብቆ ማተኮር በሚስጥራዊ አያያዙና የሰብዓዊ መብት ይዞታን በሚጻረር ባሕርዩ ብዙ መተቸቱ ቀጥሏል። ለምሳሌ የዓለም ባንኩ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንኮዚ-ኦኮንጆ-ልዌአላ በአፍሪቃ የማዕድን ሃብት ላይ ዓይናቸውን ያሳረፉ የቻይና ኩባንያዎች የተሽፈነ ውል ማድረጋቸውን እንዲያቆሙና በመዋዕለ-ነዋይ ረገድም ግልጽ እንዲሆኑ ነው ያሳሰቡት።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ