1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና እንቅስቃሴ በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 1 2006

በአፍሪቃ ሀገራት የመሠረት ልማት ፕሮዤ ለማነቃቃት በሚታሰብበት ጊዜ ሁሉም የሚያስበው ስለ ቻይና ነው። ቻይና እአአ በ1960 ኛዎቹ ዓመታት በሶሻሊስታዊው ፕሮዤ አማካኝነት ከዛምቢያ እስከ ታንዛንያ የሚዘልቅ የባቡር ሀዲድ ግንባታን በገንዘቧ መርዳቷ ይታወሳል።

https://p.dw.com/p/1D7tg
Tansania Daressalam Chinesisches Entwicklungsprojekt
በታንዛንያ የቻይና ፕሮዤምስል Getty Images/AFP

እአአ ከ1990ኛዎቹ ዓመታትም ወዲህም ቻይና አፍሪቃ ውስጥ መንቀሳቀስ የጀመረችው የኤኮኖሚ ጥቅም ለማሟላት ነው። ይሁንና፣ ወደ ሀገሯ የጥሬ አላባ ፍላጎትዋን በንግድ ለማስገባት ለሌላ ጉዳይ ደንታ አትሰጥም ወይም ትኩረት አታደርግም በሚል ስለሷ ያለውን አመለካከት ለመቀየር ትፈልጋለች።  

ቻይና አፍሪቃ ውስጥ መንገዶችን፣ የእግር ኳስ ስቴድየሞችን በመስራት እና «ብራይትባንድ »የኢንተርኔት መስመሮችን በመዘርጋቷ ነው የምትታወቀው። በምላሹ ከአፍሪቃ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብትን ከአህጉሩ በንግድ ወደ ሀገሯ ታስገባለች። ቻይና ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ ሲነሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጎላው ይህ ነው። በዩኤስ አሜሪካ የሚገኘው የብሩኪንግስ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ቻይናዊትዋ ዩን ሱን እንደሚሉት፣ ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ ቻይና በወቅቱ ይህንን አመለካከት ለመቀየር እየሞከረች ነው።

Xi Jinping in Südkorea 03.07.2014 Seoul
ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግምስል Reuters

« ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ ቻይና በአፍሪቃ አኳያ በምትከተለው አሰራር ላይ አዲስ አካሄድ ታይቶዋል። በቻይና የውጭ ፖሊሲ ላይ አፍሪቃ ለቻይና የያዘው ትርጓሜ ከፍ ያለ ቦታ ተሰጥቶታል። ቻይና በአፍሪቃ ዘላቂ ልማት ለማስገኘት ለሚደረገው ጥረት ልዩ ትኩረት መስጠት ጀምራለች። »

ከጥቂት ጊዜ በፊት ቻይና ባወጣችው አንድ መጽሐፍ በአፍሪቃ ልታነቃቃቸው ያሰበቻቸውን ፕሮዤዎች በዝርዝር አስቀምጣለች። ከነዚህም 30 ሀኪም ቤቶች፣ 150 ትምህርት ቤቶች፣ 105 ታዳሽ የኃይል ምንጭ እና የውኃ ፕሮዤዎችን የመገንባት፣ እንዲሁም፣ ከ5,000 የሚበልጡ የግብርና ባለሙያዎችን የማሠልጠን ዕቅዶች ይገኙባቸዋል። እርግጥ፣ ቻይና ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ዓይነት ፕሮዤዎችን በአፍሪቃ ደግፋለች፣ ይሁንና፣ ይላሉ ዩን ሱን፣ እንዳሁኑ በይፋ አሳውቃ አታውቅም። የቻይና ታታሪነት ምን ያህል ማደጉን በወቅቱ ለመናገር አዳጋች ነው። ምክንያቱም፣ መንግሥት ይህንን በተመለከተ ይፋ መቀርዝር አያወጣም። ከዚህ በተጨማሪም፣ ብዙዎቹን ፕሮዤዎችን ስንመለከት የትኛው የልማት ርዳታ ፣ የትኛው ደግሞ ውዒሎተ ንዋይ መሆኑን መለየቱ አስቸጋሪ ነው።

እርግጥ፣ እስካሁን የቻይና ትኩረት ያረፈው በኤኮኖሚ ትብብሩ ላይ ነው። የቻይና መንግሥት እአአa በ1990 ኛዎቹ ዓመታት የተከተለው በዓለም አቀፍ ደረጃ የመንቀሳቀስ ሥልት መሠረት፣ የሀገሩን የነዳጅ ዘይት እና የከበሩ ማዕድናትን የመሳሰሉ የጥሬ አላባ ፍላጎት ለማርካት እና የኤኮኖሚውን ልማት ለማሳደግ በሚል እሳቤ የሀገሩ ተቋማት ከአፍሪቃ ጋር ኤኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲጀምሩ ይህንኑ ዓላማውን ከግብ እስካደረሰም ድረስ፣ ከፈላጭ ቆራጭ እና ሙስናን ካስፋፉ መንግሥታትም ጋር አብሮ ከመስራት ወደ ኋላ አላለም። እንደ ዩን ሱን አመለካከት፣ ይኸው አሰራሯም ብዙ ወቀሳ አፈራርቆባታል።

China Investment Afrika Äthiopien - Adama toll road Arbeiter
የአዳማ አውራ ጎዳናምስል AFP/Getty Images

« ይኸው ወቀሳ ስለ ቻይና ያለውን አመለካከት አብዝቶ ጎድቶታል፤ ብሎም፣ ቻይና በአፍሪቃ ያለችው ለአህጉሩ የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ስትል ነው ገጽታዋን አበላሽቶታል። እና እነዚህ እኩይ አስተያየቶች ቻይና አሁን ገጽታዋን ለመቀየር በጀመረችው ጥረት ላይ ወሳኝ ድርሻ አበርክተዋል።»

ቻይና የምታደርገው ትብብር ወይም ርዳታ በመጀመሪያ ደረጃ የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ የታለመ መሆኑን በናይሮቢ የሚገኘው የኤኮኖሚ ጥናት ተቋም ተንታኝ ኬንያዊው ዴቪድ ኦዊሮ አስታውቀዋል። « ቻይና የምትከተለው ሞዴል ወደ ሀገሯ ወደቦች የሚያደርስ መሠረተ ልማት መገንባት ነው። »

አንድ የቻይና ተቋም ከጥቂት ጊዜ በፊት በኬንያ አንድ ዓቢይ አውራ ጎዳና ሰርቷል፣ ይህ ቻይና በአፍሪቃ ለመገንባት ካቀደቻቸው ፕሮዤዎች መካከል አንዱ ነው። ያም ቢሆን ግን አፍሪቃ እንደሚገባት ተጠቃሚ ናት ብለው አያምኑም።

« ቻይናውያኑ በአፍሪቃ እና በቻይና መካከል በእኩልነት እና ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ አሰራር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዳለ ብዙ ጊዜ ይናገራሉ። እርግጥ፣ ቻይና ከአፍሪቃ የምታገኘው ጥቅም የታወቀ ነው፣ ግን ብዙ አፍሪቃውያን የማያሰላስሉት ጉዳይ፣ አፍሪቃ ከቻይና የምታገኘው ምንድን ነው የተሰኘውን ነው። ምክንያቱም፣ የንግዱን ሚዛን ብንመለከት፣ በይበልጥ ተጠቃሚዋ ቻይና መሆንዋን ነው የምናየው። »

Xi Jinping in Südkorea 03.07.2014 Seoul
ሲ ሲ ቲቪምስል AFP/Getty Images

ቻይና ዋነኛዋ የአፍሪቃ የንግድ ተጓዳኝ ናት፣ የንግዱ መጠንም እአአ እስከ 2020 ዓም በእጥፍ እንደሚጨምር እና 400 ቢልዮን ዩኤስ ዶላር እንደሚደርስ ይጠበቃል። በመገናኛ ብዙኃኑም ዘርፍ የቻይና መንግሥት ብዙ ገንዘብ በማውጣት «ሲሲቲቪ» ወይም « «ቻይና ሬድዮ ኢንተርናሽናል » የመሳሰሉትን ጣቢያዎችን በአፍሪቃ ለማስፋፋት እና አፍሪቃውያን ጋዜጠኞችን ለማሰልጠን እየሰራ ነው። የ«ሲሲቲቪ» ወይም « «ቻይና ሬድዮ ኢንተርናሽናል » ዜና እና ዘገባ አቀራረብ በተለይ በኤኮኖሚው ዘርፍ ያተኮረ ሲሆን ፣ አፍሪቃም የበለጸገ አህጉር መሆኗን የሚያጎላ ነው። የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን ስለአፍሪቃ ለብዙ አሰርተ ዓመታት ባቀረቡት አሉታዊ ዘገባ አኳያ አሁን የቻይና መገናኛ ብዙኃን አዎንታዊ አቀራረብ በአፍሪቃውያን ዘንድ ጥሩ አመለካከት አትርፏል።የቻይናን አሰራር የሚተቹት የኤኮኖሚ ምሁር ባለሙያ ኦዊሮ ይህ የቻይና አካሄድ ለኬንያ ሕዝብ የተለየ ዜና የማግኘት ሁኔታ ፈጥሮለታል።

«በኔ አስተያየት የቻይና መገናኛ ብዙኃን ለብዙ ሰው ሌላ አስተያየት እንዲሰሙ ተጨማሪ አማራጭ ወይም ዕድል ከፍቶላቸዋል። እነዚህ አስተያየቶች ፤ ቁጥጥር ይደረግባቸው አይደረግባቸው፣ የኬንያ ሕዝብ በአፍሪቃ እየተሰራ ያለውን ስራ ወይም እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ ሌሎች ሀገራት እንዴት እንደሚያዩት ለማወቅ ጥሩ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። »

የጀርመናውያኑ የፍሪድሪኽ ኤበርት ተቋም ባካሄደው ጥናት መሠረት፣ ቻይና ስለ ሀገሯ እና በአፍሪቃ በልማቱ ዘርፍ ስለምታደርገው እንቅስቃሴ ይቀርባል ለምትለው ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ምላሽ ለመስጠት እና በአህጉሩ የጀመረቻቸው የልማት ፕሮዤዎችም አፍሪቃንም እኩል ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆኑናቸውን ለማጉላት በሚል እየተንቀሳቀሰች መሆንዋን አመልክቶዋል።

ሂልከ ፊሸር/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ