1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይናና የጀርመን ትብብር በኅዋ ምርምር ፤

ረቡዕ፣ ጥቅምት 22 2004

ቻይና፣ በጎቢ በረሃ ከሚገኘው የኅዋ ጉዞ ማደራጃ ጣቢያዋ፣ ከጂኳን ፣ ትናንት ፤ «ሸንቺው 8» (ተዓምረኛ መርከብ እንደማለት ነው ትርጉሙ)የተባለችውን የጠፈር መንኮራኩር ወደ ኅዋ አምጥቃለች።

https://p.dw.com/p/RuXM
ምስል dapd

ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ረገድ ከጀርመን ጋር በተደረገ ምርምርም፤ ጀርመናውያን አንድ የምርምር ሰንዱቅ በተጠቀሰችው መንኮራኩር ልከዋል። መንኮራኩርዋ ያመራችው፤ ቻይና ባለፈው መስከረም ወደ ኅዋ ወዳመጠቀቻት 8,5 ቶን ወደምትመዝነው የጠፈር ጣቢያ (ላቦራቶር ) «ቲያንጎንግ 1 » ነው። ቲያንጎንግ ማለት የሰማይ ቤተ-መንግሥት ማለት ነው። ስለሆነም፤ «ሸንቺው 8» ከቲያንጎንግ ጋር እንድትገጣጠም ነው የሚደረገው። ይህ ዓላማና አቅድ ከተሣካ፤ ቻይና በሚመጡት ወራት በተጨማሪ ሁለት መንኮርኩሮች ታመጥቃለች በአንደኛው ጠፈርተኞች ጭምር ይላካሉ። ቻይና ፤ እ ጎ አ እስከ 2020 የተደራጀ የጠፈር ጣቢያ ለመመሥረት ነው የምትፈልገው። ከቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረትና ካሁኗ ሩሲያ እንዲሁም ከዩናይትድ እስቴትስ ቀጥሎ ቻይና 3ኛዋ የኅዋ ተመራማሪ መንግስት ለመሆን የበቃችው እ ጎ አ፣ ከ 2003 ወዲህ ነው።

ትናንት፣ «ሸንቺው 8 »ን ስትመጥቅ፤ በሥፍራው ተገኝተው ደስታቸውን ከገለጡት መካከል፤ ጀርመናውያን ሳይንቲስቶችም ነበሩ። የጀርመን የአየርና የኅዋ ጉዞ ጉዳይ መ/ቤት እንዳስታወቀው፤ «ሲምቦክስ» የተባለ የ 40 የሲጋራ ፓኬት መጠን ያላቸው ክፍሎች ያሉት የምርምር ሰንዱቅ በመንኮራኩሯ ወደ ኅዋ እንዲላክ አድርጓል። 17 የተለያዩ ከሥነ ህይወት ጋር እንዲሁም ከክብደት ማጣት ጋር የተያያዙ የምርምር ዓይነቶች ናቸው ጀርመናውያኑ እንዲከናወኑ ያቀዱት። የጀርመን የአየርና የኅዋ ጉዞ ጉዳይ መ/ቤት ባልደረባ ፔተር ፕሮይ---

«በተላከው ሰንዱቅ ውስጥ ምርምሩ የሚያተኩረው ከበሽታ የመከላከል አቅም ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፤በካንሠር ኅዋሳት ላይ ያተኮረ ምርምርም ይደረጋል። በተጨማሪም፣ ቀንድ አውጣና የውሃ አረንጓዴ ተልኳል። ሌላው ፕሮቲን እንደ አንጸባራቂ መስታውት መሰል ድንጋይ የሚለውጥበት ሙከራ ይሆናል።»

የቻይና የጠፈር መንኮራኩር «ሸንቺው 8 » በሁለት ቀናት ውስጥ ነው ከኅዋዋ የቤተ ሙከራ ጣቢያ ቲያንጎንግ አንድ ጋር መገጣጠም የሚኖርባት። ከባድ ተግባር ነው። እርግጥ ነው ፤ ይህ ፤ የ 10 ዓመታት ልምድ ላላቸው ፣ ለሩሲያውያንና አሜሪካውያን ቀላል ጉዳይ ነው። ለቻይና ግን፣ የጠፈር ጉዞ ጉዳይ ሊቅ፣ ቺ ፋረን እንደሚሉት ፣ አዲስ ተግዳሮት ነው።

«ሁለት መንኮራኩሮችን የማገጣጠሙ ሥነ ቴክኒክ የተወሳሰበና በዛ ያሉ እንከኖች ሊያጋጥሙ የሚችሉበት ሁኔታ ነው። ሁለቱንም መንኮራኩሮች በአንድ ምኅዋር ላይ እንዲገኙ ማብቃትና ማገጣጠም በኋላም መልሶ ማለያየት---ከባድ ተግባር ነው። »

ቻይና ፤ እ ጎ አ እስከ 2020 ፣ የራሷን የተደራጀ የኅዋ የምርምር ጣቢያ እስክትገነባ፤ ከጀርመን ጋር በዚህ ረገድ የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉ እንደማይቀር ነው የሚገመተው። ሁለቱ አገሮች፣ በመጪው ጸደይም ከኅዋ ምርምር ጋር በተያያዘ፤ አንድ ሌላ የትብብር ፕሮጀክት እንደሚኖራቸው ተገልጿል። የ «ሲምቦክስ» የምርምር ሰንዱቅ አንዱ የትብብር ማጠናከሪያ ምልክት ነው። አሁንም ፔተር ፕሮይ---

«ይኸው ትብብር፣ ለሁለቱም ወገኖች፤ አዲስ አጋርነትን በመፍጠር ጠፈርተኞች በሚላኩበት እርምጃ ጭምር አዲስ በር የሚከፍት ነው። ይኸው ተባባሪነት ለጀርመን ሳይንቲስቶች ምርምር ፤ ወደጠፈር ለሚደረግ ጉዞ ጭምር ፤ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት፤ በኅዋ ምርምር ጀርመን መሪ ድርሻ እንዳታበረክትም የሚያስችል ይሆናል።»

ጀርመን ከዩናይትድ እስቴታስና ከሩሲያም ጋር በዓለም አቀፉ የኅዋ የምርምር ጣቢያ ተሳትፎ አላት። ከቻይና ጋር የሚደረገው ትብብር ፤ ፕሮይ እንደሚሉት በፉክክር መልክ መታየት የለበትም። አንድ ግልጽ ጉዳይ አለ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ፤ ዓለም አቀፉ የኅዋ የምርምር ጣቢያ ከጥቅም ውጭ ሲሆን፤ በጠፈር የምርምር ጣቢያ እንዳደራጀች የምትገኝ ቻይና ብቻ ትሆናለች ማለት ነው።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ